Tuesday, January 28, 2014

አንድነት ህወሓት/ኢህአዴግ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሀሳብ እንዳያገኝ እያካሄደ ያለውን አፈና አጥብቆ እንደሚቃወም ገለጸ January 28/2014


(ዘ-ሐበሻ) አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫው “ህወሓት/ኢህአዴግ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሀሳብ እንዳያገኝ እያካሄደ ያለውን አፈና አጥብቀን እንቃወማለን” ሲል አወገዘ።

የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዴሞክራሲ ዕጦት ሰለባ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል ያለው አንድነት ስርዓቱ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል እንደሚያደርገው በትግራይም ሰብዓዊ መብት ይረግጣል፣ ፍትህ ይደፈጥጣል፣ በካድሬዎች ይደበደባል፣ ይንገላታል፣ እንዲሰደድ ይደረጋል፡፡ ስርዓቱና በስርዓቱ ውስጥ የደላቸው ሹማምንት በስሙ ከመነገድ በዘለለ ዋጋ የተከፈለበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዘርግቶ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም ሲል በመግለጫው ላይ አስቀምጧል።


     
        የመቀሌ ከተማ (ፋይል)

“ህወሓት/ኢህአደግ ክልሉን እንደዋና ካምፕ በማየት በአፈና ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ የትግራይ ህዝብ የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን እንዳያገኝ፤ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳያዳምጥ የተፈረደበት ሕዝብ ነው ማለት ማጋነን አይደለም፡፡ ይሄ እውነትም ሕወሓት/ኢህአዴግ በተለያየ ጊዜ በህዝቡ ላይ በፈፀማቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች የታየ ነው፡፡” የሚለው የአንድነት መግለጫ ” ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አምባገነኑ ህወሓት/ኢህአዴግ አረና ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ ሊያደርግ የነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ታፍኖበታል፣ አባላቱ ተደብድበዋል እንዲሁም ታስረዋል፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዳያገኝና በጉልበት የህወሓት አንጡራ ሀብት ብቻ ሁኖ እንዲያገለግል ከመፈለግ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ፓርቲያችን በመቀሌ ከተማ ሊያደርግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በከፍተኛ አፈናና እስር እንዲያስተጓጉል መደረጉ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሓሳብ የማዳመጥ፣ የሚጠቅመውን የመምረጥና የመቃወም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡” ብሏል።

አማራጭ ሓሳብ በሚያቀርቡ ፓርቲዎች ላይ ህወሓት/ኢህአዴግ እየወሰደ ያለውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ርምጃና አፈና በጥብቅ እንደሚያወግዝ ያስታወቀው አንድነት “አንድነት የአረና ፓርቲ የሚያደርገውን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ህወሓት/ኢህአደግ ለማደናቀፍ የሚያደርገውን ህገወጥ ዘመቻ እንዲያቆም እየጠየቀ አሁንም ተቃዋሚዎችን ‹‹ከጠላቶቻችን ጋር የሚተባበሩ›› በማለት የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመነጠል የሚካሄደውን ዘረኝነት የተሞላበት ከፋፋይ ርምጃ ለአገራችን እጅግ አደገኛ እንደሆነ አምኖ እንደ ሌላው ህዝብ ሁሉ ለነፃነቱ መከበር የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰላማዊ ትግሉን በመደገፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እንዲሆን የከበረ ጥሪ እናቀርባለን፡፡” ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።
(ዘ-ሐበሻ)

No comments:

Post a Comment