Sunday, January 19, 2014

‹‹ለሱዳን የተሰጠ መሬት የለም›› ሪፖርትር መንግሰትን ጠቅሶ አስተባበለ


ግብፅ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ ብድርና ዕርዳታ እንዳይሰጡ እየተንቀሳቀሰች ነው ተባለ

ዓለም አቀፍ አበዳሪና ለጋሽ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ብድርና ዕርዳታ እንዲያቆሙ ግብፅ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን መንግሥት መረጃ እንዳለው አስታወቀ፡፡ 

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር ሦስተኛ ስብሰባ በቅርቡ ያለውጤት ከተበተነ በኋላ፣ በግብፅ በኩል አፍራሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ ረፋድ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና፣ በግብፅ በኩል የቀረበውና በኢትዮጵያና በሱዳን ውድቅ የሆነው ሐሳብ፣ እስካሁን ግድቡን አስመልክቶ የተጀመሩ ውይይቶችን ወደኋላ የሚመልስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ባለሙያዎች ያሉበትና ከሦስቱም አገሮች የተውጣጡ የውኃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የኤክስፐርቶች ፓነል ለአንድ ዓመት በግድቡ ዙሪያ ጥናት አካሂዶ ባወጡት ሪፖርት፣ ከተወሰኑ ቴክኒካዊ ማስተካከያዎች ውጪ ግድቡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ መሆኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

የፓነሉ ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሦስቱ አገሮች የተውጣጡ የውኃ ባለሙያዎች ያሉበት ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን፣ ግብፆች አዲስ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የኮሚቴውን ሥራ በበላይነት እንዲከታተል የሚል ሐሳብ ነው ያቀረቡት፡፡

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል መቋቋም ላይ ሳይሆን፣ ሚናውን በተመለከተ ነው፡፡ በዚህ ልዩነት የተነሳ ያለውጤት ስብሰባው ከተበተነ በኋላ፣ ግብፆች በሚዲያዎቻቸው ‹‹ኢትዮጵያ ለመተባበር እምቢተኛ ሆነች›› እያሉ እያቀረቡ መሆኑንና ከዓለም ባንክ፣ ከአይኤምኤፍና በሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በምንም ምክንያት ኢትዮጵያ በገንዘብ እንዳትደገፍ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆናቸውን መንግሥት መረጃ እንደደረሰው አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ይቋረጣል የሚል እምነት ያላቸው ግብፃውያን፣ የገንዘብ ተቋማቱ ኢትዮጵያ የዚህን ግድብ ግንባታ ካላቆመች በማንኛውም መንገድ የሚያደርጉትን ዕርዳታ እንዲያቆሙ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ግብፃውያን ከዚህ አፍራሽ ድርጊታቸው ተቆጥበው በኤክስፐርቶች ፓነል ሪፖርት መሠረት መተባበራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡ ከተለመደው አፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማስታወቅ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሑመራና በመተማ አካባቢ ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ስለመስጠቷ እየተነገረ ስላለው ጉዳይ መንግሥት አስተባብሏል፡፡ በአንዳንድ ሚዲያዎች ሱዳን በግድቡ ላይ ባሳየችው አዎንታዊ አቋም ምክንያት፣ ሲያወዛግብ የቆየውን ሰፊ የድንበር መሬት መስጠቷ የተዘገበ ቢሆንም፣ አምባሳደር ዲና ግን፣ ‹‹እንኳን መሬት ሊሰጥ ይቅርና በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ውይይትም አልተቋጨም፤ እስካሁንም ስምምነት ላይ የተደረሰ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

ላለፉት አሥር ዓመታት ድንበሩን በተመለከተ ሲሠራ የቆየው የጋራ ኮሚሽን፣ በሁለቱም አገሮች መካከል ያለው ድንበር እንዲካለልና የግጭት መንስዔ የሆነውን ጉዳይ ለመፍታት እየሞከረ መሆኑን፣ በቅርቡ ‹‹ለሱዳን መሬት ተሰጠ›› ተብሎ የተነገረው ግን መሠረት የሌለው ወሬ መሆኑን አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል፡፡ ሪፖረትር ጋዜጣ /
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment