Tuesday, January 21, 2014

“የአዲስ አበባ ተማሪዎች ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ተጋልጠዋል”


“የአዲስ አበባ ተማሪዎች ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ተጋልጠዋል”
* ሴት የቢሮ ሠራተኛ ሴቶች በወሲብ ንግድ ኑሮአቸውን ይደጉማሉ
* ተማሪዎች ያለዕድሜያቸው ጫት፣ ሲጋራና ልቅ ወሲብ ይጀምራሉ
በአዲስ አበባ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች፤ ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለቶች እንደተጋለጡ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር “ስነምግባር ለእድገት ሁሉ መሠረት ነው” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በቀረቡት ጥናቶች በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ በየትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ባሉ ህገወጥ የአልኮል፣ የአደንዛዥ እጽ መጠቀሚያ እና የወሲብ ፊልሞች ማሣያ ቤቶች መበራከት የተነሣ ለችግሩ ተጋላጭነታቸው በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተጠቁሟል፡፡
አብዛኞቹ ተማሪዎች ወሲብ መፈፀም የሚጀምሩት በዚሁ የትምህርት ደረጃ ላይ እያሉ ነው ተብሏል፡፡ ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን አክሊሉ በጥናታቸው እንዳመለከቱት፤ ተማሪዎች ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ፣ ጫት እና ልቅ ወሲብ የሚጀምሩት በአብዛኛው ሁለተኛ ደረጃ ከገቡ በኋላ ሲሆን 41.5 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲጋራ ማጨስ እንደሚጀምሩ ጠቅሰው፤ 67.1 በመቶ ያህሉ ደግሞ በዚህ የትምህርት ደረጃ ወሲብ መፈፀም ይጀምራሉ ብለዋል፡፡
18.1 በመቶ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም ያለ እድሜያቸው በሲጋራ ሱስ የሚጠመዱ ሲሆን 20.6 በመቶዎቹም በዚህ የእድሜ እርከን ውስጥ ወሲብ መፈፀም እንደሚጀምሩ ተጠቁሟል፡፡ የአልኮል መጠጥ እና የጫት ተጠቃሚነትን መጠን በተመለከተ ከሌሎች የትምህርት ደረጃዎች ይልቅ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በከፍተኛ ደረጃ የድርጊቱ ጀማሪዎችና አዘውታሪዎች እንደሆኑ ጥናቱ ይገልፃል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ ተማሪዎች መካከል 51.4 በመቶዎቹ የአልኮል ተጠቃሚነትን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ የጀመሩ ሲሆን፤ 27.2 በመቶዎቹ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ጀምረዋል፡፡ 44.6 በመቶ የሚሆኑት ጫት የጀመሩት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲሆን፤ 15.1 በመቶዎቹ ደግሞ የ1ኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
በተለይ የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በከፍተኛ መጠን ያለእድሜያቸው ለአጓጉል ድርጊቶች መጋለጣቸው፣ በስነምግባር የታነፁ ዜጐችን በማፍራት ረገድ አገሪቱ ፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነው ብለዋል – ጥናት አቅራቢዋ፡፡ እጽና አልኮል መጠቀም፣ ልቅ ወሲብ ከመፈፀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ያመላከቱት አጥኚዋ፤ በተለይ ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት የከተማ ልጆች ሲሆኑ ወላጆቻቸው የተማሩ የሚባሉና ከፍ ያለ የገንዘብ አቅም ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች በአንፃሩ የገንዘብ አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ፣ አልኮልና እፆችን እንዲሁም የወሲብ ተግባራትን እንደልባቸው ለመፈፀም እንደሚቸገሩ ተጠቁሟል፡፡
በእነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ያሉና የአቻ ግፊት ሳይበግራቸው ከእነዚህ ሁሉ ሱሶች ነፃ ሆነው የተገኙት ለስነ ምግባራቸው መታነጽ ምክንያቱ፣ በወላጅ ምክር ያደጉና የሃይማኖት ጥንካሬ ያላቸው መሆኑን ያመለከቱት ጥናት አቅራቢዋ፤ የሃይማኖት ተቋማት በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ ለመስራት ቢሞክሩ የበለጠ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ በእኚሁ ጥናት አቅራቢ የቀረበው ሌላው ርዕሰ ጉዳይ በጐልማሶች ላይ ያተኮረ ሲሆን በሀገራችን ከ150ሺህ በላይ ሴተኛ አዳሪዎች እንዳሉ ቢገመትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሴት የቢሮ ሠራተኞች እና ተማሪዎች በወሲብ ንግድ ተሰማርተው በአቋራጭ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ኑሮአቸውን እየደጐሙ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ለዚህ ልማድ መስፋፋት ደግሞ ባለሃብቶችና በእድሜ የገፉ ሰዎች አማጋጭ እየሆኑ መምት፣ የመዲናዋ የቱሪስቶችና ዓለማቀፍ ክንውኖች ማዕከልነቷ ማደጉና የጥበብ ውጤቶች ስለ ወሲብ የተዛባ አመለካከት ይዘው ብቅ ማለታቸው በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡ ማሣጅ ቤቶችና ራቁት የዳንስ ቤቶች ወሲብ ንግድ መስፋፋቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
ለእነዚህ ሁሉ የስነምግባር ጉድለቶችና ማህበረሰባዊ እሴቶች ውድቀት የህግ ክፍተት መኖሩ ትልቅ ሚና እንዳለው ባይካድም፣ በመንግስት ሚዲያዎች ሳይቀር የሚተላለፉ የማስታወቂያ መልዕክቶች፣ የቃላት አመራረጥና የፕሮግራም አቅራቢዎቹ አለባበስ፣ የመረጃዎች ፍሬ ሃሳብ እና ስነ ምግባር የጐደላቸው ጽሑፎች በስፋት መስተናገድ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብሏል፡፡ ሌላው ጥናት አቅራቢ አባ በአማን ግሩም የተባሉ የሃይማኖት አባት በበኩላቸው፤ ከቤተሰብ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ የመከባበር እሴት መጥፋት፣ ማታለልና ሙስና መስፋፋት ለትውልዱ በስነምግባር አለመታነጽ እንደምክንያት ካቀረቧቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ይሄን ለመቀየር ከሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች የአርአያነት ተግባር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አባ በአማን፤ እነዚህ አካላት የትውልዱን ስነምግባር በማነጽ ረገድ ያላቸው ሚና እንዲጐላ ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ምቀኝነት፣ ውሸት፣ ሃሜት፣ ስርቆት፣ ሙስና፣ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የአደንዛዥ እፅ ዝውውርና ተጠቃሚነት እንዲሁም ሽብርና ጦርነት በዓለም ላይ መበራከታቸው ለስነምግባር እሴቶች መጓደል ምክንያት መሆኑን የዘረዘሩት ሌላው ጥናት አቅራቢ ሐጂ አብዱልሃማድ አቡበከር፤ መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ በጋራ ኢትዮጵያውያን ወጣት ተማሪዎች ከእነዚህ የስነምግባር ጉድለቶች የሚርቁበትን አቅጣጫ ማሳየት እንደሚገባቸው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የከተማው የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዲሳሞ ኦቶሬ በበኩላቸው፤ ተማሪዎችን ከአልኮል፣ አደገኛ እጽ፣ ጫት እና ከወሲብ ሱስ ተጋላጭነት የራቁ ለማድረግ ቢሮአቸው የተለያዩ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንም፣ ለእነዚህ መጤ ልማዶች መስፋፋት ምክንያት የሆኑ የንግድ ቤቶች ከትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚርቁበትን የወሰን መጠን የሚያስቀምጥና ህጋዊ ክልከላ የሚያደርግ ህግ እየተረቀቀ እንደሆነ በቢሮው ሃላፊዎች ተገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment