Tuesday, January 28, 2014

ሰመጉ በቁጫ ከ400 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን አንድ ሰው መገደሉን ገለጸ


ጥር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ የአሁኑ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እየተባለ የሚጠራው አንጋፋው የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ባወጣው 129 ልዩ መግለጫ ” የሚለቀቁትን ሳይጨምር በሰላም በር ፖሊስ ጣቢያ 198 ሰዎች ፣በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት 212 ሰዎች ” መታሰራቸውን እና ከሚደርሰው መንገላታት እና ጥቃት ለማምለጥ በሺህዎች

የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሰደዳቸውን” ገልጿል። ቤቶች ያለ ፍረድ ቤት ትዕዛዝ መበርበራቸውን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞች ጥያቄውን ደግፋችኋል በሚል ከስራ መፈናቀላቸውን፣ አራት ግለሰቦች ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውንና የአንድ ሰው ህይወትም ማለፉን ሰመጉ ገልጿል።

“ህዳር 14 ፣ 2006 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰአት ቶኮ ደንቢያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች ትምህርት ቤቱ ሊዘረፍ ነው ብለው ባመለከቱት መሰረት በተጠራ ስብሰባ ላይ የ8 ቀበሌዎች ህዝብና የአካባቢው ባለስልጣናት ስብሰባውን ለሌላ ጊዜ ቀጥረው በመመለስ ላይ ሳሉ የቁጫን ህዝብ ዘፈን እየዘፈኑ ሲሄዱ ከነበሩት ተሰብሳቢዎች ውስጥ ዝም እንዲሉ ታዘው

ባለመታዘዛቸው መዝፈን የቀጠሉት አቶ ዛራ ዛላ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተርና የወረዳው አስተዳዳሪ የስጋት ስንታ በተገኙበት የወረዳው አስተዳደር ሹፌር አቶ ወንድወሰን ሳልሌ በክላሽ ጥይት ተኩሶ ገድሏቸዋል” በማለት ነዋሪዎች ለሰመጉ አቤቱታ ማቅረባቸውን መግለጫው ጠቅሷል።

“ቤተሰቡ አስከሬኑን እንዲቀብር በባለስልጣናት ቢጠየቅም ሳናስመረምር አንቀብርም በማለታቸውና ባለስልጣናቱ ለማስመርመር ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከቤተሰቡ እውቅና ውጪ በማዘጋጃ ቤት የመቃብር ቦታ ህዳር 17 ቀን 2006 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰአት እንደተቀበረ መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ሟቹ የ35 አመት ጎልማሳ፣ ባለትዳርና የሶሰት ልጆች አባት እንደነበሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹም ይህ ሪፖርት ሪፖርቱ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ለፍርድ አልቀረቡም። በተመሳሳይ መንገድ በካስኬ ገንዜ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው አቶ አፈወረቅ አበራ በተመሳሳይ ቀን ከአቶ ዛራ ዛላ ጋር አብሮ የነበረ ሲሆን የቁጫ ወረዳ አስተዳደር ሹፌር የሆነው ወንደወሰን ሳልሌ በክላሽ ጥይት በጀርባው ላይ እንደመታውና በሰላም በር ጤና ጣቢያ በመታከም ላይ እንደሚገኝ የቁጫ ህዝብን ዋቢ በማድረግ የሰመጉ ልዩ መግለጫ ያብራራል።

በጌሬራ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው አቶ ደባራ ደርዛ በ6/03/2006 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ላይ ቅዳሜ ገበያ ለመሄድ ተነስቶ ሞጎላ ቀበሌ ሲደርስ የወረዳው የፀጥታ ሃላፊ የነበረው አቶ አያኖ መሰኔ እና የወረዳው ፖሊስ አባል በየነ ባንጃ እንደተተኮሰባቸውና በሁለት ጥይቶች ግራ እግራቸው ላይ ተመተው ከ7/04/2006 ዓ.ም ጀምሮ በሶዶ ክርስቲያን ሆሰፒታል በመታከም ላይ እንደሚገኙ ሰመጉ ገልጿል።

የ75 አመቱ አዛውንት አቶ ጨለቦ ጨማ ህዝቡን ወክለህ አዲስ አበባ ሄደሀል ተብለው ከ11/3/2006 ዓ.ም ጀምሮ ሰላም በር ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩና እንደተደበደቡ ከ180 ሰዎች

በላይ አብረዋቸው እንደታሰሩና ዋስ ጠርተው በሀክምና ላይ እንደሚገኙ ህክምናውን ሲጨርሱም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚመለሱ በሆስፒታሉ ሆነው ቃላቸውን መስጠታቸውን መግለጫው ይጠቅሳል።

መግለጫው 46 የመንግስት ሰራተኞች ከስራ መባረራቸውን የስም ዝርዝራቸውን በመጥቀስ ይፋ አድርጓል። ሰመጉ በመጨረሻም ” መንግስት ይህንን መሰረታዊ የማንነት ጥያቄ በሕግ አግባብ በአፋጣኝ መልስ

እንዲሰጥበት፣ ለተፈፀሙት ወንጀሎች ማለትም ለግድያ፣ ለአካል መጉደል፣ ድብደባ፣ ሕገ-ወጥ የቤት ብርብራ፣ ህገ-ወጥ እስርና፣ ለስራ መሰናበት ምክንያት የሆኑትን ግለሰቦች በህግ አግባብ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ፣ ግድያ፣ የአካል ጉድለትና ከስራ መሠናበት ለደረሰባቸው ግለሰቦችና ቤተሰቦች ተገቢውን ካሳ

እንዲያሰጥ እንዲሁምበየአጎራባች አካባቢዎች ለተሰደዱት የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ ዋስትና በመስጠት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮአቸውን የሚመሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት በአፅንኦት ጠይቋል።

2 comments:

  1. የቁጫ ታጋይ ሕዝብ ቢታሰርም፣ ቢንገላታና ቢገደልም ትግሉ ግን አይሞትም!

    ReplyDelete