Tuesday, January 21, 2014

በርካታ ሙስሊሞች “ሕዝብን ለሽብር ቀስቅሻለሁ” ብላችሁ እመኑ በሚል በእስር ቤት እየተገረፉ መሆኑ ተዘገበ


ህወሐት መራሹ የኢትዮጽያ መንግስት ሕዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው ሲል ቢቢኤን ራድዮ ዘገበ። እንደ ራድዮው ዘገባ ከኢዱ ጅምላ ጭፍጨፋ ቡኋላ መንግስት ልዩ ግብረ ኃይል በማቋቋም በአ/አበባ በወልቂጤ እንዲሁም በአዳማ ከተማዎች ላይ የሚገኙ መስጂድ የሚያዘወትሩ ወጣቶችን ከየቦታው አፍኖ በመውሰድ በአገራችን ጏንታናሞ ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ “ሕዝብን ለሽብር ቀስቅሻለሁ” ብላችሁ እመኑ እየተባሉ ቀን ከሌት የስቃይ አይነት ሲያስቆጥራችው ከርሞ ጥር 7 2006 ቁጥራቸው 16 የሚደርሱ ወጣቶችን የወያኔ ፋሽን የሆነውን የሽብርተኝነት ክስ መስርቶ ወደ ቂሊንጦ (ሒጅራ ኮምፓውንድ ) አዛውሯቸዋል::




(ፎቶ ፋይል )

ራድዮው ዘገባውን ቀጥሎ ”አሁንም የስቃይ መአት እየተቀበሉ ያሉ ወንድሞች ደግሞ ዛሬም እዛው ማእከላዊ ይገኛሉ፤ ምንም በማያውቁት ወንጀል የተከሰሱ ወንድሞቻቸው ላይ በግድ እንዲህ ሲያደርጉ ነበር ብላችሁ መስክሩ ተብለው ነው የሚሰቃዩት” ካለ በኋላ በስቃይ ላይ ያሉትን ስም ይጠቅሳል።

1ኛ አብዱላሂ ከሊል፣ ከጀርመን መስጂድ የተያዘ፤
2ኛ. መስፍን ገብሬ (ሀቢብ) ከቄራ መስጂድ
3ኛ. ኡመር ሹክረላህ ከኮልፌ አካባቢ
4ኛ ሙጅብ አሚኖ ናቸው።

“ማንኛውም በሕግ ጥላ ስር የሚገኝ ዜጋ ከሕጋዊ ጠበቃውና ከቤተሰቡ ጋር መገናኘ ትእንደሚችል ወረቀት ላይ ብቻ የቀረው ህገ መንግስት ቢገልፅም መንግስትም ሁሌም በህግ ስም ሲምል ሲገስፅ ቢውል ቢያድርም ለነዚህ እና ለብዙ ዜጎች ሹፈት ሆኖባቸዋል ጠበቃ እንዳያገኛቸው “ጠበቃ አያስፈልገንም “በሉ ተብለው ብቻ የሚደርስባቸው የስቃይ በትር ለአእምሮ ይከብዳል::” ያለው የቢቢኤን ዘገባ ከዚህ ሁሉ የከፋው እውነት ‘ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በባህሉ በሃይማኖቱ ተከብሮና የፈለገውን እምነትና አስተሳሰብ ማራመድ ይችላል’ የሚለውን የሕገ መንግስት ማእዘን ገደል የከተተው እርምጃ ወንድማችን መስፍን ገብሬ (ሀቢብ) ላይ የሚደርሰው ‘ለምን ሰለምክ?’ እየተባለ በማእከላዊ ገራፊዎች የሚደርስበት ስቃይ ነው” ብሏል። ራድዮው በመጨረሻም “ይህ ወንድማችን የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ከመስከረም10 ቀን ጀምሮ ማእከላዊ እየተሰቃየ ይገኛል፤ እነዚህን ወንድሞች ከጎናቸው ልንቆም ይገባል፤ እንዲሁም የሚደርስባቸውን ኢሰብአዊ ድርጊት ሁላችንም ለማጋለጥ እንነሳ” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።


 ዘ -ሐበሻ

No comments:

Post a Comment