Thursday, January 23, 2014

እነ አንዷለም አራጌ ነገ ሰበር ሰሚ ችሎት ይቀርባሉ፤ ሕዝብ ችሎቱን እንዲከታተል ጥሪ ቀረበ፤


አንባቢዎች ዘንድ የ2005 ዓ.ም የዓመቱ ምርጥ ሰው የሚለውን ስያሜ ያገኘው የሕሊና እስረኛው አንዷዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንንና ክንፈ ሚካኤል ደበበ ነገ ጥር 16 ቀን 2006 (ጃንዋሪ 24 ቀን 2014) በሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርቡ ከቤተሰቦቻቸው አካባቢ የተገኘው መረጃ አመለከተ። እነዚህን የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚፈልጉ ወገኖች 6 ኪሎ የሚገኘው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት እንዲገኙ ጥሪ ቀርቧል።
በአንካሳው የኢትዮጵያ የሽብር ሕግ ከግንቦት 7 ጋር በማያያዝ ሽብር ለመፈጸም በማቀድ በሚል እድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷአለም አራጌ በእስር ቤት በመሆንም በጽናት በመታገል የሰላማዊ ትግል አርማ ሆኗል በሚል በብዙዎች ዘንድ ይወደሳል። ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷዓለም አራጌ የተላለፈበትን ዕድሜ ልክ እስራት ፍርድ፤ እንዲሁም ናትናኤል መኮንን እና ክንፈሚካኤል ደበበ የተላለፈባቸውን ቅጣት ለታሪክ ለመተው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይ የወሰዱት ሲሆን ነገ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሚሰጠው ውሳኔም በቤተሰቦቻቸው ዘንድ በትልቅ ተስፋ እንደሚጠበቅ ጨምሮ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ነገ በስድስት ኪሎ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ሲሰየም እነ አንዷለም አራጌም አብረው የሚቀርቡ ሲሆን የሚታገሉለትና መስዋዕትነት እየከፈሉለት የሚገኘው ሕዝብ በችሎቱ በመገኘት ይህን «ፍትህ የምትዋረድበትን
ወይም ፍትህ የምትታይበትን» ታሪካዊ ቀን እንዲመለከት ከቤተሰቦቻቸው እና ከወዳጆቻቸው ጥሪ ቀርቧል። ይህን ተከትሎም በፌስቡክና በተለያዩ የማህበራዊ ድረገጾች «እነ አንዷለም ፍትህ ያግኙ፤ ይፈቱ» የሚለው ቅስቀሳ ቀጥሏል።

No comments:

Post a Comment