Tuesday, January 28, 2014

በሽብርተኝነት ህጉ ውይይት ስም የአዲስ አበባ ህዝብ እየተሸበረ ነው ሲሉ አንዳንድ ተወያዮች ገለጹ



ጥር ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በአዲስ አበባ ውስጥ ለሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞችና በተዋረድም ከህዝቡ ጋር እተደረገ ባለው የሽብርተኝነት ህግ ውይይት፣ ነዋሪዎች ጥላቸውን እንኳን ማመን እንደሌለባቸው በአሰልጣኞች እየተነገራቸው ሲሆን፣ በስልጠናው ላይ የተካፈሉ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች፣ ስለሽብረተኝነት ልንማር ሂደን ተሸብረን መጣን ሲሉ ተናግረዋል።

በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀው የማሰልጠኛ ሰነድ ኢሳት እጅ የገባ ሲሆን፣ ሰነዱ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ቆሞ ልማቱን እንዲጠብቅና እንዲያፋጥን ይጠይቃል። በመስተዳድሩ የሚገኙ የቢሮ ሃላፊዎች፣ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር በሆኑት በአቶ ተወልደ ወ/ጻዲቅ መሪነት በሰነዱ ላይ ውይይት አድርገውበታል ። በሰነዱ ላይ የመስተዳድሩ የየደረጃው አመራሮችና ሲቪል ሰራተኞች እንዲሁም የከተማው ህዝብ እየተወያዩበት ነው።

እስካሁን ባተካሄደው ውይይት እንደታየው የመንግስት ሰራተኞች በስልጠናው ላይ የሚገኙት የስም ምዝገባ ስላለ እንጅ በዝግጀቱ አምነውበት አይደለም ይላሉ ተሳታፊዎች።

በውይይቶች ወቅት የመንግስት ባለስልጣኖች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ከህዝቡ ስለሚጠበቀው ግዴታ መሆኑን የሚናገሩት ተሳታፊዎች ፣ የአገሪቷን ደህንነት ፖሊስና የደህንነት ሃይሉ ጠብቆ ስለማይችል፣ ህዝቡ ከኮሚኒቲ ፖሊስ ጋር በመተባበር ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት ባለስልጣኖች ማሳሰቢያ መስጠታቸውን ተሰታፊዎች ይገልጻሉ።

የፌደራል ፖሊስ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ወንጀለኛን ለመለየት የአፍና የጸጉር ምርመራ ሊያደርግ እንደሚችል፣ ምርምራው እንዲደረግበት የተጠረጠረ ሰው ፈቃደኛ ካልሆነ ተመጣጣኝ ሃይል በፖሊስ ሊወሰድበት እንደሚችል፣ በማንኛውም ጊዜ በድነገት በከተማ ባስና በታክሲ ላይ ፍተሻ ሊደረግ ስለሚችል ህዝቡ መተባበር እንዳለበት የመንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የመንግስት ሰራተኞች ቦርሳ፣ፌስታልና መሰል ቁሳቁሶችን ቢሮ ውስጥ ጥለው እንዳይሄዱ የተነገራቸው ሲሆን ፣ ቢሮ ውሰጥ የተገኙ ፌስታሎችና ቦርሳዎች ለአደጋ ከማጋለጣቸው በፊት በጥንቃቄ እንዲታዩ ምክር ተሰጥቷል።

ለማወያያነት በቀረበው ሰነድ ላይ በግልጽ እንደሚታየው “ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ በሽብርተኝነት የተጠረጠረን ሰው የስልክ፣ የሬዲዮ፣ የኢንተርኔት የኤሌክትሮኒክስ፣ የፋክስ፣ የፖስታ ግንኙነት እና የመሳሰሉ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል፣ ጠለፋውን ለማስፈፀም ወደ ማንኛውም ቤት በሚስጢር የመግባት ወይም ይህንኑ ለመፈጸም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ ወይም ለማንሳት የፌደራል ፖሊስ ስልጣን ተሰጥቶታል።

እንዲሁም “ ማስረጃ ከሚሰበሰብባቸው የተለያዩ ዘዴዎች መካከል አንዱ በሽብርተኝነት ወንጀል ከተጠረጠረው ሠው ላይ ናሙናዎችን መውሰድ እና የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ ማድረግ በመሆኑ ፣ ተጠርጣሪውም በምርመራ ሂደት ናሙናውን ለመስጠት ወይም የህክምና ምርመራ ለማድረግ ፍቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ ተመጣጣኝ ኃይል ተጠቅሞ ናሙናውን የመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ሰነዱ “ የሀይማኖት አክራሪነትና አሸባሪነት ዋናው ምንጭ ድህነትና ተስፋ መቁረጥ ” መሆኑን ከገለጸ በሁዋላ ፣ ”ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ በመንግስት የወጡ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና እቅዶች ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ሰፊ ርብርብ ማድረግ” ከህብረተሰቡ እንደሚጠበቅ ይገልጻል።

ኢሳት አስተያታቸውን የጠየቃቸው ሰልጣኞች እንዳሉት ውይይቱ ህዝቡን የበለጠ የሚያሽብር ቢሆንም መንግስትም ሽብር ውስጥ መግባቱን ያመለክታል።

በሰነዱ ላይ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት7፣ አልሸባብና አልቃይዳ አሸባሪ ድርጅቶች ተብለዋል

No comments:

Post a Comment