አፍሪካው ልዑል የተሰኘውን መጽኃፍ በሬዲዩ ፋና መተረኩ ተቃውሞ ገጠመው
ኢሳት ዜና :- በፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት በመተረክ ላይ ባለው በታጋይ መዝሙር ፈንቴ ተርጓሚኒት በአቶ ዳንኤል ግዛው ጸኃፊነት የቀረበው መጽሀፍ በአማራ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር እያደረገ ነው በማለት የብአዴን አባላት ተቃውመውታል። አባላቱ በብር ሸለቆ በመካሄድ ላይ ባለው ስልጠና ላይ እንደተናገሩት ሬዲዩ ፋና ታሪካዊ ስህተት እየፈጸመ ነው ፡፡ “የህውሃት ድብቅ አላማ እውን እየሆነ ነው” ያሉት ፤ መካከለኛ እና ታዳጊ የብአዴን አመራሮች ፤ ከደቡብ ወንድሞቻችን ጋር ታሪክን በማሳሳት እና በማጥላላት የትውልድ ጠላትነትን አስፍቶ አሁንም የህውሃት የበላይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው በማለት በጽኑ ተቃውመውታል። ጥያቄው የቀረበላቸው የኢህአዴግ የስልጠና ዋና ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ “መፅሃፉ እየተተረከ መሆኑን በፍጽም አላውቅም” ያሉ ሲሆን ፣ ምላሹን አጣርተው እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡ የመጽሃፉ ትረካ ባሰቸኳይ እንዲቆም የጠየቁት አመራሮች ፣ ፋና ራዲዮን መስማት ማቆማቸውንም ለአቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡ የመለያየት ፖለቲካው መርዛማነት እያሰቃየን ነው ሲሉም አባላቱ አክለዋል፡፡ ከቀናት በሁዋላ ወደ ተለያዩ አካላት በመደወል መረጃ ያሰባሰቡት አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ” ሃይለማርያም እንደፈረመበት እና ፍቅር እስከ መቃብር ሲል እንዳወደሰው” በማሾፍ መልክ መናገራቸውንና ከፋና ሃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ” የመጽሃፉ ትረካ ቢቋረጥ በሬዲዩ ጣቢያው ላይ የሚፈጥረው ችግር ታይቶ ቢያንስ ቢያንስ የአድማጭ አስተያየት ባለመቀበል ልናጠፋው እንሞክራለን” ሲሉ መልስ እንደሰጡዋቸውና ሰልጣኞችን ለማረጋገት እንደሞከሩ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ “መጽኃፉን አንብቤ እከታተለዋለሁ” ያሉት አቶ አዲሱ፣ ስህተቱ መፈፀም የለበትም ሲሉ አክለዋል፡ “ስህተቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሁቱና ቱትሲ አይነት ግጭት የሚፈጥር ነው” ያሉት አባላቱ፣ ከደቡብ ወንድሞቻችን ጋር የሚፈፀም ቅራኔን አንፈልገውም” ሲሉ ለአቶ አዲሱ ገልጸውላቸዋል። ሟቹ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ በረከት ስምኦን መጽሀፉ እንዲታተም ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር ያሉት ምንጮች፣ ሬዲዮ ፋናም የሩዋንዳውን የራዲዮ ሚሊኮልን ስራ እየሰራ ነው ሲሉ” ተቃውመውታል።
No comments:
Post a Comment