Sunday, January 19, 2014

በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያንና ሙስሊሙ ይጋጫል ብለው አስበው ያውቃሉ? እኛ ወንድማማቾች ነን! ወሬኛውን አላህ ያጥፋው አቦ! ይሄ ነጃሳ!

By Afendi Muteki


የገለምሶው መምሬ ሙላቱ ሲታወሱ
ከአፈንዲ ሙተቂ
-------------
በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያንና ሙስሊሙ ይጋጫል ብለው አስበው ያውቃሉ? መቼም እንዲህ እንደማያስቡ ይታወቀኛል። እኔም 
እንዲህ ያስባሉ ከሚል መነሻ አይደለም ጥያቄዬን የሰነዘርኩት። አነሳሴ በተወለድኩበት አካባቢ በሚኖሩት ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል ወንድማዊ ፍቅር እንዲጎለብት ጥረት ሲያደርጉ ስለነበሩት አንድ ታላቅ ካህን ያለኝን ትዝታ በመጠኑ ላካፍላችሁ ነው።

መምሬ ሙላቱ መታፈሪያ ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በአሁኑ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ገለምሶ ከተማ ነው። መምሬ ሙላቱ የከተማዋ ቀደምት ቤተክርስቲያን የሆነው የገለምሶ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ሰባኪ ነበሩ። ታዲያ መምሬ የቅስናውን ተግባር ለነፍሳቸው ብቻ ነበር የያዙት። ለቤተክርስቲያኒቱ በሚሰጡት አገልግሎት ደመወዝ አይቀበሉም። እርሳቸው የሚተዳደሩት ከቡና ንግድ በሚያገኙት ገቢ ነው። ዘወትር የማይረሳኝ አንዱ ትዝታዬም ከዚሁ የቡና ንግድ ጋር የተያያዘ ነው።

በዘመኑ በከተማችን በነበሩት የቡና ነጋዴዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ይካሄድ ነበር። ነጋዴዎቹ ቡና በብዛት የሚገዙትም የከተማዋ ዋነኛ የገበያ ቀን በሆነው ዕለተ ማክሰኞ ነው። አንድ ነጋዴ በዚህ ቀን ብቻ ከመቶ ኩንታል በላይ ቡና ሊገዛ ይችላል። ሆኖም ነጋዴው ለገበያ የሚወጣው ብቻውን አይደለም። ወደ ከተማው የሚመጡትን አህዮች ከገበሬው እጅ እየጠለፉ የሚያመጡለት ደላሎች ያስፈልጉታል። እነዚያ የቡና ደላሎች “ቀቀቢ” ይባላሉ። አንድ ነጋዴ ከእኩዮቹ የበለጠ ቡና ለመግዛት ከፈለገ ቢያንስ ከአራት ያላነሱ ቀቀቢዎች ያስፈልጉታል። መምሬ ሙላቱ ግን “ቀቀቢ” የላቸውም። ረፋዱ ላይ ብቻቸውን ከትንሽ ሴት ልጃው ጋር ይሰማራሉ። ተሲያት ላይ ከሁሉም ነጋዴ የበለጠ ቡና ይገዙና ወደ መጋዘናቸው ያስጭናሉ። ከዚህ የጥቂት ሰዓታት ግብይት በኋላም ወደ ቤተክርስቲያናቸው ይመለሳሉ። ይህ ነገር ብዙ ሰዎችን ያስደንቅ ነበር። እኔም በልጅ አዕምሮዬ በጣም እደነቅበት ነበር። “እንዲህ በጦፈው ፉክክር ውስጥ እኚህ ሽማግሌ አንድም ቀቀቢ ሳያሰማሩ በትንሽ ሰዓታት ውስጥ ይህንን ሁሉ ቡና የሚገዙበት ሚስጢር ምንድነው? ምናልባት ድግምት ይሆን?” እያልኩ አሰላስል ነበር።

ነገሩ የገባኝ የሀይስኩል ተማሪ ከሆንኩ በኋላ ነው። የኛ ሀይስኩል በከተማው ደቡብ ምስራቃዊ ጠረፍ ላይ ነው የነበረው (አሁን ከተማው በማደጉ ወደ መሀል ገብቷል እንጂ )። ታዲያ በዚህ ሀይስኩል አጠገብ የሚያልፍ አንደ ሰፊ ጎዳና “ዌኔ” ከሚባለው የገጠር ቀበሌ ያደርሳል። ማክሰኞ ቡና በብዛት ወደ ገለምሶ የሚገባበት አንዱ በርም ይሄ የዌኔ መንገድ ነው። እናም በአንዱ ቀን ከትምህርት ቤታችን ለእረፍት ወደ መንገዱ ወጥተን ሳለ በርካታ ገበሬዎች ቡና በአህያ ጭነው ሲመጡ ተመለከትኩ። ገበሬዎቹ በየመንገዱ ዳር የቆሙትን የቡና ቀቀቢዎች “ወግድ ወደዚያ” እያሉ ያልፉአቸዋል። ቀቀቢዎቹ “በጥሩ ዋጋ ነው የምንገዛው እኮ” እያሉ ሲያባብሉአቸው ደግሞ “ማምሬ መሌ ሂንጉርጉሩ” (“እኛ ቡናችንን ለመምሬ እንጂ ለሌላ አንሸጥም”) የሚል መልስ ይሰጣሉ። እኔና ጓደኞቼ በዚህ ነገር ተገረምንና ገበሬዎቹ ምክንያቱን እንዲነግሩን ጠየቅናቸው። እነርሱም እንዲህ አሉን።

“አሁን እዚህ ወጥተው የሚታዩት ቀቀቢዎች ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም ሌቦች ናቸው። ከዚህ እያባበሉ ይወስዱንና የቡናው ሚዛን የተቀመጠበት ቦታ ስንደርስ ጉድ ይሰሩናል። እዚህ መቶ ኪሎ የሆነው ቡና እዚያ ሲሄድ አስር ኪሎ ይጎድላል። በዚያ ላይ የቀረውን ሂሳብ እንኳ መች አሟልተው ይሰጡናል? እነርሱ ፊት ሲቆጠር ሁለት መቶ የነበረው ብር ኪሳችን ከገባ በኋላ እቃ ልንገዛ ስናወጣው ሰላሳ ወይም ሀምሳ ብር ጎድሎበት እናገኛዋለን። ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ቡናችንን ተቀብለው “ሂሳቡን በኋላ ውሰድ” በማለት ካሰናበቱን በኋላ ማታ ላይ ስንመለስ ዋጋውን እጅግ አውርደው “ይህችን ታህል ተቀበል! ወይ ቡናህን ውሰድ!” እያሉ ያጉላሉናል። መምሬ ሙላቱ ግን እንዲህ ዓይነት ነጃሳ ሰው አይደሉም። ኪሎ ማምታታት፣ ሂሳብ ማጉደል፣ ቡናህን ውሰድ እያሉ በሰው ማላገጥ እሳቸው ዘንድ የለም። ቡናችንን ተረክበው ሙሉ ሂሳባችንን በስነ ስርዓቱ ቆጥረው ይሰጡናል። ለዚህም ነው ለርሳቸው ብቻ የምንሸጠው።”

ከህጻንነቴ ጀምሮ ማወቅ የቸገረኝ የመምሬ ሙላቱ ብዙ ኩንታል ቡና የመግዛት ሚስጢር በዚህ መንገድ ተፈታልኝ። ታዲያ በአንድ ወቅት የመምሬ ሙላቱ ጎረቤት የነበረው አባቴ “መምሬ ሙላቱ ገበሬው ከሚያውቀው ውጭ ትርፍ ኪሎ ከተገኘም ሂሳቡን ጨምሮ ነው የሚሰጣቸው፤ አንድ ግራም የሰው ንብረት ወደርሱ እንድታልፍ አይፈልግም” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቶኛል።

ነገሩን አያችሁት አይደል? መምሬ ሙላቱ የክርስቲያን ቄስ ሆነው ከሙስሊሙ የሀረርጌ ገበሬ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እጅግ ብዙ ቡና የሚገዙት በምትሃት አልነበረም። ገበሬው ላቡን አንጠፍጥፎ ያመረተውን ምርት ከሀቅ ውጪ ለማግበስበስ ስላልፈለጉ ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ሀቀኛነት ፍቅርን ያመጣል። ፍቅር ካለ ወንድማማችነት ይጠነክራል። ብራቮ መምሬ! ብራቮ የሀረርጌ ገበሬ! “ማምሬ መሌ ሂንጉርጉሩ! ማምሬ መሌ ሂንጉርጉሩ!”
***** ***** *****
በልጅነቴ በገለምሶ ከተማ መውሊድ ሲከበር ክርስቲያኑ መጥቶ ስርዓቱን ያያል፤ የጥምቀት በዓል ሲከበርም እኛ ሙስሊሞቹ ሄደን እናያለን። እናም ቀጥዬ የማወጋችሁን ነገር የሰማሁት የጥምቀት በዓል ከሚከበርበት ቦታ ሄጄ ሳለ ነው።

ቀሳውስቱ በተሰበሰበው ህዝብ መሀል ቆመው ቡራኬ ይሰጣሉ። ወጣት መዘምራንም በዜማ ያሸበሽባሉ። መዘምራኑ ለእረፍት መድረኩን ሲለቁ ደግሞ መምሬ ሙላቱ ለሰበካ ወደ መድረኩ ወጡ። እና አሁን የማላስታውሰው ብዙ ትምህርት ለክርስቲያኑ ህዝባቸው ከሰጡ በኋላ እንዲህ አሉ

“እኛ ክርስቲያኖች ተዳክመናል፤ ለደካማ ወገኖቻችን እጃችንን መዘርጋት እንሰስታለን፣ ድሃን መመጽወት እየረሳን ነው። እስቲ እስላሞችን ተመልከቱ። “ዘካ” ብለው አስራት ይሰጣሉ፤ “ሰደቃ” እያሉ ይመጸውታሉ። እነርሱ ወንድሞቻችን ናቸው፤ እኛስ ከነርሱ ለምን ትምህርት አንወስድም? ለምን ስስት እናበዛለን”።

መምሬ እንዲህ ብለው የሚያስተምሩ ሰው ናቸው። ገለምሶ እንደዚህ ዓይነት ሀቅና ፍቅርን የሚያስተምር ካህን ነበራት። እኔ ስለሙስሊሙና ክርስቲያኑ አብሮ መኖር ሲነገር ዘወትር የሚታወሱኝ እርሳቸው ናቸው። ታዲያ እነ መምሬ ሙላቱ በኖሩበት ሀገር ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ጦር ይማዘዛል? ሙስሊም ክርስቲያኑን አርዳለሁ ብሎ ይነሳል? ክርስቲያኑስ ሙስሊሙን ላጥፋ ብሎ ይሰለፋል? በፍጹም! እንዲህ ብሎ የሚያወራ ካለ እርሱ በርግጥ ሸይጣን የነገሰበት ወሬኛ ነው።
እኛ ወንድማማቾች ነን! ወሬኛውን አላህ ያጥፋው አቦ! ይሄ ነጃሳ!
***** ***** *****
መጋቢት 12/ 2005 ዓ.ል.

No comments:

Post a Comment