Sunday, January 19, 2014

ዶ/ር ነጋሶ አንድነት ፓርቲ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ስላልተመቻቸው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ምላሽ ባለማግኘታቸው ከፖለቲካው ዓለም ለመሰናበት ወሰኑ ::



‹‹የሕዝብ መብት ከሚቃወም የፖለቲካ ድርጅት ጋር መሥራት አስቸጋሪ ነው›› ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
‹‹የአንድነትን አቋም ሳያውቁ የፓርቲው አባል ሆነዋል ለማለት ያስቸግራል›› m አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ

ላለፉት ሁለት ዓመታት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበር የነበሩትና ለ45 ዓመታት በፖለቲካ ውስጥ እንደቆዩ የሚናገሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ከጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም.
ጀምሮ ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካው ዓለም ለመሰናበት የወሰኑት አንድነት ፓርቲ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ስላልተመቻቸው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ምላሽ ባለማግኘታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ እንደገለጹት፣ መድረክ ግንባር ከመሆኑ አስቀድሞ ባነሳቸው ሐሳቦች ላይ ሁሉም ድርጅቶች ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ ከተወያዩባቸው በኋላ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ መስማማታቸውንም ለመድረክ በመግለጽ መድረክ ወደ ግንባር መሸጋገሩን አስታውሰዋል፡፡

በሚያዝያ ወር 2005 ዓ.ም. በአንድነት ፓርቲና በእሳቸው የአመለካከት፣ የአቋምና የአቅጣጫ ልዩነት መፈጠሩን የገለጹት ዶ/ር ነጋሶ፣ አንድነት ፓርቲ መድረክ ወደ ግንባር የተቀየረው በጠቅላላ ጉባዔውና በብሔራዊ ምክር ቤቱ እምነትና ውሳኔ ሳይሆን በአመራሮች መሆኑን በመጥቀስ፣ እንደማይስማማ በዚያን ወቅት ባደረገው ግምግማ ላይ በመግለጹ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መድረክ ወደ ግንባር ከመቀየሩ አስቀድሞ ይፋ ባደረገው ፕሮግራም ላይ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተወያይተውና ተመካክረው በሕገ መንግሥት ጉዳይ፣ በቤት ጥያቄና በሌሎችም በተነሱ ነጥቦች ላይ መስማማታቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሶ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ ብቻ ልዩነት እንዳለው አንድነት ገልጾ የሽግግር ሒደቱ በሰላም መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡

ሽግግሩ ወራትን ካስቆጠረ በኋላ በሕገወጥ መንገድ እንደተደረገ በማስመሰል ወደኋላ መመለስ አሳፋሪ ድርጊት ከመሆኑም በተጨማሪ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤትና የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት፣ ፓርቲው የማይስማማበትን ነጥብ ይዞ ወደ መድረክ በመሄድ መወያየት ሲገባቸው፣ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠታቸው ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የነበሩትን የተሳሳቱ ሒደቶች በመጥቀስ እርማት እንዲደረግ ዶ/ር ነጋሶ ለአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ቢሆንም፣ ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ዶ/ር ነጋሶ የሚያነሱት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ላይ የተጠቀሰውን ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን እስከ መገንጠል›› የሚለውን የሕዝቦች የመብት ጥያቄ አንድነት ውድቅ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን ሲሆን፣ ‹‹የሕዝብን መብት ከሚቃወም የፖለቲካ ድርጅት ጋር መሥራት አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አንድነት የመድረክን ወደ ግንባር መቀየር የማይቀበለው ‹‹የውህደት›› ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መመሥረት እንዳለበት ስለሚፈልግ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሶ፣ በሕጋዊና በትክክለኛ መንገድ ስምምነት የተፈጸመበትን ‹‹ግንባር›› ‹‹ውህደት›› ካልሆነ ማለት የማይሆንና የማያስኬድ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ያልተስማሙባቸውን ነጥቦችና ስምምነት ከተደረገ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አግባብ አለመሆኑን በመጠቆም ላቀረቧቸው ጥያቄዎች የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ምላሽ በመንፈጉ ምክንያት፣ ዶ/ር ነጋሶ ከፖለቲካው ዓለም መሰናበታቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ ቀደም ብሎም ከፖለቲካ ሥራና ተሳትፎ ለመልቀቅ በማኮብኮብ ላይ እንደነበሩ አልሸሸጉም፡፡

ምክንያታቸውንም ሲገልጹ ነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም 70 ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡ ከዕድሜያቸው ከግማሽ በላይ ለ45 ዓመታት በፖለቲካ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብን የፖለቲካ ባህል ሲያስታውሱ፣ በኦሮሞ ገዳ ዲሞክራሲ አንድ መሪ ዕድሜው 48 ሲሆነው የአመራር ሥልጣኑን ለወጣቱ መልቀቅ እንዳለበት የሚገልጸውን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ማሰባቸውን አብራርተዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ዓለም ራሳቸውን ማግለላቸውን ከዚህ በኋላ በማንኛውም መንገድ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በአባልነትም ሆነ በመአራርነት እንደማይሳተፉ ያረጋገጡት ዶ/ር ነጋሶ፣ ‹‹ጆሮዬ ለፖለቲካ ክፍት ይሆናል፤ የማስበውን በጽሑፍና በአፌ እናገራለሁ፤ አንድነትንም ሆነ ሌሎችንም በመዋቅራዊ መልክ ሳይሆን እደግፋለሁ፤ ሲያስፈልግ እተቻለሁ፤ ሲያስፈልግ እቃወማለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ ለዶ/ር ነጋሶ ከፖለቲካ መገለል ምክንያት ስለመሆኑ ለተነሳለት ጥያቄ በሕዝብ ግንኙነት አማካይነት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ፓርቲው በቅርቡ አዲስ አመራር መምረጡንና ቀደም ሲል በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሥልጣን ሽግግሩን ፈጽመው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አቅርበው ሽግግሩን ማፅደቃቸውን የገለጹት የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ናቸው፡፡

ለብሔራዊ ምክር ቤቱ የአዲሱን አመራር ቀጣይ የሥራ የሽግግር ጊዜ ሲያቀርቡ፣ ከዕድሜያቸው ጋር በተገናኘ ለቤተሰቦቻቸው ራሳቸውን ከፖለቲካ እንደሚያገሉ ቃል መግባታቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ በመድረክ ላይ ያላቸውን አቋምም ግልጽ ማድረጋቸውን አክለዋል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ አንድነት መድረክን መገምገሙና ማጥናቱ ትክክልና ተገቢም ነው፡፡ የግንባሩ አባል የሆነ ድርጅት ፖለቲካውን አግባብ ባለው መንገድ እየመራ ነው? አይደለም? የሚለውን ጥናት ማድረግ ተገቢ ነው ካሉ በኋላ፣ መድረክ አሁን ባለው ሁኔታ የሚታየውን ነገር ሁሉ ማሻሻያ በማድረግ ሊቀጥል ይገባል የሚል አቋም እንዳላቸው መናገራቸውን አቶ ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ መድረክ ወደ ውህደት በማደግ አንድ ግዙፍ ብሔራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር ያቀረበውን ሐሳብ በቀላሉ ሊሳካ የሚችል ባለመሆኑ፣ ሐሳቡን እንደማይደግፉም ዶ/ር ነጋሶ ማሳወቃቸውን አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ያነሱትን የልዩነትና የድጋፍ ሐሳብ አንድነት ፓርቲ እንደሚያከብር የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ፓርቲው ግን ግልጽ የሆኑ የፖለቲካ አማራጮች እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግልን ወደፊት ለመግፋት ብሔራዊ ምክር ቤቱና ጠቅላላ ጉባዔው አስቀድሞ ባዘጋጁዋቸውና በሚያሻሽሉዋቸው ነጥቦች ትግሉን እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

አንቀጽ 39ን በሚመለከት አንድነት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ የሚያነሳቸውን ነጥቦች ፍፁም በሆነ ሁኔታ እንደሚያከብር የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ ዶ/ር ነጋሶ የአንድነት ፓርቲን አቋም በግልጽ ሳያውቁ የፓርቲው አባል ሆነዋል ለማለት እንደሚያስቸግር አክለዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ ከአንቀጽ 39 የማይቀበለው በመጨረሻው ንዑስ አንቀጽ ላይ የተቀመጠውን ‹‹እስከ መገንጠል›› የሚለውን ሐረግ መሆኑን ይህንንም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የተቃጣ አደጋ በመሆኑ፣ መቼም ቢሆን የአገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማንም ለድርድር እንደማያቀርብ በግልጽ ሊታወቅ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ላለፉት 45 ዓመታት በቆዩበት የፖለቲካ ሕይወታቸው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል፣ እንዲሁም የኢሕአዴግ አባል የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አመራር እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ከመለያየታቸው በፊት ለስድስት ዓመታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ከቀድሞ የአገር መከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ ጋር በመሆን የአንድነት ፓርቲ አባል ከመሆናቸውም በላይ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፓርቲው አመራር አባልና ሊቀመንበር መሆን ችለው ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment