Tuesday, November 4, 2014

መንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጥሞታል


1 ዶላር እስከ 22 ብር እየተሸጠ ነው፤"የብርን ዋጋ በቅርቡ ሊወርድ ይችላል"

etb-100-ethiopian-birr

የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደገጠመው የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጹ፡፡ አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አጥኚ እጥረቱ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
ከ20 ቀናት በፊት እያንዳንዱ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሬ ይሸጥ እንደነበር የተናገሩት ምንጮች፣ ከ20 ቀን ወዲህ ግን በሁሉም የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ማንኛውም አይነት የውጭ ምንዛሬ እንዳይሸጥ በደብዳቤ (circular ዞሯል) ተከልክሏል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ዜጎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደተቸገሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ “በተለየ ሁኔታ የሚሸጥላቸው ሰዎች ከጉዞ ወኪላቸውና ከበላይ አካል ይዘውት በሚመጡት ደብዳቤ መሰረት ብቻ ነው ምንዛሬ ሊያገኙ የሚችሉት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እንደበፊቱ ማንም የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አይችልም” ሲል አንድ የንግድ ባንክ ሰራተኛ ገልጾዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ የተከሰተው በዶላር ምንዛሬ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የውጭ ምንዛሬዎች ላይ መሆኑንም ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ አሁን ላይ አንድ የአሜሪካ ዶላር በጥቁር ገበያ እስከ 22 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ከብሄራዊ ባንክ አካባቢ የደረሱት የነገረ ኢትዮጵያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት መንግስት ቀደም ሲል በIMF የቀረበለትን የብር ዋጋን የመቀነስ “devalue” የማድረግ ጥያቄ መቀበሉ እንደማይቀር ታውቋል፡፡ “አሁን ያለው ሁኔታ እንደሚያሳየን መንግስት የብርን ዋጋ በቅርቡ መቀነሱ አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡ አንዳንድ ‘አርቲፊሻል’ የውጭ ምንዛሬ እጥረቶች ቢኖሩም ዋናው የችግሩ መነሻ ግን የብር ዋጋ መቀነሱ ጉዳይ ነው” ሲሉ የብሄራዊ ባንክ የኢኮኖሚ አጥኚው ለነገረ ኢትዮጵያ አስረድተዋል፡፡
ሰሞኑን መንግስት ለወራት ተከልክሎ የነበረው የአረብ ሀገራት የስራ ጉዞ እንደገና እንዲጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ይህም ወደ አረብ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎች ተጨማሪ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ከማሰብ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል፡፡(ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)

No comments:

Post a Comment