Thursday, January 23, 2014

በርካታ የየረር ባሬ ጎሳ አባላት ታሰሩ



ጥር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶማሊ ክልል በቀላፎ አካባቢ የሚኖሩ የየረር ባሬ ጎሳ የአገር ሽማግሌዎች ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያስገቡት ደብዳቤ ለኢሳት መድረሱን ተከትሎ የክልሉ ባለስልጣናት ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ በርካታ የአገር ሽማግሌዎችን ማሰራቸው ተሰማ።

የአገር ሽምግሌዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሀመድ ኡመር እና ጄኔራል አብርሀም በቅጽል ስማቸው ኳታር የሚመራው ልዩ ሚሊሺያ እየተባለ የሚጠራው ሀይል ታህሳስ 1 እና 2 በከፈተው ተኩስ በትምህርት ላይ የነበሩ ህጻናትንና ወጣቶችን ጨምሮ 47 ሰዎችን መግደሉን የሟቾቹን ስም ዝርዝር በመጥቀስ ገልጸው ነበር።

ልዩ ሚሊሺያው ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንዳሉ ተኩስ መክፈቱን የአገር ሽማግሌዎቹ በደብዳቤያቸው ላይ የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ደርሶ እንዲታደጋቸውም ጠይቀዋል።

የየረር ባሬ ጎሳ አባላት የክልሉ መንግስት እንደ ተወላጅ ባለመቁጠር ጭቆና እንደሚያደረስባቸው በመግለጽ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ መንግስት ልዩ ሚሊሺያዎችና በየረር ባሬ ጎሳ አባላት መካከል ተደጋጋሚ ግጭት ሲደረግ ከቆየ በሁዋላ ሰሞኑን መሳሪያ ለማስፈታት ወደ አካባቢው የተጓዘው የክልሉ ልዩ ሚሊሺያ ሃይል ካፍ እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ላይ በከፈተው ተኩስ ህጻናትንና ሴቶችን ጨምሮ 47 ሰዎች መገደላቸውን የአገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል። ጥር 11 በተቀሰቀሰው ግጭት ከቆሰሉት ከ100 በላይ ሰዎች 17 ሰዎች በህክምና እጦት መሞታቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የብሄረሰቡ ተወካይ ለኢሳት ገልጸዋል።

ዜናው በኢሳት መተላለፉን ተከትሎ የሚሊሺያ ሃይሉ በትናንትናው እለት 16 የአገር ሽማግሌዎችን ይዞ ማሰሩንም ተወካዩ ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሰካልንም።

No comments:

Post a Comment