Tuesday, January 28, 2014

“የኢትዮጵያ ፓርቲዎች የሃቀኝነት ጥያቄ ይነሳባቸዋል”



ለ46 ዓመታት በፖለቲካ ትግል ውስጥ እንደቆዩ የሚናገሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞ የኢፌዲሪ ኘሬዚዳንት ኋላም
የተቃዋሚው አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ በቅርቡ ከፓርቲ-ፖለቲካ ራሳቸውን አግልለዋል።
ዶ/ር ነጋሶ፤ ለምን ከአንድነት ፓርቲ ለቀቁ? ስለተቃዋሚዎችና ስለኢህአዴግ ምን ይላሉ? በስጋት ስለሚኖሩበት
የመንግስት ቤት ጉዳይስ?
በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ብሥራተ ገብርኤል በሚገኘው መኖሪያ
ቤታቸው አግኝቶ  በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡
በስጋት ነው የምኖረው መውደቂያዬን አላውቀውም
እኔ የታገልኩት ቁስ ለመሰብሰብ አይደለም
ታጋይ እንጂ ዲኘሎማት አይደለሁም
ለ46 ዓመታት በፖለቲካ ትግል ውስጥ እንደቆዩ የሚናገሩት የ70 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞ የኢፌዲሪ ኘሬዚዳንት ኋላም የተቃዋሚው አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ በቅርቡ ከፓርቲ-ፖለቲካ ራሳቸውን አግልለዋል። ዶ/ር ነጋሶ፤ ለምን ከአንድነት ፓርቲ ለቀቁ? ስለተቃዋሚዎችና ስለኢህአዴግ ምን ይላሉ? በስጋት ስለሚኖሩበት የመንግስት ቤት ጉዳይስ? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ብሥራተ ገብርኤል በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አግኝቶ በስፋት አነጋግሯቸዋል፡፡ በስጋት ነው የምኖረው መውደቂያዬን አላውቀውም እኔ የታገልኩት ቁስ ለመሰብሰብ አይደለም ታጋይ እንጂ ዲኘሎማት አይደለሁም ለምንድነው የፓርቲ-ፖለቲካ በቃኝ ያሉት? አንደኛው፤ የእድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ጳጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም 70 ዓመት ሞልቻለሁ፡፡ ለ46 ዓመት ያህል በቀጥታ ህይወቴን ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር አቆራኝቼ ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ይበቃል የሚል ስሜት አደረብኝ፡፡ ከአሁን በኋላ ለወጣቶች ቦታውን መልቀቅ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በኔ በኩል የተቻለኝን ያህል በፓርቲ-ፖለቲካ ውስጥ አገልግያለሁ፡፡
አሁን ይበቃኛል፡፡ ይህን ስል ትግሉን አቆማለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ ሁለተኛ፤ የጤንነት ጉዳይ ነው፡፡ የስኳር ህመምተኛ ነኝ፡፡ በክኒን ነው የምኖረው፡፡ የደም ግፊትም አለብኝ፡፡ እንደልቤ መንቀሣቀስ አልችልም፡፡ በሊቀመንበርነት ከመሩት “አንድነት” ፓርቲ ጋር ስላለዎት የአመለካከት ልዩነት ይንገሩን? ለእኔ ከፓርቲ-ፖለቲካ መገለል ከላይ ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች በበለጠ ይሄኛው ዋናው ምክንያቴ ነው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ሊደረግ በታቀደ ጊዜ፣ በአመራር ውስጥ መግባት የሚፈልጉ እንዲወዳደሩ ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ለሊቀመንበርነትም ሆነ ለብሔራዊ ምክር ቤት ለመወዳደር አልፈለግሁም። ያልፈለግሁበት ምክንያት ደግሞ እኔ ወደ አንድነት የመጣሁት በመድረክ ምክንያት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ውይይት ነው መድረክ የተመሠረተው፡፡ መጀመሪያ መድረክ ወደ ጥምረት ሲሸጋገር ድርጅቶች ናቸው ተስማምተው ጥምረቱን ያቋቋሙት፡፡ እኔ ደግሞ በወቅቱ በየትኛውም ድርጅት ያልታቀፍኩ ስለነበርኩ ሁለት ምርጫ ብቻ ነበረኝ፡፡
ወይ ከመድረክ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቆም አለያም በፓርቲ ጥላ ስር ሆኜ መንቀሣቀስ፡፡ ተሣትፎዬ እንዲቀጥል ስለፈለኩ፣ የግድ ወደ አንድ ፓርቲ መግባት ነበረብኝ። ኘሮግራሙን በማዘጋጀት ብዙ ረድቻለሁ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሊሠሩ የሚችሉበት ጠንካራ ኘሮግራም ነው፣ በጣምም ደስ ስለሚለኝ ተሣትፎዬን መቀጠል ፍላጐቴ ነበር፡፡ ስለዚህ በፓርቲ ለመታቀፍ ከስድስቱ የመድረክ ተጣማሪ ፓርቲዎች የትኛው ኘሮግራም የበለጠ ለኔ ይስማማኛል መምረጥ ነበረብኝ፡፡ እናም አንድነትን መረጥኩ፡፡ በዚህ መልኩ ነበር ወደ አንድነት የመጣሁት፡፡ ከመጣሁ በኋላም መድረክ ራሱን አሣድጐ ወደ ግንባር ተሸጋገርን፡፡ ይህን ስናደርግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ብዙ ውይይቶች ነበሩ፡፡ ከየድርጅቱ ሁለት ሰዎች የተወከሉበት የሥራ አስፈጻሚ አለ፡፡ የዚያም አባል ነበርኩ፡፡ የአንድነት ፓርቲ ኘሮግራም ያስቀመጠው አቅጣጫ፤ ሁሉም ፓርቲዎች ቢዋሃዱ ለዚህች ሀገር ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልጽ ነው፡፡ ህዝቡም ተመሣሣይ ግፊት ያደርግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ነው መድረኩ ከጥምረት ወደ ግንባር የተሸጋገረው። የመድረኩ ሥራ አስፈጻሚ፤ የግንባሩን ኘሮግራም እና የወደፊት አቅጣጫዎች ሠርቶ ለየፓርቲዎቹ ሥራ አስፈጻሚዎች አቀረበ፡፡ የድርጅቶቹ ሥራ አስፈጻሚዎች ከተወያዩበት በኋላ በኘሮግራሙ ተስማሙ፣ አንድነትም ተስማማ፡፡ የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ ከተስማማ በኋላ፣ የመጨረሻ ወሣኝ የሆኑት ሁለት አካላት ውሣኔ ይጠበቅ ነበር፡፡ አንደኛው፤ ብሔራዊ ምክር ቤት ሲሆን ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
በዚህ ተዋረድ መሠረት፣ ሥራ አስፈጻሚው የተስማማበትን የግንባሩን ኘሮግራም ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት አወረደ፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተቀበለው፡፡ ከዚህ በኋላ የመጨረሻ ወሣኙ ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ጠራንና፣ ጠቅላላ ጉባኤው በበጐ ተቀበለው፡፡ ይሄን አካሄድ እንግዲህ ሁሉም የመድረክ ተጣማሪ ድርጅቶች ናቸው የተገበሩት፡፡ አንድነትን ጨምሮ ሁሉም ድርጅቶች በዚህ ሂደት “ግንባሩ ይፈጠር” የሚለውን ከወሰኑ በኋላ የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠራ፡፡ ከእያንዳንዱ ድርጅት በደንቡ መሠረት 10 ሰው ተወከለ፡፡ 10 የአንድነት ወኪሎችም በመድረኩ ጉባኤ ተገኙ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንደኛ፤ መድረክ የገንዘብ ችግር ነበረበት፡፡ ሁለተኛ፤ ደግሞ ሰዎች በትርፍ ጊዜያቸው ነበር የሚሠሩት፡፡ እነዚህ የስራ መጓተቶች ፈጠሩ፡፡ በዚህ የተነሳም አንዳንድ ጭቅጭቆች ተነሱ፡፡ ለምሣሌ ኘ/ር በየነ፤ በግርማ ሠይፉ ላይ ሲሠጡ የነበረው አስተያየት፣ ግርማም ሲሰጠው የነበረው ምላሽ፤ አቶ ቡልቻም በአንድነት ላይ ሲሰነዝሩት የነበረው አሉታዊ አስተያየት…፤ እነዚህ ሁኔታዎች በአንድነት አባላት ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ፈጥረዋል፡፡ እንዴት የመድረክ አባል ሆነን አሉታዊ አስተያየት ይሰነዘርብናል የሚሉ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ ይሄ አሉታዊ ሁኔታ እያለ ከአንድነት አባላት አንድ ሃሣብ መጣ፡፡ “የመድረክን ሂደት እንገምግም” የሚል፡፡ በብሔራዊ ምክር ቤቱም ሂደቱን ገምግመን ማጠናከር አለብን የሚል ውሣኔ ላይ ተደረሰ፡፡ አንድ ኮሚቴም ተቋቋመ፡፡ ድጋሚ የተቋቋመው ኮሚቴ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግምገማውን አጠናቆ፣ ውጤቱን ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አቀረበ፡፡ እዚያ ላይ ነው እንግዲህ ችግሮች መፈጠር የጀመሩት፡፡
ገምጋሚ ኮሚቴ ያመጣው አንደኛው የግምገማ ውጤት፤ የመድረክ አባል ድርጅቶች ከአንድነት ኘሮግራም ጋር የማይስማሙ አቋሞችና አላማዎች አሉት፤ በዚህ ሁኔታ ግንባር ፈጥሮ አብሮ መሥራት አይቻልም የሚል ነው፡፡ሁለተኛው ደግሞ ግንባር እንዲሆን የተወሰነው በደንብ ጥናት ተደርጐበትና በቂ ውይይት ተካሂዶበት ሳይሆን አመራሩ ብቻ ያደረገው ነው የሚል ሆነ፡፡ ይሄ ነው በእኔና በአንድነት አባላት መካከል ልዩነት የተፈጠረው፡፡ በእርግጥ ቀድሞም ቢሆን መድረክ እና አንድነት የሚለያዩባቸው አንዳንድ ነጥቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለምሣሌ የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ጉዳይ፣ የግለሰብና የቡድን መብት ጉዳይ፣ የመሬት ጥያቄ አፈታት፣ የፌዴራሊዝም ጥያቄ የመሣሠሉት ላይ ልዩነት ነበረው፡፡ እንዴት እነዚህ ልዩነቶች እያሉ ግንባር እናቋቁማለን የሚል ጉዳይም ተነስቷል፡፡ በወቅቱ እኔያቀረብኩት አስተያየት “እነዚህ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ዋናው በዴሞክራሲያዊ አካሄድ ወደፊት ልዩነቶቹ የሚፈቱበት ሁኔታ በኘሮግራሙ መቀመጡ ነው” የሚል ነበር፡፡ በመድረክ ያሉ ፓርቲዎች ፌዴራሊዝምን የሚደግፉ ቢሆንም በኢትዮጵያ አንድነት እምነት አላቸው፡፡ በኘሮግራሙም መገንጠልን አንደግፍም የሚል አቋም ላይ ተደርሷል። “ልዩነቶች ሊያለያዩን አይገባም፤ አብረን እየሠራን ከምርጫው በፊት ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ምህዳር እንዲፈጠር በማድረግ፣ የጋራ ማኒፊስቶ አዘጋጅተን፣ ወደ ፓርላማ እንገባለን ነበር የተስማማነው፤ እኛ ብቻ ሣንሆን ኢህአዴግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶችም ፓርላማ ይገባሉ፣ ይህን መነሻ አድርገን የጋራ መንግስት እናቋቁማለን፡፡ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት መዋቅር ከተፈጠረ በኋላ፣ የመድረኩ ግንባር ተጣማሪዎች የየራሣቸውን ኘሮግራም ይዘው ወጥተው አሊያም አንድ ሆነው የመሠላቸውን ትግል” ይቀጥላሉ በሚል ይሄን ስምምነት የፓርቲው ግምገማ አፈረሰው። በዚህ የተነሣ በሃሣብ ተለያየን፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ግምገማውን ተቀበለው እኔ ተቃወምኩኝ፡፡
ይሄ የሆነው በ2005 ሚያዚያ ወር ነው፡፡ ሁለተኛው ልዩነት የተፈጠረው ደግሞ የግምገማው ውጤት ምን ይሁን በሚለው ላይ ነው፡፡ የግምገማው ውጤት ወደ መድረክ ይሂድና ለውይይት ይቅረብ፤ በሌላ በኩል ወደ ሚዲያ ወጥቶ ህዝቡ ይወያይበት፤ ይሄ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረግ በሚል ብሔራዊ ምክር ቤቱ ወሰነ። ነገር ግን ጉዳዩ በማግስቱ ከውሣኔው ውጪ ሚዲያ ላይ ቀድሞ ወጣ፡፡ አንድ ግለሰብ ጋዜጣ ላይ በስፋት አወጣው፡፡ ይሄን የመድረክ ሰዎች ሲያዩት ትልቅ ቁጣ አስነሣ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ አንድነት ራሱን ሂስ ያድርግና ማስተባበያውን በጋዜጣ ያውጣ ወይም ይሄን ባደረገው ሰው ላይ እርምጃ ውሰዱ የሚል ማስጠንቀቂያ ከመድረክ ቀረበ፡፡ የእኔ አቋም “በሚዲያ ቢወጣ ምናለበት፣ ሂስም ማድረጉ ክፋት የለውም” የሚል ነበር፡፡ ሌሎች ግን አልተስማሙም። እንግዲህ በዚህ ላይም በእኔና በሌሎች የፓርቲው አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በመድረኩ ስብሰባዎች ላይ በሙሉ ህሊናዬ ሆኜ አንድነትን ለመወከል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገባሁ፡፡ እንደ ሊቀመንበር የግድ አንድነትን መወከልና የፓርቲውን ሃሣብ ማስተጋባት አለብኝ በሌላ በኩል ደግሞ ህሊናዬ ይሞግተኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ዘንድሮ የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ከመግባት ተቆጠብኩ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ የውህደት ጉዳይ ተጀመረ፡፡ መኢአድ እና አንድነት ይዋሃዱ ተብሎ ድርድር ተጀመረ፡፡ የቅድመ ውህደት ሠነድም ተዘጋጀ፡፡ በዚያ ሰነድ ላይ እኔና ብሔራዊ ምክር ቤቱ አሁንም ተለያየን፡፡ ብዙ የልዩነት ነጥቦች ናቸው፡፡ እነሱን አሁን መዘርዘር አልፈልግም፡፡ እርስዎ ውህደቱን አይደግፉም ማለት ነው? ውህደት እደግፋለሁ፤ ነገር ግን ሲዋሃዱ በምን ላይ ነው የተመሠረቱት፤ የውህደት ስምምነቱስ ምንድን ነው? በሚለው ላይ አንዳንድ ጥልቀት ያለው ውይይት ሊካሄድባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ግን እነዚህን ውይይት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች እንዳለ ተቀብሏል። ለምሣሌ የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ጉዳይ አለ። አንቀጹ የመገንጠል መብትንም ያካትታል፡፡ ይሄን አንቀጽ የውህደቱ ተደራዳሪ ኮሚቴ አይደግፍም፤ ከህገ መንግስቱም መሰረዝ አለበት ሲል ተስማምቶበታል፡፡ በእኔ በኩል ደግሞ ይሄ የማይቻል ነው፡፡ አንቀጽ 39ን ይደግፋሉ? አዎ! እደግፋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የመብት ነው፡፡ መብቱ ይከበር ነው እንጂ መገንጠል ይኖራል ማለት አይደለም፡፡
ስለዚህ እኔ አንቀጽ 39 ከህገ መንግስቱ ይሠረዝ የሚለውን አልደግፍም፡፡ ይህን ተቃውሞዬን በማሠማበት ጊዜ፣ እኛ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አንደራደርም የምትል ማሻሻያ በድርድር ሰነድ ላይ ቀረበች፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ይሄን ሙሉ ለሙሉ ተቀበለው፡፡ በእኔ በኩል አሁንም ይሄ አባባል አስቸጋሪ ነው አልኩ፡፡ መብት አክብረህም አንድ ክፍለ ህዝብ መብቴ አልተከበረም፤ እገነጠላለሁ ካለ ምንድነው የሚሆነው? ወደ ጦርነት ነው የሚኬደው ወይስ ሌላ አማራጭ አለ? እዚህ ላይ ልዩነቶች ተፈጠሩ፡፡ አሁን መጨረሻ ላይ ደግሞ በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የምረጡኝ ቅስቀሣ ሲካሄድ ነበር። እዚያ ላይ ጠቅላላ ጉባኤው፤”ውህደቱ ያስፈልጋል በማለት በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ከመኢአድ፣ ከአረና እና ከመሣሠሉት ፓርቲዎች ጋር ውህደት እንዲፈጸም” ብሎ የወሰነውን ውሣኔ ኢ/ር ግዛቸው ወሰደና፣ “እንዲያውም ለውህደቱ የተሰጠው ጊዜ ዘግይቷል በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ አደርጋለሁ” ሲል ቅስቀሣ ማካሄድ ጀመረ፡፡ በተጨማሪም “ከአሁን ጀምሮ በጥምረት፣ በግንባር በመሣሠሉት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፤ ውህደት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፤ በዚህ አካሄድ ነው የምሠራው” ሲል አቋሙን ገለፀ ፤ በዚህም በከፍተኛ ድምጽ ተመረጠ፡፡ ይሄ ለኔ ሌላ ትርጉም አለው፡፡ የእኔ ግልጽ አቋም ምን መሠለህ? ከተቻለ ውህደት ጥሩ ነው፤ ወደ ውህደት የምትደርሰው ግን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው እንጂ አድርጉ ስለተባለ መሆን የለበትም፡፡ ውህደት ላይ ሁሉም በአንድ እጅ ማጨብጨብ አለበት፤ በኘሮግራም ሙሉ ለሙሉ መስማማት አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ይሄ የመጨረሻው ውሣኔ ላይ እንድደርስ እና ከፓርቲው እንድወጣ ያደረገኝ ጉዳይ ነው፡፡
በዚህና ከላይ ባስቀመጥኳቸው ምክንያት አቅጣጫው የተለወጠ ይመስለኛል፡፡ እኔ ደግሞ ከአቅጣጫ ለውጡ ጋር ህሊናዬ ተስማምቶ ሊሠራ አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ከአንድነት ልወጣ ችያለሁ፡፡ ከፓርቲው ከወጣሁ በኋላ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሣስብም የደረስኩበት ድምዳሜ የፓርቲ-ፖለቲካ ይበቃኛል የሚለው ሆነ፡፡ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ከፓርቲ ፖለቲካ ሲገለሉ መጽሀፍ ይጽፋሉ፣ልምዳቸውን ያካፍላሉ፡፡ እርስዎ ምን አሰቡ? ርዕሱንና ይዘቱን መግለጽ አልፈልግም እንጂ መጽሃፍ እየጻፍኩ ነው፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ ምክር መስጠትና ልምድ ማካፈልም አለ፡፡ እኔ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው በአንድነትም ሆነ በመድረክ ላይ “ትክክል አይደሉም” ብዬ ጫና ለመፍጠር አልፈልግም፡፡ እንዲጐዱም አልፈልግም፡፡ ለዚህች ሀገር ፖለቲካ አስፈላጊ ኃይሎች መሆናቸውን በሚገባ አምናለሁ፡፡ ከአንድነት የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከነበሩት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ጋርም አለመግባባቶች ተፈጥረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ መነሻው ምን ነበር? ኢ/ር ዘለቀ የድርጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበር፡፡ የፓርቲውን የድርጅት ስራ ማንቀሣቀስ ነበረበት፡፡ ግን እንደታሰበው ሣይሆን ድክመት ተፈጠረ፡፡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የተቻለውን ያህል መከርን፤ ግን አልሆነም፡፡ እኔ ነበርኩ ኃላፊነቱን የሠጠሁት፡፡ ሥራው ከተዳከመ አልንና ኃላፊነቱን እንዲለቅ አደረግን፡፡ እሱ ግን ደብዳቤ አልደረሰኝም ብሎ ጋዜጣ ላይ አወጀ፡፡ ይሄ ግን አይደለም፤ በወቅቱ ደብዳቤውን ሰጥቼዋለሁ፡፡ ይሄ ነው የግል ፀብ ያስመሰለው እንጂ የአለመግባባቱ መንስኤ የአሠራር ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ራሱ በአንዳንድ የዲስፒሊን ግድፈቶች የተነሳ በአባልነቱ ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡ በእኔና በአሥራት ላይም በየጋዜጦቹ ያወጣቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡
አሁን ደግሞ ኢ/ር ግዛቸው በሥራ አስፈጻሚነት መልምሎታል፡፡ እኔ በዚህ ምንም ቅር አይለኝም፡፡ በግል ግን እኔና እሱ ፀብ የለንም፤ እንቀራረባለን፡፡ በ46 ዓመታት የፖለቲካ ህይወትዎ ለኢትዮጵያ ህዝብ አበርክቻለሁ የሚሉት ጉልህ አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ዴሞክራሲና ፍትህ ከሌለ፣ ጭቆናና የሰብአዊ መብት ጥሰት ከተንሰራፋ፣ ሰው ሁሉ መታገል አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔም በዚህ መርህ መሠረት፣ የራሴን ድርሻ ህሊናዬ በፈቀደው መንገድ እየተጓዝኩ አበርክቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ዴሞክራሲ እንዲኖር፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ አነቃቅቻለሁ ለማለት እችላለሁ፡፡ ለህሊና መኖር እንደሚቻል ያሣየሁም ይመስለኛል፡፡ ዋናው ነገር ሰው ሁልጊዜ መብቶቹ ካልተከበሩ መታገል አለበት፡፡ ባላደርግሁት ብለው የሚቆጩበት ፖለቲካዊ ውሣኔ ይኖርዎት ይሆን? አየህ… አሁን ለምሣሌ ሶሻሊዝምን እደግፍ ነበር። ደርግ ሶሻሊስት ነኝ ባለ ጊዜ ልደግፈው እችል ነበር፤ ነገር ግን አምባገነን ነው፡፡ ወጣቶችን የሚገድልና መብቶችን የሚደፈጥጥ ነበር፤ በዚያ ሶሻሊስት ስለሆነ ብቻ ሁሉን ሃጢያቶቹን ትቼ እሱን ለመደገፍ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ኦነግን ረድቻለሁ፤ ነገር ግን ኋላ ላይ ተጣላን፤ የተጣላንበት ምክንያት ተበታትኖ በየጐጡ እየተደራጁ የሚደረጉ ትግሎችን ተቃውሜ፣ ወደ አንድ መድረክ መሰባሰብ ይገባል የሚል አቋም በመያዜ ነበር፡፡ በአውሮፓ ይገኙ የነበሩ ሁለት የኦሮሞ ድርጅቶችን ለማቀራረብ ስንቀሣቀስ አንደኛው ድርጅት፤ “ይሄ ጐበና ዳጩ /የሚኒልክ ጦር አዝማች የነበሩት/ ነው “አለኝና አገለለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ኦፒኤልኤፍ ከሚባል ድርጅት ጋር እየሠራን እያለ፣ በ1983 “ዱለ ወልቂጡማ ቢሊሱማ” /ዘመቻ ለነጻነትና ለእኩልነት/ ሲታወጅና ጦሩ ከጐጃም ተነስቶ ወደ ወለጋ ሲጓዝ “ይሄ ደግሞ ቅኝ ግዛት ነው” አሉ፡፡ እኔ በወቅቱ “ይሄ ዳግም ቅኝ ግዛት ሊሆን አይችልም።
ምክንያቱም ደርግ ሌላ ቦታ ተሸንፎ መሠረት ያደረገው ኦሮሚያ ውስጥ ነው፤ ስለዚህ ይህን ኃይል ለመደምሰስ የሚደረግን ዘመቻ ዳግም ቅኝ ግዛት ነው ብሎ ያለመደገፍ ደርግ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ብዬ አቋም በመያዝ ከእነሱ ጋር ተለያየን፡፡ እንደገና ወደ ኦህዴድ ከመጣሁ በኋላ በ1993 ዓ.ም ከኢህአዴግ የተለየሁት በአቅጣጫ ልዩነት ነው፡፡ ሶሻሊስት ነን ብዬ አብሬ ስሰራ እነሱ ነጭ ካፒታሊዝምን ነው የምንከተለው ብለው በድንገት አወጁ፤ እኔ ደግሞ በካፒታሊዝም አላምንም፡፡ ምክንያቴም ካፒታሊዝምን እንከተላለን ሲባል እንዲሁ የውሸት በመሆኑ ነው፡፡ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሣቀስ ባልቻሉበት እና የብሔር ጥያቄ ባልተፈታበት ሁኔታ ካፒታሊዝምን እንከተላለን ማለት ሌላ ችግር ያመጣል ብዬ ተለያየን ፡፡ ከዚህ አንጻር ህሊናዬ በሚፈቅደው መንገድ ነው ስሄድ የነበረው ማለት ነው፡፡ ህሊናህ በፈቀደው መንገድ ስትጓዝ ደግሞ የሚቆጭህ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ እኔ አንዳችም የሚቆጨኝ ነገር የለም በውሣኔዎቼ ሁሉ ደስተኛ ነኝ፤ የራስን ሃሣብና የህሊና ጥያቄ ገፍቶ ለድርጅታዊ ውሣኔ ብቻ መገዛት በእኔ በኩል ትክክል አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ልዩነት ቢኖርህም ልዩነትህን ውጠህ እዚያው ብትቆይ ይሻልህ ነበር” የሚል ሃሣብ ያመጣሉ፤ ለኔ ግን ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ አንዳንዶች እርስዎ ዶ/ር ነጋሶ፤ “ቀጥተኛ ሁሉን ነገር በግልጽ የሚናገሩ ስለሆኑ ለፖለቲካው የሚሆኑ ሰው አይደሉም ይላሉ…. አዎ! እኔ ዲኘሎማት አይደለሁም፡፡ ቀጥተኛ ታጋይ ነኝ፡፡ ፖለቲካው ወደዞረበት እየዞረ የሚሄድ ፖለቲከኛ ዲኘሎማት አይደለሁም፡፡ ዲኘሎማት የሆኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ በዚህም በዚያም ብለው ግባቸው ላይ ለመድረስ ነው የሚጥሩት፡፡ እኔ ያንን አልችልበትም ፡፡ ቀጥተኛ መሆንዎ ያሣጣዎት ነገር አለ? ምን ያሣጣኝ ነገር አለ? /ረጅም ሣቅ/ ምናልባት በቁሣቁስ አሣጥቶኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ማቴሪያል ደግሞ ድሮም አልነበረኝም፤ አሁንም የለኝም፡፡ ሰዎች ከኢህአዴግ ጋር ባትጣላ ኖሮ ቢያንስ እንደ መቶ አለቃ ግርማ ትኖር ነበር ይሉኛል፡፡
ያንን ካየህ በቁስ ደረጃ ያጣሁት ነገር አለ ተብሎ ሊታሠብ ይችላል፡፡ ይሄ ያለሁበት ቤትም የኔ አይደለም፤ ከዚህም ውጣ ከተባልኩ ቆይቷል፡፡ መውደቂያ ስለሌለኝ እምቢ ብዬ ነው እንጂ፡፡ አበል የለኝም፣ ከአንድነት ትሠጠኝ የነበረች 3 ሺ 800 ብር አበልም ከበቀደም ጀምሮ ቆማለች፡፡ የምኖረው እንግዲህ ከቀበሌ በማገኛት 1300 ብር ጡረታዬ ነው፡፡ ባለቤቴም መጠነኛ ገቢ የምታገኝባት ሥራ አላት፡፡ እንግዲህ አሁን ያለሁበትን የኑሮ ደረጃ ካየህ፣ አጥተሃል የሚሉኝ ሰዎች ሃሣብ ትክክል ነው ልትል ትችላለህ፤ ነገር ግን ይሄ ለኔ አይቆጨኝም፤ ስሜትም አይሰጠኝም፤ ምክንያቱም እኔ በዚህ አይደለም የታገልኩት ቁስ ለመሰብሰብ አይደለም ፡፡ እስቲ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ አናውራ…. በአሁኑ ወቅት ለህዝብ መብትና ጥቅም በሃቀኝነት የሚታገሉ ፓርቲዎች አሉ? በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሃቀኛ ናቸው አይደሉም የሚለው ግምገማ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁሉም በመሠለው መንገድ እየታገለ ነው፡፡ ለኔ ግን ካየኋቸው ተሞክሮዎች፣ በእርግጥም ሃቀኛ ድርጅት ነው ብዬ የማምነው የህዝብን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነትን የሚቀበል ፓርቲ ነው፡፡
ለዚህ ተግባራዊነት የሚንቀሣቀስ መሆን አለበት እንጂ ለፓርቲ ኘሮግራም እና ዓላማ ብቻ የሚሠራ መሆን የለበትም፡፡ እዚህ አገር ሁሉም ፓርቲዎች ለህዝብ ነው የሚታገሉት ይባላል። ግን ከገዥው ፓርቲ ጀምሮ በሁሉም ላይ ችግር አያለሁ፡፡ ኢህአዴግ ለስሙ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ ምናምን ይላል፤ የሚሠራው ግን ሌላ ነው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም የምንታገለው ለህዝብ የስልጣን ባለቤትነትና ለዴሞክራሲ ነው ይላሉ፤ ያ ከሆነ በጋራ መሥራትን ለምን ይፈሩታል? ከዚህ አኳያ ከተመለከትነው ሁሉም ፓርቲዎች ላይ የሃቀኝነት ጥያቄ ይነሣባቸዋል ማለት ነው፡፡ እርሶ ሲመሩት የነበረው አንድነት፤ “ገዥው ፓርቲ ሀገሪቱን በብሔር ከፋፍሎ ኢትዮጵያዊነትን ሸርሽሯል” የሚል አመለካከት አለው፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ “የቁጫ ብሔረሰብ ማንነቱ ለምን አይከበርም ሲል የብሔር መብት ጥያቄ ያነሣል፡፡ እነዚህ ነገሮች እርስ በእርሣቸው አይጋጩም? በአንድነት ኘሮግራም ላይ አንድ አንቀጽ አለ። የኘሮግራሙ 3.1.5 አንቀጽ፤ “አብይ የፖለቲካ ጥያቄዎች በፖለቲካዊ መንገድ ነው የሚመለሱት፤ ይሄም በህጋዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ፤ በውይይት እና በድርድር ነው፤ በዚህ መንገድ አብይ ጥያቄዎች ካልተፈቱ ወደ ህዝብ ነው የሚሄደው” ይላል፡፡ ይሄ አንቀጽ እውነት ይታመንበታል ወይ የሚለው ለኔ ጥያቄ ነው፤ ለእኔ ከፖለቲካ ጥያቄዎች አንዱ የብሔር ጥያቄ ነው፡፡ አብይ የፖለቲካ ጥያቄ እንደሚኖር የምታምን ከሆነ፣ አንቀጽ 39ን መቃወም የለብህም ማለት ነው፡፡ የብሔር ጥያቄ የምታምንበት ከሆነ “በኢትዮጵያ አንድነት አልደራደርም” አትልም ማለት ነው፡፡ እኔ ተቃርኖውን በዚህ መንገድ ነው የማየው፡፡የቁጫን ህዝብ በተመለከተ ግን የአንድነት ኘሮግራም ላይ የግለሰብ እና የቡድን መብት መከበር እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ የቁጫ ህዝብ አንድ ቡድን ነው፤ አንድነት የማንነት ጥያቄ ሣይሆን የመብት ጥያቄውን ነው የደገፈው፡፡
ጥያቄያቸው ይሰማ ነው ያለው። እነሱ የጠየቁት ይሰማ ከሚለው አኳያ ነው እንጂ ማንነታቸው ይታወቅ የሚል አይደለም፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ጥሩ አቅጣጫ ይዟል፤ በቀጣይ ምርጫም የስልጣን ባለቤት ሊሆን ይችላል ብለው ተስፋ የጣሉበት ፓርቲ አለ? አሁን ይህን ማለት ጥሩ አይደለም፡፡ ይሄኛው ከዚህ የተሻለ ነው ብዬ መወሰንም አልችልም፡፡ ፓርቲዎች ይደራጁ፣ ይሞክሩ፤ ከተመረጡ ይመረጡ፤ አሁን አለ ወይም የለም የሉም ብዬ ከደመደምኩኝ ጥሩ አይሆንም ነገር ግን ሁሉም በተቻለ መጠን ከልባቸው ለህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ይታገሉ፡፡ በኢህአዴግ በኩልም የፖለቲካ ምህዳሩን መክፈትና ሁሉንም ፓርቲዎች በእኩል ማስተናገድ አለበት፡፡ ፓርቲዎች ከአሁን ጀምረው ተሰባስበው፣ ለዲሞክራሲ መሥራት አለባቸው፡፡ አሁን ጥሩ እየሠሩ ነው የሚሏቸው ፓርቲዎች የሉም? እየሞከሩ ነው ሶስተኛ አማራጭ አለ። አክትቪዝምን የሚከተሉ አሉ፣ አንድነትም፣ መድረክም…. ሌሎችም አሉ፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ግን ይሄኛው ይሻላል ያኛው አይሻልም ወይም ሁሉም አይረቡም በሚለው ላይ ግን አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ከፓርቲ ፖለቲካ ራስዎን ቢያገሉም በግልዎ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በግልዎ ለፓርላማ መወዳደርስ? የለም ይበቃኛል፡፡ ወደ ፓርላማው መግባትም አልፈልግም፡፡ ምናልባት በፓርቲዎች መካከል ስምምነት ለመፍጠር፣ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል መቻቻል እንዲኖር፤ ሁሉም በብሔራዊ ጉዳይ እንዲስማማ የማድረግ እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ እሞክራለሁ፡፡ ምናልባት ኢህአዴግ፤ ለሁለተኛ ጊዜ አብረውት እንዲሰሩ ወይም በማማከር እንዲያግዙት ቢጠይቅዎ ፈቃደኛ ይሆናሉ? ምክር ከፈለገ አብሬ ብሠራ ምንም ችግር የለብኝም፡፡
ስብሰባዎች ካሉ እሣተፋለሁ፡፡ በቅርቡ አቶ ስብሃት ነጋ በሂልተን ሆቴል አንድ ሴሚናር አዘጋጅቶ ጋብዞኝ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ተሣትፌያለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆርናሊዝምና ኮሚኒኬሽን ኢንስቲትዩት የፌዴራሊዝም ጥያቄ ላይ በተደረገ ውይይት ጋብዞኝ አስተያየቴን ሰጥቻለሁ፡፡ በቅርቡም ሌላ ውይይት ላይ እንድገኝ ጠይቀውኛል፡፡ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ከተፈጠረ ለምን እምቢ እላለሁ፡፡ የመድረክ ሰዎች ብዙዎቹ እኮ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከቀጠረኝ የመንግስት ስለሆነ አልፈልግም አልልም፡፡ ኢህአዴግም በምክር ከፈለገኝ አማክረዋለሁ፤ “ይሄን ብታደርግ ይሻላል፤ ይሄ ጥሩ አይደለም” ለሚለው ሃሣብ በሩን ከከፈተ ጥሩ ነው፡፡ ድሮ የትግል አጋርዎ የነበሩት የቀድሞ የኦነግ አመራር አቶ ሌንጮ ለታ “ወደ ሠላማዊ ትግል ተመልሻለሁ አዲስ ፓርቲም አቋቁሜያለሁ” ማለታቸው ለኢትዮጵያ ፋይዳው ምንድን ነው? ተቀባይነትስ ያገኛሉ ብለው ያስባሉ? በአገር ውስጥ 72 ፓርቲዎች ስላሉ የእነሱ አዲስ ፓርቲ ይዞ መምጣት ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡ ከሌሎች ጋር ቢቀናጁ ይሻላል የሚል ሃሣብ አለኝ። ምክንያቱም በኦሮሞ ስም የተደራጁ ብዙ አሉ፡፡ “በኢትዮጵያ ጥላ ስር መኖር ይቻላል” ከሚለው አኳያ ስንመለከተው የእነ ሌንጮ መምጣት የሚጨምረው እሴት ይኖራል፡፡
በሌላ በኩል በአጠቃላይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሣቀሱ ፖርቲዎች ሁለት አቅጣጫ ነው የያዙት፡፡ አንዱ እንገንጠል፣ ሌላው በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነን እንኑር የሚሉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ጥላ ሥር እንኑር ለሚሉት የእነ ሌንጮ መመለስ ድጋፍ ሲሆን እንገንጠል ለሚሉት ደግሞ ድጋፉን ያጐድልባቸዋል፡፡ አገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ ሲታገሉ የቆዩትን የኦሮሞ ድርጅቶችና የእነ ሌንጮ ፓርቲ ውዝግብ ውስጥ እንዳይገቡ እፈራለሁ፡፡ በሌላ በኩል ኦነግ በእነ ሌንጮ ላይ ትግሉን ገድለውታል የሚል ሃሣብ የሚያነሣ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለኦሮሚያ “ህዝብ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ እንኑር” የሚለውን አስተሣሠብ የበለጠ ያጠናክራል፡፡ በእኔ እይታም የኦሮሞ ህዝብ ይሄንን ነው የሚፈልገው፡፡ የዳያስፓራውን ፖለቲካ እንዴት ይገመገሙታል? አንዳንዶች የሃይማኖት ተቋማትን በዘር እስከ መከፋፈል ደርሰዋል በሚል ይተቻሉ… ጨለምተኛነት አለ፣ አክራሪነት አለ፣ በሀይማኖትና በጐሣ መከፋፈል የእነ ሌንጮ ፓርቲ ተቀባይነት ያገኛል ወይ የሚለው አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ 17 ዓመት ጀርመን ሀገር ስለኖርኩ አውቀዋለሁ፤ ከአንዳንድ የኦሮሞ ጓደኞቼ ጋር የምጣላው ለዚህ ነበር፡፡ ለምሣሌ እኔ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ አስመጥቼ ሳነብ ሲያዩ፡፡ “እንዴት ይሄን የአማራ ጋዜጣ ታነባለህ?” ይሉኛል ወይም መንገድ ላይ ሰውን በአማርኛ ሰላም ስል ደስ አይላቸውም ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ዛሬም አሉ፡፡ እዚያ ነጻነት አለ፤ ግን ነጻነት በዚህን ያህል ደረጃ መከፋፈላቸው፤ በአገር ቤቱ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡ ከኢህአዴንም ከአንድነትም የወጡት በአቅጣጫና በአመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ከሁለቱ የበለጠ ያልተመቾት የቱ ነው? በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
የኢህአዴጉ በአንድ በኩል “የህወኃት አንጃ” ያላቸውን ሰዎች ያስተናገደበት መንገድ አስከፊ ነው፡፡ ያኔ እኔ ምርጫ ቦርድ ብሆን ኖሮ፣ ኢህአዴግን ሠርተፊኬቱን እሠርዝበት ነበር። ምክንያቱም ሰዎቹ ህገ-መንግስቱና የምርጫ ህጉ በሚፈቅደው መንገድ አይደለም የተባረሩት፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው አልተጠበቀም ያ ለኔ ብዙ ራስ ምታት ፈጥሮብኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሰኔ ላይ አቅጣጫ መቀየር መጣ፡፡ እንግዲህ እሱ እና አሁን በአንድነት ያጋጠመኝ ይመሣሠላል፡፡ እኔ ላይ ጭቅጭቅና አለመግባባት በመፍጠር ረገድ ግን የኢህአዴጉ ነው የሚበዛው፡፡ ከአንድነት ስወጣ በእድሜ መግፋት እና በጤና እንደምለቅ አስቀድሜ ስለገለፀኩ ከጭቅጭቅ ያመለጥኩ ይመስለኛል። አንድነት በዚህ በኩል ሊበራል ነው፡፡ ሃሣብን ያከብራል፤ ያለ ቅሬታ ነው የተለያየነው፡፡ የኢህአዴጉ ግን የልብ ድካም ሁሉ ያመጣብኝ ነበር፡፡ አዲሱን የኢፌዲሪ ኘሬዚዳንት በተመለከተ አስተያየት አለዎት? የኘሬዚዳንት ተቋም ኃላፊነትና ተግባር እንዲሆን የተፈለገው የእንግሊዙ ሲስተም ነው፡፡ በእንግሊዝ ንግስቲቱ ሀገርን ትወክላለች፤ ሆኖም ግን እዚያ ብዙ ጥንቃቄ አለ ንግስቲቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ትደግፋለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፊናው እያንዳንዷን ነገር ማማከር፣ ሪፖርት ማድረግና የውሣኔ ሃሣቦችን መቀበል አለበት፡፡
እዚህ ያ የለም፤ አሁን ተፈጥሮ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔ ባለሁበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማክሮኝ አያውቅም፡፡ እኔም ብዙ ጊዜ የኦህዴድን የድርጅት ሥራ በመሥራት ላይ ተጠምጄ ስለነበር በሌሎቹ ሥራዎች ላይ አልተንቀሣቀስኩም። ኘሬዘዳንት ግርማም በህመም ምክንያት አልተንቀሣቀሱም፡፡ የአሁኑ እንግዲህ እየተንቀሣቀሱ እንደሆነ አላውቅሁም፡፡ ሆኖም ግን በእድሜም በጤናም ደህና ናቸው፡፡ በትምህርትም ደህና ናቸው፤ በግርማ ሞገስም ገጽታቸው ለኘሬዚዳንትነት አይከፋም፡፡ ነገር ግን የኛ ህገ መንግስት ለኘሬዚዳንቱ ስልጣን አይሠጥም፡፡ በግል ቂም አለው ወይ እንዳትለኝ እንጂ የአሁኑ ኘሬዘዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና ዳዊት ዮሐንስ ነበሩ ያኔ በእኔ ላይ የፈረዱት። ሁሉን ነገር እንዳጣ የወሰኑት እነሱ ናቸው፡፡ በ97 ዓ.ም ምርጫ ጊዜ ምርጫ ውስጥ ገብተሃል፤ ብሎ አዋጅ ጥሰሃል ስለዚህ ጥቅማ ጥቅሞችህንና መብትህን ታጣለህ” ብለው የወሰኑት እነሱ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሙላቱ ያኔ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ነበር፡፡ አሁን የሚኖሩበት ቤት ከኘሬዚዳንትነት ሲለቁ የተሰጥዎ ነው? ከኘሬዚዳንትነት የለቀቅሁ እለት የት እንደሚያስገቡኝ ጨንቋቸው፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጠገብ ካለች አንዲት ቤት ነበር ያስገቡኝ፡፡ እዚያ 6 ወር ከኖርን በኋላ ወደ ቦሌ ወሰዱን፤ ጥሩ ቤት ነበረች፤ 3 መኝታ ቤት አላት፣ ቢሮ ግን የላትም፡፡ ግድግዳውና መስታወቱ ተሠነጣጥቆ በጋዜጣ ነበር እየሸፈንን ሁለት አመት ቆየን፡፡ ከዚያ አሁን ያለሁበት ቤት አመጡን፡፡ አሁን ከፓርቲ ፖለቲካ ሲገለሉ ጥቅማ ጥቅሜን መለሼ ላገኝ እችላለሁ የሚል ተስፋ የሎትም? የቀድሞ ኘሬዚዳንት ከወገንተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መገለል አለበት ይላል፡፡ አተረጓጐሙ እንግዲህ በኢህአዴግ እይታ አፍህን ዘግተህ ተቀመጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ማስጠንቀቂያ የደረሰኝ አዳማ ላይ የሮያል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በክብር እንግድነት ጋብዞኝ ባደረግሁት ንግግር ነው በወቅቱ ኢህአዴግ እንደሚለው “ልማት ያስፈልገናል፣ ልማት እንዲመጣ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል፣ ዴሞክራሲ እንዲመጣ የመብት ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል” አልኩ። አክዬም፤ “በኦሮሚያ ሠላም ስለሌለ እንደሌሎች አካባቢዎች ልማት እየተፋጠነ አይደለም፣ ይህ የሆነው ደግሞ ዲሞክራሲ ስለሌለ ነው” ብዬ ተናገርኩ፡፡ ከሁለት ሣምንት በኋላ ዳዊት ዮሐንስ ጠራኝና የኦሮሚያ ክልል ከሶሃል አለኝ፡፡ “ፖለቲካ ውስጥ እየገባህ ነው፤ ከአሁን ሰዓት ጀምሮ በዚህ ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ጥቅማ ጥቅምህን ታጣለህ” አለኝ፡፡ “የፈለከውን አድርግ፤ እኔ አቋሜን ከማራመድ ወደ ኋላ አልልም” አልኩትና ሄድኩ፡፡ በዚያው ውሣኔያቸውን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ እኔም ክስ መስርቼ፣ ከስሼ ሰበር ደርሶ ለእነሱ ተወሰነ፡፡
የሚሠጠኝ አበል፣ መኪና፣ ሠራተኞች፣ ቤት የመሣሠለውን አጣሁ እኔ አሁን ከፓርቲ ፖለቲካ በመውጣቴ በድጋሚ ጥቅማ ጥቅሜን አገኛለሁ የሚል ተስፋ የለኝም፡፡ ኢህአዴግ ይህን ካደረገ ተለውጧል ማለት ነው፡፡ እኔ ግን አሁንም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ መተቸቴንና መቃወሜን እቀጥላለሁ፡፡ ለኘሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በ4ዐዐሺህ ብር መኖሪያ ቤት መከራየቱን የሚተቹ ወገኖች አሉ? እርስዎ ምን ይላሉ? እኔም ከሚቃወሙት ወገን ነኝ፡፡ በዚህች ድሃ ሀገር ለምን ይሄ አስፈለገ? አንደኛ እኔ እንደሠማሁት ቤቱ 2ዐ ክፍሎች ነው ያሉት፡፡ አሁን በተሻሻለው ህግ ደግሞ ኘሬዚዳንቱ ከ3 እስከ 4 ክፍል ቤት ይሠጠዋል ነው የሚለው፡፡ በሀገራችን የድህነት ሁኔታ በ4ዐዐ ሺህ ብር ቤት መከራየት ያስፈልጋል ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ከሚያቀርቡት ወገን ነኝ፡፡ አሁን እርስዎ የሚተዳደሩት በምንድነው? እስከአሁን ድረስ ለኢኮኖሚ የሚጠቅመኝን ሥራ አልሠራሁም፡፡ ለፒኤችዲ የጻፍኳት መጽሃፍ አለች ከዚያች ትንሽ ገንዘብ አግኝቻለሁ፡፡ ከዚያ “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” ከሚለው መጽሃፌ ደግሞ ሩብ ያህሉን አግኝቻለሁ፡፡ ሌላው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲቋቋም፣ ዘመዶች አክስዮን ግዛ ብለውኝ በ4 ሺህ ብር የገዛሁት አለኝ፡፡ ከዚያ በስተቀር ምንም የኔ የምለው ሃብት የለኝም፡፡ ደምቢዶሎ ያለው የወላጆቻችን ቦታ ተወስዷል፡፡ እዚህም የራሴ የምለው ቤትም ሆነ ቦታ የለኝም፡፡ ከዚህ ከምኖርበት ቤትም ውጣ ብለውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አቤቱታ በማቅረቤ እስከአሁን ድረስ ዝም ብለውኛል፡፡ ግን በፈለጉ ጊዜ እንደሚወስዱት አውቃለሁ፡፡ ዋስትና የለኝም፤ በስጋት ነው የምኖረው፤ ቀጣይ መውደቂያዬንም አላውቀውም፡፡ ልጆችዎ የት ናቸው? ልጃችን አሁን የፊልም ትምህርቷን ጨርሳ ሎስአንጀለስ ውስጥ ሥራ እያፈላለገች ነው፡፡ ከቀድሞዋ ባለቤቴ የወለድኳቸው ደግሞ አንደኛው ጀርመን ሀገር ይሠራል፤ ሴቷ ደግሞ ለንደን ነው ያለችው፡፡

ልጅ ወልዳለች አሁን የእነሱ ጉዳይ አያሣስበኝም፡፡ እኔ አንድ ነገር ብሆን ባለቤቴ ምን ትሆናለች የሚለው ነው የሚያስበኝ፡፡ በቅርቡ በኢቲቪ በተላለፈ ዶክመንተሪ ላይ እርስዎና ሌሎች የአንድነት አመራሮች በ“ኢሳት” ጣቢያ ላይ ቃለ ምልልስ መስጠታችሁ ተተችቷል… ዶክመንተሪውን ተከታትየዋለሁ፡፡ የመጀመሪያው ላይ አሥራት ጣሴ፣ እኔ እና ዳንኤልን ነበር የሚያሳዩት ሁለተኛው ላይ እኔና ዳንኤል ኢንተርቪው ሰጥተዋል የሚል ትችት አቀረቡ ያቀረቡት፡፡ በቃለ ምልልሱ ምን እንዳልን ግን አላቀረቡም፡፡ ይህ እንግዲህ እነ ነጋሶ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላቸው ለማለት ተፈልጐ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ይህ የአሁኑ ሌላ የኘሮፖጋንዳ ሥራ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጨዋታ ጥሩ አይደለም፡፡ የትም አያደርሣቸውም፡፡ ቢተውት ጥሩ ነው፡፡ ለወደፊት እርሶ ምን ዓይነቷን ኢትዮጵያ ለማየት ይመኛሉ? መብትና ነጻነት የተከበረባት፣ ሁሉም የፈለገውን የሚያስብባትና ያሻውን አቋም የሚገልጽባት ኢትዮጵያን ባይ ደስ ይለኛል፡፡ ሰው በፈለገው መንገድ እየተደራጀ የፈለገውን ተቃውሞ በመንግስት ላይ የሚያቀርብባት፣ የፈለገውን ግለሰብ እና ፓርቲ የሚመርጥባት፣ዜጐች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ወሣኝ የሚሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት ምኞቴ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሙሉ ነጻነቱ ከተከበረለት፣ አቅሙን መጠቀም ይችላል፤ ያኔም ልማት ይመጣል፡፡ ይች ሀገር በተፈጥሮ ሀብት እግዚአብሔር የባረካት ነች፣ ይህን ተጠቅመን ድህነትን የምንቀርፍባትን ኢትዮጵያ እመኛለሁ፡፡
addis admas

No comments:

Post a Comment