Tuesday, January 21, 2014

ሰለ ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ በጥቂቱ …….


ከጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ጋር የቅርብ ትውውቅ እና አባታዊ ወዳጅነት ያላቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “አገቱኒ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ክፉ ቀንን በተመለከተ እልህ እና ስሜታዊነት የተቀላቀለበት አጠር ያለ ትንተና አስፍረዋል፡፡ ከዚህ ፅሁፋቸው አንድ አረፍተ-ነገር መጥቀስ ብችንል “ክፉ ቀን ጥሩ ነው ጀግና ያፈራል” የሚል ጽሁፍ አለበት፡፡ ጭቆና በበረታበት በዚህ በእኛ ጊዜ፣ በዚህ ክፉ ቀን፣ እውነትም አንድ ጀግና ተፈጥራለች፡፡Reeyot-Alemu
ይህ ክፉ ቀን ያፈራት እውነተኛዋ ጀግና ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ነች! ርዕዮት አለሙ በቃልቲ እስር ቤት ሶስት ዓመት ልትደፍን ጥቂት ጊዜያት የቀሯት ሲሆን በዚህም ረጅም የእስር ቆይታዋ በርካታ ፈታኝ ወቅቶችን አሳልፋለች አሁንም እያሳለፈች ትገኛለች፡፡
ያለ ፍትሃዊ ፍርድ ወደ ወህኒ መወርወሯ ሳያንስ በወህኒ ቤት የሚደረግላት አያያዝ እጅግ መድሎ እና መገለል የበዛበት እንዲሁም እንደ አንድ እስረኛ መብቶቿ የማይከበሩበት ሁኔታ ላይ ነው ያለቸው፡፡
ርዕዮት ከሌሎች እስረኞች በተለየ መልኩ ከእናት እና አባቷ ውጭ በማንኛውም የቤተሰብ አባል ሆነ እጮኛዋ እንዲሁም በሌላ ሰው እንዳትጎበኝ ተከልክላለች፡፡ርዕዮት አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ የጡት ላይ ህመም ያለባት ቢሆንም እና ይህንንም በማስመልከት በግሏም ሆነ በቤተሰቦቿ አማካኝነት የህክምና ክትትል እንድታገኝ ለማረሚያ ቤቱ ጥያቄ ብታቀርብም አስፈላጊውን ህክምና እንዳታገኝ ያለህግ አግባብ ተከልክላለች፡፡
ርዕዮት በእስር ቤቱ ለአስተዳደሩ ሰራተኞች ቅርብ በሆኑ እስረኞች ከፍተኛ ዛቻ እና መገለል ይደርስባታል፡፡ በርዕዮት አለሙ ላይ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ግን ህገመንግስቱ የሰጣትን የመናገር እና የመጻፍ እንዲሁም ባጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነቷን ተጠቅማ ስለእኩልነት፣ ስለፍትህ፣ ስለመልካም አስተዳደር፣ ስለሰብዓዊ መብት እና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በመጻፏ ብቻ ነው፡፡ ሃሳቧን በነጻነት በመግለጿ ምክንያት ርዕዮት አለሙ አሸባሪ ተብላ ተፈርጃለች፡፡
የሰው ልጅ መጎዳት ከምንም በበለጠ የሚያስከፋት ባለ ሩህሩህ ልቧ ይህቺ ወጣት አሸባሪ ተብላ በመጀመሪያ 14 ዓመት ተፈርዶባት የነበረ ሲሆን ምንም እንኳ የሃገሪቱ የፍትህ ስርዓት ነጻነት ጉዳይ አጠያያቂ ላይ የወደቀ መሆኑን ብታውቀውም ይግባኝ በማለት ፍርድቤቱን የሞገተች እና ፍርዱን ወደ አምስት አመት ማስቀነስ የቻለች ናት፡፡ ለርዕዮት አለሙ የአምስት አመት የእስር ፍርድም ፈጽሞ የማይገባ ቢሆንም ይህን ይግባኝ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቅርባ ይግባኝ ያለ በቂ ምክንያት ውድቅ ተደርጎባታል፡፡
ርዕዮት አለሙ ያላት ውስጣዊ ጥንካሬ እና ስብዕና እውነተኛ ጀግና መሆኗን ያስመሰክራል፡፡ በቼንጅ መጽሄት እና በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ በአምደኝነት እንዲሁም በአዲስ ፕሬስ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት የጋዜጠኝነት ስራ ስትሰራ የቆየች ሲሆን እስከታሰረችበት ጊዜ ድረስ ደግሞ በፍትህ ጋዜጣ ቋሚ አምደኛ ሆና በርካታ ጽሁፎችን ጽፋለች፡፡
በተጨማሪም በ96.1 ኤፍ ኤም ራዲዮ ላይ ከጓደኛ ሽለሲ ጋር በመሆን በሀገሪቷ የትያትርና ስነጥበብ እድገት እና ተግዳሮቶች ዙርያ ሳምንታዊ ፕሮግራም ታዘጋጅ ነበር፡፡
ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ሁለገብ ጸሃፊ ስትሆን ከኪነጥበብ ጉዳዮች ጀምሮ ፓለቲካዊ ነክ ጉዳዮች ላይ መልካም አስተዳደርን በተመለከተ፣ ስለእኩልነት፣ ስለ ፍትህ፣ ስለ ዴሞክራሲ እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችም ዙሪያ በርካታ ጽሁፍ አቅርባለች፡፡ ርዕዮት ጽሁፎቿ ቅንነት የሚታይባቸው ሲሆን ለእውነት፣ ለሰው ልጅ እኩልነት፣ እንዲሁም ለሃገር አንድነት ያላትን ብርቱ አቋም በጽሁፏ ታንጸባርቃለች፡፡
የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ስራዎች በአጠቃላይ ተሰብስበው የኢህአዴግ ቀይ እስክርቢቶ በሚል እርዕስ በመጽሐፍ መልክ የታተሙ ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት እየተነበበ ይገኛል፡፡ ርዕዮት ከጋዜጠኝነት ስራዋ በተጨማሪ ትጉህ መምህር ስትሆን በተማሪዎቿም ሆነ በስራ ባልደረቦቿ ዘንድ የተከበረች ባለሙያ ነች፡፡ከስራዋ ጎን ለጎን ትምህርቷን በመቀጠል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአንድ ጊዜ ሁለት ዲግሪ በውጭ ቋንቋዎች እና በትያትር ሰነጥበብ ትምህት ተመረቃለች፡፡
ለወትሮው ዘወትር ጥር 13 ቀን በወዳጅ ዘመዶቿ ተከባ ልደቷን በደመቀ ሁኔታ ታከብር የነበረችው ርዕዮት አለሙ ያለፉት ሁለት አመታት ልደቷ የተከበረው በቃልቲ እስር ቤት ደጃፍ ነው፡፡ ቤተሰቦቿ፣ የሙያ አጋሮቿ እና ጓደኞቿ በተገኙበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በቃልቲ እስር ቤት ደጃፍ ልደቷ ሲከበር ርዕዮት አለሙ ምንም የመከፋትም ሆነ የሃዝን ምልክት ሳይሆን የታየበት እንዲያውም ከሌላው ጊዜ በበለጠ ደስተኛ እና ፍልቅልቅ ሆና ነው ያከበረቸው፡፡ የአሁኑ የርዕዮት አለሙ ልደት በቃልቲ እስር ቤት ደጃፍ ብቻ ሳይሆን የሚከበረው በተለያዩ ቦታዎች እና ሃገሮች የጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተሰባሰቡበት በክብር እና በደመቀ ሁኔታ ነው፡፡
የርዕዮት አለሙን የልደት በዓል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለማክበር ቀደም ብለው በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች እና ሌሎች ዌብ ሳይቶች እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ለዚህም በመላው አለም የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አወንታዊ ምላሻቸውን እና ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ለርዕዮት አለሙ ልደቷ በመላው አለም ዙሪያ መከበሩ የሚገባት እንጅ የሚያንሳት አይደለም፡፡
ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ስለ እኩልነት፣ ስለመልካም አስተዳደር እና ስለ ፍትህ በመጻፏ እና መንግስትን አጥብቃ በመሞገቷ ያለ ሰሟ ስም ተሰጥቷት አሸባሪ ተብላ ያለ አግባብ ፍርድ አምስት አመት ተፈርዶባት በቃልቲ እስር ቤት መስዕዋትነት እየከፈለች ትገኛለች እና! ምንም እንኳ በእስር ላይ የምትገኝ ቢሆንም እና አሁን ያለችበት ሁኔታ አስከፊ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም ለርዮት አለሙ የልደት ቀኗ ነው እና እንኳን አደረሰሽ ለማለት እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment