ሰናይ ገ/መድህን ይባላል። በኤርትራ ቴሌቪዥን እና ሬድዮ የአማርኛ አገልግሎት ክፍል ውስጥ እ.አ.አ. ከ1998 እስከ 2011 ድረስ ሰርቷል። በዚሁ የረዥም ጊዜ የጋዜጠኝነት ሙያው ነበር ሰናይ ከተስፋዬ ገ/አብ ጋር አስመራ ውስጥ በቅርብ ለመተዋወቅ የበቃው። ዛሬ ኗሪነቱ ሜልበርን፣ አውስትራሊያ የሆነው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ሰናይ ገ/መድህን ለስለስ ብሎ በተጻፈ ቋንቋ አመሻሹ ላይ የሻእብያ ሰላይ መሆኑን በተረጋገጠው “የቢሾፍቱ ልጅ” እንዲህ እያለ ይተርክልናል። መልካም ንባብ።
ተስፋዬ ከደቡብ አፍሪካ አስመራ መግባቱን አንድ ኤርትራዊ ደራሲ ወዳጄ ነገሩኝ። ያረፈዉም አስመራ ዉስጥ ከጥቂት ታላላቅ ተብለዉ ከሚታወቁት በአንዱ በሆነዉ ሳቫና ሆቴል ነበር፡፡ ወዳጂ ከተስፋዬ ጋር ትዉዉቃቸዉ ኢትዮጵያ እያሉ መሆኑን ከገለጡልኝ በሁዋላ አብረን ሄደን እንኩዋን በሰላም መጣህ እነድንለዉ ጋበዙኝ። አላቅማማሁም። በጋዜጠኝነቱና ደራሲነቱ ብቻ ብሎም ባነጋጋሪዉ የቡርቃ ዝምታ ስሙ የተነሳዉን ተስፋየን ለመተዋወቅና ለማዉጋት እንዴትስ አቅማማለሁ? በዚያ ላይ እኔም ጋዜጠኛ። ወሬ አነፍናፊ። ያልተመለሰዉ ባቡር የሚለዉን መፅሐፉን ኢትዮጵያ እያለሁ አንብቤለት ነበር፡፡ የቡርቃ ዝምታ ሲወጣ ኤርትራ ብሆንም የመፅሃፉን ይዘት በተመለከተ ጋዜጦች ላይ የተስተናገዱ የተለያዩ አስተያቶችን አንብቢያለሁ፣ ከሰዎች ጋርም ተወያይቼ ነበር። ሙሉ መፅሃፉን አላነበብኩም። ያኔ ከወዳጄ ጋር እንደወትሮዉ ሁሉ ስለ ፅሁፎቹ እየተወያየን ነበር የደረስነዉ፡፡ አልነበረም፡፡ ወዳጄ ቀጠሮ አልነበራቸዉም እዚያ ማረፉን ብቻ ከሰዉ ሰምተዉ እንግዳ ስለሆን አናጣዉም በሚል ነበር ያዘገምነዉ። ዕዉቁን ኢትዮጵያዊ የጠፈር ሳይንቲሰት ኢንጅነር ቅጣዉ እጅጉን ባልገመትኩት ሁኔታና በአድናቆት ተሞልቼ የተዋወቅኩትም ቃለመጠይቅ ያደረግኩላቸዉም እዚሁ ሆቴል ተገኝቼ ነዉ ፡፡ አስመራ በቆዩባቸዉ ጥቂት ቀናት ያረፉት እዚሁ ሳቫና ሆቴል ነበር። አብረዋቸዉ ከመጡ ሁለት ኢተትዮጵዉያን ጋር፡፡ ጊዜዉ 2004 አመጣጣቸዉና ቆይታቸዉ ሚስጥራዊ፤ የሚያዉቁትና የተገናኙትም ከፕሬዚዳንት ኢሳያስና ኮ/ል ጠዓመ (መቐለ) ከሚባለዉ ወታደራዊ ስላይ ጋር ነበር፡፡ ጌታ ነፈሳቸዉን ይማር።
እነሆ ተስፋዬ ገብረአብም እዚሁ ሆነ ያረፈዉ። አጋጣሚ ወይንስ…. ለሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ ለተስፋየ የሚሰጥ የስልክ ቁጥር ነግረን ተመለስን። የኔንም ጭምር። በሚቀጠለዉ ቀን ተስፋየ ለኔም ለወዳጄም ደወለና ቀጠሮ ያዝን። ቀጠሮአችን እዚያዉ ያረፈበት ሳቫና ሆቴል ነበርና ከወዳጄ ጋር አብረን ሄድን። ከኔ ጋር የመጀመሪያ የትዉዉቅ ሰላምታ ከወዳጄ ጋር ደግሞ የአዲስአበባ ጥቂት የግንኙነት ጊዜያቶቻቸዉን አንስተን አወጋን። በጋለ መንፈስ የተሞላ ነበር ጨዋታችን። ተስፋየ መፅሃፍ ለማሳተም ዝግጅቱን ማጠናቀቁን / የጋዜጠኛዉ ማስታዎሻን / ስለ ስነ ፅሁፍ ሚድያ ብሎም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ ብዙ ነገሮችን በቆይታችን አንስተናል። አስመራ ስለከተሙት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች ስናወራም የዮናታን ዲቢሳ ስም ተነሳ። “ዮናታን እዚህ ነዉ ያለዉ አይደል?” ሲል ጠየቀንና መኖሩን ነገርነዉ፡፡ ሊያገኘዉ እንደሚፈልግ በጉጉት ሲያየን ወዳጅነታችንን ገለፅልነት። ችግር የለዉም ለማለት። ዮናታን በሽግግሩ ዘመን ራዲዮ ፋናን በቦርድ ሰብሳቢነት ሲመራ በነበረበት ወቅት የተስፋየ አለቃ ነበር። የቀድሞ የኢህዲን ነባር ታጋይና ከዚያም የኦህዴድ መስራችና ስራአስፈፃሚ የነበረዉ ዮናታን ኦነግን 2002 አካባቢ ተቀላቅሎ አስመራ ነዉ ያለዉ።አሁን እንኩዋን ኦነግና ፖለቲካ በቃኝ ብሎ ከኤርትራ መዉጪያ የወንድ በር እየጠበቀ መሆኑን አዉቃለሁ። በኤርትራ የ15 ዓመት ኑሮየ ካፈራሁዋቸዉ የቅርብ ወዳጆቼ አንዱ ነዉ። በሞቀ የጨዋታችን መሓል ድንገት ተስፋየ “በኤርትራ የጋዜጠኞችና ደራሲያን ማህበር ስለሌለ ማህበር ማቁዋቁዋም አለብን” ሲል ሃሳብ ሰነዘረ። እኔና ወዳጄ ተያየን ፡፡ “እንዲህ ዓይነት ነገር አዚህ አይወዱም አታስበዉ !” አከታትለን መለስንለት። በጥርጣሬ ዓይን መተያየታችንንም አስታዉሳለሁ፡፡
ከተስፋየ ጋር የመጀመሪያ ዕዉቂያ አድርጌ ስንመለስ ከወዳጄ ጋር ስለ ተስፋየ ጥቂት ነገሮችን አንስተናል፡፡ በተለይም ያረፈበት ሆቴል በአስመራ ዉድ ከሚባሉት አንዱ በመሆኑ “ወጭዉን እንዴት ይችለዋል ምክንያቱም ቋሚ ገቢ የለዉም፡፡ በዚያ ላይ እንደነገረን ኤርትራ ረዘም ላለ ጊዜ የመቀመጥ ሃሳብ አለዉ፤ ስለዚህ ቤት መከራየት ነዉ የሚያዋጣዉ ፡ ወይንስ ወጭዉን የሚሸፍንለት ይኖር ይሆን የሚሉ የወዳጅነት ሃሳቦችን ተለዋወጥን፡፡ “ከባለቤቱ በላይ ኣዋቂ እንትን ነዉ” ለሚለዉ ብሂል አልተጨነቅንም። የጋዜጠኛዉ ማስታወሻ የተባለዉ መፅሃፉ ኤርትራ እንደሚታተምና ገበያ ላይ እንደሚዉል የነገረንን ግን በጥርጣሬ አማነዉ፡፡ ያዉም አሳታሚዉና አከፋፋዮቹ ተቁዋማት የመንግስት (ህግደፍ) የሆኑት ሳቡር ማተሚያ ቤትና አዉገት መፃህፍት ሙዚቃና ቪዲዮ አከፋፋይ የመሆናቸዉ ነገር ተስፍሽ የህግደፍ ባለሙዋል እየሆነ ነዉ መሰል ማለታችን አልቀረም፡፡(ሁለቱም በህግደፍ ስር ያሉ የንግድ ተቁዋማት ናቸዉ)። አማርኛ መፃህፍት ሙዚቃና ቪዲዮ ኤርትራ ዉስጥ እነኩዋን ሊታተሙ እንደ ወንጀለኛ እየታደኑና እያስቀጡ ባለበት ሁኔታ ታዲያ ህግደፍ ለተስፍሽ እንዳሻህ በአማርኛዉ ገበያ ፈንጭበት ማለቱ ያለ ቃልኪዳን አልነበረም፡፡ በነገራችን ላይ ተከታዩ የደራሲዉ ማስታወሻ መፅሃፉም የታተመዉም ስርጭቱም ከዚያዉ ነዉ፡፡ የመፅሃፉ ገበያ ቅብብሎሽ የተካሄደዉም ከእዚያዉ ከአስመራ በህግደፍ ደላላነት ነዉ፡፡ ሻጭ ተስፋየ አትራፊ …፡፡ ነገርን ነገር እያነሳዉ ሄደ መሰለኝ። ተስፋየን ያረፈበት ሆቴል ሄደን ካገኘነዉ በሁዋላ ሳንገናኝ ሰነባበትን። ምነዉ ጠፋ ማለታችን ተገቢ ነበር። ምክንቱም ላገሩ እንግዳ መሆኑና በቋንቋም በተመሳሳይ የዉይይት ርዕሰ ጉዳዮችና ለሙያ ነክ ወግ እንፈላለጋለን ብለን በመጠበቃችን። ዮናታንንም አላገኘዉም። ዮናታን ግን ተስፋየን በሩቅ እንዳየዉ ነግሮኛል።
ከወር ወይም ሁለት ወር በኋላ ይመስለኛል የጋዜጠኛዉ ማስታወሻ ገበያ ላይ ዋለ። የአስመራ ዋናዉ ሃርነት ጎዳና ላይ ሳይቀር በመፅሃፍ ሻጮች ተቸበቸበ። 100 ናቅፋ። በዚያዉ ሰሞን አለቃየ ጠራኝና “የጋዜጠኛዉ ማስታወሻ መፅሃፍን በራዲዮ ትረካ ታቀርበዋለህና እንካ ቀድመህ አንብበዉ” ሲል አዘዘኝ፡፡ ሙሉ በኢንተርኔት የሚሰራጩና ረዘዣዥም ትረካ የሚያሻቸዉን ፅሁፎች ብዙ ጊዜ አንብቢያለሁ። ለምሳሌ የቀድሞ አየር ሃይል ባልደረባ የነበሩት ካፕቴን ተሾመ ተንኮሉ ያወጡትን ረዥም ግለ ታሪክ ሙሉዉን፤ የዶክተር ነገደ ጎበዜን ህገ መንግስትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ በሚል ካሳተሙት መፅሃፍ አብዛኛዉን፡፡ ሙሉ መፅሃፍ በትረካ ሲስተናገድ ግን የጋዚጠኛዉ ማሰታዋሻ ለፕሮግራማችንም ለኔም የመጀመሪያ ነበር። የበላይ ትዕዛዝ ነዉ። ለነገሩ የትረካ ንባብብን በፍቅር ስለምወድ ቅር አላለኝም። በወጋየሁ ንጋቱ የፍቅር እስከ መቃብር ትረካ ፍቅር እንደተለከፍኩ አሁንም ያ የትረካ ፍቅር ዉስጤ አለና። በአንድ ሌሊት መፅሃፉን አጋመስኩና ለቀረፃ ዝግጁ ሆንኩ።ከዚያ ስቱዲዮ ልዩ የቀረፃ ፕሮግራም ተይዞልኝ በአርቲስት ትግስት ዉብና
ለስላሳ የሙዚቃ ቅንብር ሲዲ እያጀብኩ ትረካዉን ነካሁት። በተለያየ ስሜት ዉስጥእየሆንኩ፤ በሚያስቀዉ ሳቅ እየተፈታተነኝ በግነቱ እየተገረምኩ ፡፡ ከስር ከስር በቅድሚያ እየተቀረፅኩ ለአየር በቃ፤፤
ለስላሳ የሙዚቃ ቅንብር ሲዲ እያጀብኩ ትረካዉን ነካሁት። በተለያየ ስሜት ዉስጥእየሆንኩ፤ በሚያስቀዉ ሳቅ እየተፈታተነኝ በግነቱ እየተገረምኩ ፡፡ ከስር ከስር በቅድሚያ እየተቀረፅኩ ለአየር በቃ፤፤
ታዲያን በዚያን ሳልስት ተስፋየን ከዉጭ አገልግሎት ዳይርክተሩ አለቃችንና ከአንድ እንግዳ ሰዉ ጋር ማስታወቂያ ሚኒስቴር ካፊተርያ አየሁት። እንግዳዉን ሰዉየ አዉቀዋለሁ። ኤርትራ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ተቃዋሚዎችን በበላይነት ከሚያዙና ከሚያስተባብሩት ኤርትራዊያን ወታደራዊ የስለላ ኮሎኔሎች አንዱ ነዉ። ኮሎኔል ፍፁም ወይንም በቅፅል ስሙ ( ሌኒን )። ኮሎኔል ፍፁም ከእኛ ክፍል ጋር በቅርብ ስለሚሰራ በሚገባ እንተዋወቃለን። ሶስቱን አንድ ላይ እንዳየሁዋቸዉ የእለቱ ጉዳይ ወዲያዉ ገባኝ። ከጥርጣሬ በላይ። ይሄዉም አለቃችን ኮሎኔሉንና ተስፋየን ለተልዕኮ እያስተዋወቀ ነዉ። ምክንያቱ ደግሞ የተስፋየን መፅሃፎች ወደ ኢትዮጵያ በድንበር በድብቅ ማሻገርና ማሰራጨት ። ኮሎኔሉ በእኛ ፕሮግራም የተላለፉ የተለያዩ የፕሮፓጋንዳ ህትመቶችና ዲቪዲዎችን በታማኝ ኢትዮጵያዊያን ተቃዋሚዎች አማካኝነት በድንበር ማሸጋገሩን አዉቃለሁ። ይሄዉ ተስፍሽም ከኤርትራዊያን የስለላ ኮሎኔሎች ጋር የሚስጥር ግንኙነቱን ሲያደርግ አየሁ። ከግንኙነቱ በሁዋላ ቢያንስ የአማርኛዉ ክፍል ጋዜጠኞችን ሰላም ይለናል ብለን ጠብቀን ነበር አላደረገዉም። ከኮሎኔል ፍፁም ጋር መገናኘቱ እንዲታወቅበት አልፈለገም ይሆናል። ማንም ልብ እንዳላለዉ አይነት ሹልክ ብሎ ወጣ። እርግጠኛ ነኝ ካፌቴርያ ከነበርነዉ ዉስጥ ከእኔ በቀር ተስፋየ ገብረአብ መሆኑን ያዋቀ አልነበረም። በግርምት ኣሻግሬ እያየሁ ነበረና ከሄዱ በሁዋላ አብረዉኝ ለነበሩት “ከአለቃችንና ኮሎኔል ጋር የነበረዉ ተስፋየ ገ/አብ ነዉ ስላቸዉ” የቱ የቱ ብለዉ ተከታልለዉ ወጡ።ተስፋየ ፈጥኖ የኮሎኔል ላንድክሩዘር ላይ ተሳፍሮ ሄዱዋል። ከዚህ በሁዋላ ተስፋዬ ለገዥዉ ፓርቲ ቅርበት ያለዉ መሆኑን ለመገመት አዋቂ ቤት መሄድ አላሻኝም፣ ገና ከጅምሩ ማለት ነዉ፡፡
የጋዜጠኛዉ ማስታወሻ ትረካ በተከታታይ ሁለት ሶሰት ዕሁድ ዓየር ላይ በዋለ ሰሞን ተስፋይ ቢሮ ስልክ ደወለልኝና ቀጠሮ ያዝን፡፡ ኒያላ ሆቴል አመሻሽ ላይ ተገናኝተን ገና ሰላምታ ሳንጣገብ ስለመጽሃፉ ትረካ አድናቆቱን አዥጎደጎደዉ። በነገራችን ላይ አንተ ነህ አይደል የምትተርከዉ? እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በፐሮግራሞቻችን የአቅራቢ ስም አይገለጥም ነበርና ሰዎች ቢደነጋገሩ አይገርመንም ነበር፡፡ ተስፍሽን ግን እንዴት አወቅ አላልኩትም፡፡ “እኔ ከጻፍኩት በላይ እያጣፈጥክ ያንተ ወግ እሰኪመስል ድረስ ነዉ እየተረከዉ ያለኸዉ”፡፡ ከትረካዉ እየጠቃቀሰ ወጉን በጂን ያወራርድዉ ያዘ፡፡ እኔም ከታሪኮቹ እያነሳሁ እየጣልኩ የምሽቱን ጨዋታ አጀብኩት፡፡ በይዘቱ ላይ መነጋገሩን አልፈለግኩም፡፡ የማልስማማባቸዉ ቢኖሩም፡፡ ትረካዉን በተመለከተ ግን ባድናቆቱ ዉነት ዉነት ሙቀት በሙቀት ሆንኩላችሁ። የአማርኛ ስነ ጥበብ የጠማዉ ኤርትራዊም በትረካዉ እየረካ መሆኑን ከግራም ከቀኝም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከምናገኘዉ ወሬ ላይ የባለቤቱ በላዩ ለይ ሲታከልበት …፡፡ ለነገሩ ሳካብድ ነዉንጂ የህዝባዊ ግንባር ፖለቲካ እጅ እጅ ላለዉና የአማርኛ ሙዚቃ እንዳይሰማ እግድ ለተጣለበት ኤርትራዊ ትረካዉ ፍቱን መዝናኛዉ ቢሆን ምን ይገርማል አትሉም።
ከዚያ በሁዋላ ከተስፍሽ ጋር ያለቀጠሮ ቁዋሚ ተሰላፊ ከሆነበት ኒያላ ሆቴል መገናኘታችን ልሙድ ሆነ፡፡ ዋል አደር ሲል በተደጋጋሚ ከዉስን ኤርትራዉያን ወጣቶች ፀሃፍት ጋር አገኘዉ ጀመር። በህግደፍ ስር የሚሰሩና የዘመኑ ተጠቃሚ የሚባሉ ናቸዉ። በጭፍን የህግደፍ ደጋፊነታቸዉ ይታወቃሉ። ህግደፍ ጠቀም ያለ አበል የሚቆርጥላቸዉ ወጣት ምሁራን በብዛት አሉ። አብዛኛዎቹ (ሁሉም እንበል) ደርግ ከኤርትራ ሲባረርና ህግደፍ ሲገባ የአስመራ ዩኒቨርስቲ የነበረበትን የተማሪ ርሃብ ያስታገሱ ናቸው። ከ1.00 -2.00 ነጥብ ለዲግሪ ገብተዉ ገዋን ለብሰዉ የወጡ። ኢነጅነር ዳኛ…ሆነዋል። አንዱ በህግደፍ የበላይነት የሚታተመዉ ሀዳስ ኤርትራ ጋዜጣ አከፋፋይ ነዉ። ሌላኛዉ የህግደፍ ወጣቶች ማህብር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነዉ። ሌላኛዉም… ተስፋየም ወደ ቢጤዎቹ ተጠጋ ማለት ነዉ፡፡ ተስፋዬ ያለከለላና መከታ መኖር አይችልምን የምትል ነገር ወጋ አደረገችኝ። በአማርኛ ካለዉ ተወለድ ወይ ካለዉ ተጠጋ የሚለዉን ብሂል ልብ ይሉዋል፡፡ በትግርኛ ደግሞ ተመሳሳዩ ሲኖር ካለዉ ተጠጋ የሚለዉን ወደ ጋራ ተጠጋ ይሉታለል ( ….ናብ ጎቦ ተፀጋእ )። በወታደራዊ አባባል ገዥ መሬት ያዝ እንደማለት ነዉ።፡ስለዚህ ተስፍሽ ገዥ መደቡንም ካዝናዉንም እንዴት መጠጋት እንደሚችል ጥሩ አድርጎ ለምዶታል ማለት ነዉ። ግን ከረፈደ ነዉ ህግደፍን የሙጥኝ ያለዉ። ምክንያቱም ህግደፍ ራሱ ከለላ ፍለጋ ኩዋታርን ኢራን እጅ በሚያይበት አይዞህ ባዩን ጋዳፊን በዉርደት ባጣበት ብሎም ያየነፃነት ፋኖነቱ እንደጉም በበነነበትና በወገኖቹ ኤርትራዊያን ሳይቀር አይንህን ላፈር በተባለበት ጊዜ ነዉና የተጎዳኘዉ። ነገርን ነገር ካነሳዉ ዘንዳ ተስፋዬ እርም ኤርትራዊ ብሎ ኦሮሞነትን የሙጥኝ ያለዉ ለዚህ ይሆን? ምክንያቱም በክፉ ጊዜ ህግደፍን መወዳጀቱ በብዙ ኤርትራዊያን ሙሽሙሽ (የማይረባ ) መባሉን መቼም ሳይሰማ አይቀርም። እዚች ላይ እንዲያዉም ለኢሳያስ አፈወርቂ የቀኝ እጅ ከሆኑትና ለብዙ በኤርትራ ለሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ተቃዋሚዎች ደብዛ መጥፋት (ኮ/ል ታደሰ ሙሉነህን) ጨምሮ ተጠያቂ ከሆኑት ቁልፍ ወታደራዊ ስለላ ኮሎኔሎች ከአንዱ ከ ኮ/ል ዮናስ ሴት ልጅ ጋር ጋብቻ ቢጤ መስርቶ ልጅ መዉለዱን ጠቆም ብናደርግስ? ጋብቻዉ በኣጋጣሚ ከልብ ለልብ ፍቅር ነዉ ወይንስ ፖለቲካዊ ጋብቻ? በየዋህነት እንለፈዉ ይሆን ከሆነ የግጥምጥሞሽ ነገር እንላለን ግና የህዝባዊ ግንባርን አያሌ ፖለቲካዊ ጋብቻዎች ስንመነዝር ( ኢሳያሰ ራሳቸዉ በትግሉ ዘመን ሆነ ብለዉ ገደሉት የሚባለዉን የአካለጉዛይ ተወላጁን ታዋቂ አመራር አብረሃምን አካባቢ ሰዎች ለማስደሰትና ለመያዝ የአካለጉዛይ ተወላጅ የሆነችዉን ታጋይ ሳባ ሀይሉን አግብተዉ መዉለዳቸዉን ማጣቀሻ ስንመዝዝ ፡፡ከሳባ በፊት የሃማሴን ልጅ የነበረችዉ ሚስታቸዉ አሁንም አስመራ እንደምትገኝ በመዘከር ነዉ) ኢሳያስ ፖለቲካዊ ጋብቻቸዉ እየኮሰኮሳቸዉ ሳይሆን ይቀራል በአደባባይ የሚማግጡት፡፡በፍቅር ላይ ያልተመሰረተ ጋብቻ እንዴት አይኮሰኩስ። ነገርን ነገር እየመዘዘዉ የጎንዮሽ እየነጎደ ተቸገርኩ እኮ ጃል! ስለዚህ ተስፍሽም ጋብቻዉ ፖለቲካዊ ሆኖ የወደፊቱ የኤርትራ ኑሮ ከኮሰኮሰዉና እነ ወዳጁ ዳዉድ ኢበሳ በለስ ከቀናቸዉ ኦቦ ተብሎ ደብረዘይት ለመመሸግ ቀብድ መክፈሉ ይሆን! ሰዉየዉ እኮ ተስፍሽ ነዉ ፡፡
በነገራችን ላይ ተስፋየን ምነዉ የነዳዉድ ኢብሳ ብቻ ወዳጅ አደረከዉ የሁሉም ኦሮሞ ወዳጅ አይደለምን የሚል ጠያቂ እንደሚኖር አስባለሁ፡፡ ለዚህ ትዝብት ቢኖረኝ ነዉ፡፡ በቀጣይ እማቀርበዉ፡፡
*ተስፋየ ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ ሌላ አሁን ስሙን የማልገልጠዉ ሰዉ እና እኔ ሆነን ያደረግነዉ ጭዉዉት።
*የተስፋየ የአስመራ ኒያላ ሆቴል (የመንግስት ሆቴል ነዉ ) ሃድራዉና የጂን ላይ ወጎች
*ተስፋየ የኢትዮጵያን ሪቪዉ ኤልያስ ክፍሌና የእኔ የአንድ ሰሞን ድርድሮች
*የወግ ገጠመኞች ነገር ከተነሳ ተስፋየና እኔ ካነሳናቸዉ ከጣልናቸዉ የታዘብኩትን (እሱም ታዝቦኝ ይሆናል )
*የደራሲዉ ማስታወሻ ላይ ካሉት ባለታሪኮች ፡ ኮ/ል አለበል አማረ ሌ/ኮ/ል አበበ ገረሱ እና የወሎዉን ባለታሪክ
የመሳሰሉትን የዘከርኩትን እያስታወሰኩ በቀጣይ ላወጋችሁ አስባለሁ ፡፡
የዚያ ሰዉ ይበለን
*የተስፋየ የአስመራ ኒያላ ሆቴል (የመንግስት ሆቴል ነዉ ) ሃድራዉና የጂን ላይ ወጎች
*ተስፋየ የኢትዮጵያን ሪቪዉ ኤልያስ ክፍሌና የእኔ የአንድ ሰሞን ድርድሮች
*የወግ ገጠመኞች ነገር ከተነሳ ተስፋየና እኔ ካነሳናቸዉ ከጣልናቸዉ የታዘብኩትን (እሱም ታዝቦኝ ይሆናል )
*የደራሲዉ ማስታወሻ ላይ ካሉት ባለታሪኮች ፡ ኮ/ል አለበል አማረ ሌ/ኮ/ል አበበ ገረሱ እና የወሎዉን ባለታሪክ
የመሳሰሉትን የዘከርኩትን እያስታወሰኩ በቀጣይ ላወጋችሁ አስባለሁ ፡፡
የዚያ ሰዉ ይበለን
ሠናይ ገብረመድህን (ጋዜጠኛ)
አዉስትራሊያ ፣ሜልበርን
ጥቅምት 2007
አዉስትራሊያ ፣ሜልበርን
ጥቅምት 2007
ተስፋዬማ የእጁን ከኢሳያስም ከኤርትራ ህዝብም ከትግራይን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህዝብም ያገኛል ፡፡
ReplyDelete