Thursday, January 16, 2014

“የአንድነት ፓርቲ የመጪው ጊዜ ፈተና” – የመልስ መልስ ለአቶ ግርማ ካሳ እና ለመሰሎቻቸው – ከፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)


“የአንድነት ፓርቲ የመጪው ጊዜ ፈተና” በሚል ርዕስ ለጻፍኩት ጽሁፍ ስለሰጡት ምላሽ ከልብ አመሰግናለሁ። ሀሳቦችን በጨዋ መንገድ ማንሸራሸር ለእድገት ይጠቅማልና ሁላችንም ይልመድብን እላለሁ። ስለአንድነት ፓርቲ ተቆርቋሪ ሆነው የሰጡት መልስ ብዙም እንዳላረካኝ ስገልጽልዎ በከፍተኛ አክብሮት ነው። ማንም ጤናኛ ሰው በአገር ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋል። አንድነት ፓርቲ በዚህ እምነት የሚያደርገውን ትግልም አደንቃለሁ። ይሁን እንጅ የትግል ፍሬ መለኪያው ሂደት ሳይሆን ውጤት ነውና አንድነት ፓርቲ፣ ኢ/ር ግዛቸው ሊሄዱበት ባሰቡት መንገድ ከተጓዘ፣ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። እርስዎ በዚህ አስተያየት አልተስማሙም። አለመስማማትዎን ሁለት ቁምነገሮችን በማንሳት ለማሳየት ሞክረዋል፤ እኔም በእነዚህ ነጥቦች ላይ ተመስርቼ የመልስ መልስ አቀርባለሁ።

አንደኛ፤ አንድነት ፓርቲ፣ የአገሪቱ የህግ አካል የሆነውን ፣ የምርጫ ስነምግባር መመሪያው እስካሁን አለመፈረሙ ስህተት ነበር፣ አሁንም ፈርሞ ከኢህአዴግ ጋር መነጋገር አለበት የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል። የስነምግባር መመሪያውን ፈርመው ለድርድር ተቀምጠው የነበሩት የቀድሞው የመኢአድ ሊቀመንበር ኢ/ር ሃይሉ ሻውል በመጽሀፋቸው የተናገሩት ሰነዱን መፈረም ያዋጣል አያዋጣም የሚለውን ለማየት ይረዳናልና ልጥቀስ፤-

” ከኢህአዴግ ጋር ያደረግነውን ድርድር በተመለከተ አንዳንዱ ‘ ወደሰለጠነ ፖለቲካ ልንገባ ይሆን?’ ብሎ በደህና ሁኔታ ያየው ወገን ነበር። ሌላው ወገን ግን ‘እንዴት ያሰረውን ሰው ሄዶ እጅ ይጨብጣል’ የሚል ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምቷል። የ2002ቱን የምርጫ ስነምግባር ሰነዱን ስንፈርም ተቃውሞ እንደሚኖር ሳናውቅ ቀርተን አይደለም። ፊርማው ብቻውን ለእኛ ደስታን የሚሰጠንም ሆኖ አልነበረም።ሌላኛው አማራጭና አስተሳሰብ ግን ግብዝነትናን የሚያጠናክርና የሰላም ሂደትን የሚገታ ይሆናል የሚል ግምት መያዛችን አንዱ ምክንያታችን ነው። በወቅቱ እኛ ሰነድ መፈረማችን ለህዝብ ምን ፋይዳ አለው የሚለውንም በአግባቡ አይተነዋል። እኛ ያሰብነው ወረቀት ቢሮ ውስጥ ይፈረማል፣ ያልቃል የሚል ነበር። እነሱ ግን አምባሳደሮች ጋብዘው፣ ሚዲያዎችን ጠርተው የተለየ ዝግጅት አደረጉ። ነገሩን ለዓለም ለማሳወቅ መፈለጋቸው ለሁሉም ግልጽ ሆነ። በዚያን ወቅት እኛ የማናውቀው ውጥረት ነበረባቸው የሚል የዘገየ ግምት ተከሰተልኝ ። እኔ እንደሚመስለኝ የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች የመታዘብ ይሁንታ የሰጡት ያ ስምምነት ስለተፈረመ ይመስላል። መኢአድ ሰነዱን የፈረምንበት ዋናው ምክንያት ግን የ500 ስቃይ ላይ የነበሩ እስረኞችና የቤተሰቦቻቸው ሰቆቃ አሰቃይቶን ነው። እኔን በተመለከተ ኢህአዴግ ወደ እኛ አስገባነው ብሎ ቢያስወራም አልሰመረለትም።”

(ህይወቴና የፖለቲካ እርምጃየ፣ ሃይሉ ሻውል፣ ገጽ139)።

አቶ ግርማ እዚህ ላይ አራት ነጥቦችን ላንሳ። አንደኛው፣ አቶ ሃይሉ እንዳሉት የስነምግባር መመሪያው ለኢህአዴግ አለማቀፍ ተቀባይነትን ለማሰጠት ጠቅሟል። ቢያንስ የምርጫ ታዛቢ እንዲላክ አድርጓል። የታዛቢው የመጨረሻ ሪፖርት ባያምርም። ሁለተኛ አቶ ሃይሉ 500 ሰዎችን ከእስር ለማስፈታት ብለው እንጅ ሙሉ በሙሉ አምነውበት ሰነዱን አለመፈረማቸውን ገልጸዋል። ልብ ይበሉ አቶ ግርማ! ከ80 ሚሊዮን እስረኞች የተፈቱት 500 ዎቹ ብቻ ናቸው። 80 ሚሊዮኑ ህዝብ ከእስር እንዲፈታ ስንት የምርጫ ስነምግባር ፊርማዎችን መፈረም ይኖርብን ይሆን? ሶስተኛ ፣ መኢአድ ፊርማውን መፈረሙ ህዝቡ እንዲከፋፈል አድርጎታል። አንድነትስ ተመሳሳይ ነገር አይሰራም ብለው ያስባሉ? የሚከፋፈለውን ህዝብ አንድ ለማድረግ እርስዎ የህዝብ ግንኙነት ስራ ለመስራት ተዘጋጅተዋል? አይርሱ ፖለቲካ 50 በመቶው ገጽታ ( image) ነው። አራተኛ፣ ኢህአዴግ የፊርማውን ስነስርአት ለራሱ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተጠቅሞበታል። በድብቅ ይፈረማል የተባለውን ፊርማ ለአደባባይ አብቅቶታል። በአንድነት ላይስ እንዲህ እንደማይደረግ ምን ዋስትና አለ? በህዝቡ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ስሜትስ እንዴት ነው መቋቋም የሚቻለው?

ኢ/ር ሃይሉ ሻውል አያበቁም፣ ይቀጥላሉ ” በሌላ በኩል ከህዝቡ ወገን ደግሞ ” ሃይሉ ከዳን” የሚልም ነበር። ውጪ አገር ያሉትማ በኢንተርኔት ላይ ፎቶግራፌን እያገላበጡ እኔ ለቀድሞው ጠ/ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ እጅ እንደምነሳ አስመስለው ሲዘልፉኝ ከርመዋል።… የሰነዱ መፈረም ለ2002 ምርጫ ዝግጅት ለእኛ አባላት ትንሽ ፋታ ሰጥቷል። ገጠር ሲታገሉ የሰነበቱት እሳት ውስጥ ነበሩ፤ ከፊርማው በሁዋላ ለአጭር ቀናት ቢሆንም በመጠኑ ማስፈራራት ጋብ አለ።” ይሄ ፊርማውን በመፈረም የተገኘ ጥሩ ዜና ነው አቶ ግርማ። ግን ይቀጥል ይሆን ? እንመልከተው፦ ” ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ ግን ሁሉም ነገር ተረሳና ኢህአዴግ የተለመደ ጭቆናውን ማስፋፋት ተያያዘው… መኢአድ ከ2002 ምርጫ ጋር ተያይዞ ከኢህአዴግ ጋር የስነምግባር ደንቡን ከፈረመ በሁዋላ በኢህአዴግ በኩል የተገቡ ቃሎች ባለመተግበራቸው ከጋራ መድረኩ ራሱን አግልሏል። ኢህአዴግ ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር እንዲሆን ፈለገ። በመድረኩም እንነጋገር ብለን የምንጠይቀውን አጀንዳ አይቀበሉትም። የሄ ከሆነ የጋራ ስምምነት የምክክር አይደለም ብለን ተውነው። ስንመለከተው ኢህአዴግ ትእዛዝ የሚያስተላልፍበት መድረክ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ግንባታ ጸር እንጂ ጠቃሚ አለመሆኑን በገሀድ ታየ። ገዢው ፓርቲ በዚህ በጋራ መድረክ አባልነት የቀጠሩትን ፓርቲዎች ደመወዝ መሰል ድጎማ እየከፈለ በቁጥጥር ይዟቸው ቀጥሎአል።በ2002 የስነምግባር ደንቡን ብንፈርምም የእኛ አባሎች ላይ የሚደርሰው ወከባና እንግልት ከዚያ በሁዋላ እየቀጠለ መጣ…” ይሉና አቶ ሀይሉ ይቀጥላሉ…

አቶ ግርማ ካሳ እንግዲህ አንድነትንም ወደዚህ የአራዊቶች ጉባኤ ( ፋቡላ) በመክተት ፓርቲውን በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ሊያደርጉት እና ደሞዝ ሊያሰፍሩለት ያስባሉ ማለት ነው። ለአንድነት ፓርቲ ታጋዮች ካለኝ ከበሬታ አንጻር ፓርቲው በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር እንዲሆን አልመኝም። ወርሃዊ ደሞዝ እንዲሰፈርለትም አልሻም።ምክንያቱም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል የሚገድል ነውና ።

መድረክም አንድነትም ፊርማውን እስከዛሬ ባለመፈረማቸው የረባ ውጤት አላገኙ ይሆናል፤ ነገር ግን ” No to cheating!” በማለታቸው ከመኢአድ የተሻለ ክብር እና ድጋፍ አግኝተው እንደነበር አንዘነጋውም።

ሁለተኛው መከራከሪያዎ አቶ አንዱዓለምንና ናትናኤልን በተመለከተ የሰጠሁትን አስተያየት ተንተርሶ የቀረበ ነው። እኔ አንድነቶችን ከመከፋፈል ማዳን እንጅ፣ እነሱን የመከፋፈል አላማ የለኝም፣ በፍጹም!። ይሄን ስጽፍም ፓርቲውን ከመከፋፈል ለማዳን እንጅ ለሌላ አላማ አይደለም። ወ/ት ብርቱካን እስር ቤት ከገባች በሁዋላ ፓርቲዋ ( አመራሩ) ረስቷት ነበር። እንዴያውም አንዳንዶች “እንኳን ታሰረች” ሳይሉ ሁሉ አልቀረም። ያን ጊዜ ማን ነበር ለብርቱካን አብዝቶ የጮኸው? ዲያስፖራው እና በተለይ ኢሳት አልነበሩምን? የካናዳው ልጅ ተክሌ ” ብርቱካኔ ብረሳሽ ቀኜ ይርሳሽ” ብሎ ዜማ ያወጣላት አምስተርዳም የኢሳት ስቱዲዮ ውስጥ ሆኖ ነው። በወቅቱ የነበሩ ባልደረቦቼ ብርቱካንን በተመለከተ ብዙ ዝግጅቶችን ይሰሩ ነበር። ምንም እንኳ ኢሳት እዚህ ውስጥ እንዲገባ ባልሻም፣ “የኢሳቱ ባልደረባ” እያሉ ስለጻፉና በተዘዋዋሪም እኔ የጻፍኩትን የኢሳት አቋም አድርገው ለማሳየት ስለሞከሩ ትንሽም ብትሆን እውነቱን ለመናገር ይጠቅማል ብየ ስላሰብኩ ነው ኢሳትን መጥቀሴ። ( በነገራችን ላይ ኢሳት የግል አስተያየቴን እንዳልጽፍ እያደረገኝ ነው፣ በግሌ የምጽፈውን አንባቢዎች ” የኢሳት አቋም አድርገው ይወስዱብኝ ይሆን” እያልኩ በመስጋት፣ መጻፍ እየፈለኩ አልጽፍም፤ ለሀሳብ ነጻነት በሚታገል ድርጅት ውስጥ የምሰራ ሰው፣ በዚሁ ድርጅት መልሼ መታፈኔ ይገርመኛል፤ ያፈነኝ ግን ድርጅቱ ሳይሆን፣ ሰዎች ከድርጅቱ ጋር ያያይዙብኝ ይሆን የሚለው ፍርሀት ነው።)

አንዱዓለምና ናትናኤል የብርቱካን እጣ እንዲገጥማቸው አልሻም። በፓርቲው ሸውራራ አካሄድ ስነልቦናቸው እንዲጎዳም አልፈልግም፤ የስነምግባር ደንቡን መፈረም አንዱዓለምን እና ናትናኤልን ከእስር እንደያማያስፈታ አስረግጬ መናገር እችላለሁ። እነሱን የማያስፈታ ሰነድ ደግሞ ጥንቅር ብሎ ይቅር። አንዱዓለምና ናትናኤል በመረሳታቸው እጅግ ያንገበግበኛል። የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉና የገንዘብ መዋጮ የመሰብሰቡ ስራ እንኳ ቆሟል። ይሄ አልበቃ ብሎ በደንብ ባልተጠና የፖለቲካ አካሄድ ስነልቦናቸው ሲጎዳ አይቶ በሁዋላ ከመጸጸት አሁን የሚመስለንን መናገሩ ይጠቅማል እንጅ አይጎዳም።

እነ አንዱዓለም ያልመከሩበት ፖሊሲ በምንም ታዕምር ተግባራዊ መሆን የለበትም! አንዱዓለም የታሰረው ሮቢን አይላንድ አይደለም! ማማከር ይችላል። አንዱዓለም ” አይቃወምም ፣ ይስማማል” በሚል የሚቀርበው መከራከሪያ ብዙ መንገድ አይወስድም።

አንዱአያም አራጌ ” ያልተሄደበት መንገድ” በሚለው መጽሀፉ በገጽ 58 ላይ ስለ አምባገነኖች ባህሪ የጠቀሰው ትክክለኛ ነው እላለሁ ” የአለም ታሪክ እንደሚያሳየው አምባገነኖች በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸው ለቀው አያውቁም። እንደውም እነርሱ ስልጣን ከለቀቁ ሀገር እንደሚበታተን፣ ህዝብ እንደሚጨራረሽ የማስፈራሪያ ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ። ፈርተው ያስፈራሉ። ይሄ ባህሪያቸው መሆኑን መረዳትና ያለመዘናጋት መታገል ያስፈልጋል… ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ አሁን ያለውን አገዛዝ ለህዝብ ፈቃድ እንዲገዛ የግድ ማለት ያስፍልጋል።”


እኔ ነገ ስለሚሆነው ነገር ነው የምጽፈው፣ ትክክል መሆንና አለመሆኔን ለማየት ትንሽ ጊዜ መጠበቁ የሚሻል ይመስለኛል። ተሳስቼም ከሆነ ያን ጊዜ ሂሳቤን አወራርዳለሁ። ( በነገራችን ላይ አንድ ጊዜም እንዲሁ ሰማያዊ ፓርቲ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዱን በመቃወሜና ቀኑን እንዲቀይረው በመጠየቄ ብዙ ትችቶችን አስተናግጃለሁ፤ በሁዋላ ፓርቲው ( የእኔን ምክር ሰምቶ ይሁን አይሁን አላውቅም) ቀኑን ቀየረው፤ ለወረደብኝ ትችት ግን ሂሳቡን ያወራረደልኝ ሰው አልነበረም፤ ሲጽፉብኝ የነበሩ የማውቃቸው ሰዎች ሳይቀር ድምጻቸውን አጠፉ። እኔ ከተሳሳትኩ ሂሳቤን እንደማወራርድ ቃል እገባለሁ፣ ለመመጻደቅ ሳይሆን ለእድገት ይጠቅማል ብየ ስለማምን ነው።)

No comments:

Post a Comment