Friday, January 3, 2014

የአቦይ ስብሐት ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ


(ፋክት መጽሄት)
‹‹ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት ምን ማለት ነው? አፄ ሀይለስላሴ ከኢትዮጵያዊነት ወድቀዋል የሚል የለም፡፡ ኮሎኔል መንግስቱንም የሚል የለም፡፡ . . . ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት፤ በቃ በአጭሩ ኢትዮጵያዊ አለመሆን ነው፡፡ ሌላ ማንነት መገንባት (IDENTITY DEVELOP) ማድረግ ነው፡፡›› ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ኢትዮ-ምህዳር፣ ቅጽ 02፣ ቁጥር 47፡፡

ሀሳብን በመግለፅ ነፃነት እጅግ አድርጌ አምናለሁ፡፡ እንዲያውም ብዙዎች ‹የዲሞክራሲ መገለጫው ነፃ-ምርጫ ነው›፣ የሚሉትን ወረድ አድርጌ፣ ‹ዋናው የዲሞክራሲ መገለጫ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ነው›፣ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነፃና ዲሞክራሲያዊ የሚባለው ምርጫ በምስጢር የሚከናወን መሆኑ ነፃ ያለመሆኑ ማስረጃ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ግን እንደ ነፃ ምርጫ በምስጢር የሚደረግ አይደለም፡፡ በዚህ ተራ ምክንያት ነው ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ ከነፃ-ምርጫ የላቀ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ገላጭ ሆኖ የሚሰማኝ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሀገሬን ሳያት ‹ነፃ› ምርጫን ያህል፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት አልተሳካላትም፡፡ ለዚህ ነው ተቃማዊ ፓርቲ መስርተው በ‹ነፃ› ምርጫው ለመሳተፍ ከሚጥሩት የበለጠ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነትን ለማበረታታት ለሚውተረተሩት ልቤ የሚደነግጠው፡፡ ለአቦይ ስብሀትም የተለየ ግምት ያደረብኝ በዚሁ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ በ‹ነጻ› ምርጫ ቢያሸንፍም፣ የዲሞክራሲ መገለጫው ነፃ ምርጫ ነው ብለው አልተቀመጡም፤ ለሃሳብ ነፃነት መረጋገጥ ከፍተኛ ማበረታታት እያደረጉ ነው፡፡ በእድሜዬ፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል እንደ እሳቸው የሀገራችንን ሁለንተናዊ ሁኔታ አስመልክቶ በነፃነት (ሀሳቡን በሾመው መንግስት ሀሳብ ሳይቃኝ) የሚገልፅ አላጋጠመኝም፡፡ በዚህ የተነሳ ለአቦይ ስብሀት ትልቅ አድናቆት አለኝ፡፡
ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝም የአቦይ ስብሀት ህዳር 17፣ 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ተማሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ነው፡፡ እንደ ብዙዎቹ አወዛጋቢ የአቦይ ስብሀት አስተያየቶች፣ በዚህ ውይይት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡዋቸውን አስተያየቶች አንብቤና ግራ ተጋብቼ ብቻ ላልፋቸው አልፈለኩም፡፡ ጥያቄ አዘል አስተያየቴን ልሰነዝር ወደድኩ፡፡
መቼም ለረዥም አመታት ታግሎና አታግሎ፣ በታላቅ መስዋእትነት በተገኘ ድል፣ የተገኘ ስልጣን ይዞ፣ ሀገርና ህዝብ የሚመራ ሰው በጋዜጣና በመጽሔት፣ በሬዲዮና ቲቪ፣ በስብሰባና በአውደጥናት የሚጽፈውና የሚናገረው፣ ‹ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት አለ፤ ሀሳቤን ለመግለጽ አልፈራም› ለማለት ሳይሆን፣ የሚያስተላልፈው ቁምነገር ስለሚኖር ነው፡፡ ለመሆኑ የአቦይ ስብሀት የዩኒቨርሲቲው ንግግር፣ ወደፊት ሀገር ለሚረከቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚጠቅም፣ ምን ጠብ የሚል ቁም ነገር (ከእሳቸው የህይወት ልምድና የፖለቲካ ሰውነት አንፃር) አለው?፡፡
እንደ እኔ እምነት ማንም ባለስልጣን እንደሳቸው ቁምነገር ሲናገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ አንዱን እውነት ጠቅሼ ልሟገት፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የኤርትራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት አለው፡፡›› ብለዋል አቦይ ስብሀት፡፡ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ ወይም እንደኔ ተጽፎ ሲያነቡ፣ ውሸት ብለው ደንግጠው አዝነዋል፡፡ እኔ ግን እውነት ተናግረዋል እላለሁ፡፡ በእሳቸው (ምናልባም ደርግን ባስወገዱልን አብዛኞቹ ነፃ አውጪዎቻችን) አመለካከት የእኛ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነት ከኤርትራውያን ያነሰ ነው፡፡ በመሆኑም ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አላቸው የተባሉት ኤርትራውያን፣ ያነሰ ኢትዮጵያዊ ናችሁ ከተባልነው የበለጠ ኢትጵያዊ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዘመንና አጋጣሚ የመረቃቸው ኤርትራውያን በሀገራቸው ጥሩ ኤርትራዊ፣ በሀገራችንም ጥሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ እኛ እዚህ ኢትዮጵያዊ እዚያም ኤርትራዊ አይደለንም፡፡ ከኤርትራ ንብረታችን ተዘርፎ ስንባረር፣ የኤርትራ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያም መሪዎች ውሸት ብለው አላግጠውብናል፡፡ ለምን? እዚያ በኤርትራዊነት ስለሚበልጡን መሪዎቹ ዘርፈው አባረሩን፡፡ እዚህ በኢትዮጵያዊነት ስለሚበልጡን መሪዎቻችን አፊዘው ተቀበሉን፡፡ እውነቱን ብለዋል አቦይ ስብሀት! በመሪዎቻችን ሚዛን ኤርትራውያን በኢትዮጵያዊነት ይበልጡናል፡፡ ምን ኤርትራውያን ብቻ! ‹‹ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊያ፣ ለሱዳን፣ ለጅቡቲም፣ ለኤርትራም አትራፊ መሆን የእኛ የቤት ስራ ይመስላል፡፡›› ያሉት አቦይ ስብሀት ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሱማሌስ በኢትዮጵያዊነት ስለሚበልጡን አይደል! እንግዲያማ በኮረንቲ በቀን አስሬ መጥፋት እቃችን እየተቃጠለ፣ ቋት የገባ እህል ሳይፈጭ እያደረ፣ በየቢሮው ያለስራ እየተዋለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሱዳን ድረስ፣ የኮረንቲ መስመር ዘርግተው ለምረቃ ይሄዱ ነበር!
በቀደም በሳዑዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን መከራና ግድያ በሰላማዊ ሰልፍ እንዳንቃወም የተደረገው በመሪዎቻችን ሚዛን ኢትዮጵያዊነታችን ቀሎ በመገኘቱ ይመስለኛል፡፡ አቦይ ስብሀት እንዳሉት ከእኛ የበለጠ ኢትዮጵያዊነት ያላቸው ኤርትራውያን አዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቢጠይቁ ይፈቀድላቸው የነበረ ይመስለኛል፡፡ አቦይ ስብሀት እንዳሉት፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ሚዛን ከኤርትራውያን ቀለን ብንገኝ ተጠያቂው ማነው? የደርግን የአምባገነን ግፈኛ መንግስት ባንኮታኮተንበት ጀግንነት፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜታችንን ለማንኮታኮት የሚታገለው የኢህአዴግ መንግስት አይደለምን? ሀገርን ለማስተዳደር የተሰናዳን ህገ-መንግስት ሀገር ነው የሚሉ አንጋፋ ባለስልጣኖች የሚያስተዳድሩት ህዝብ ነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፡፡ እናም ዜግነቱ በሀገሩ ሳይሆን በህገ-መንግስቱ እንዲቀረጽ ይፈለጋል፡፡ ህገ መንግስታዊ እንጂ ሀገራዊ ዜግነት አይፈቀድለትም፡፡
አቦይ ስብሃት፣ ‹‹ሀገር ማለት ህገ-መንግስት ነው›› ብለዋል፡፡ ለምን አሉ? ህገ መንግስቱን ያስረቀቀውም፣ ያፀደቀውም ኢህአዴግ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ እስከዛሬ እንደታዘብኩት ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ፣ ባለስልጣናቱ እንደ ኢሊት ከ1983 ዓ.ም ቀድሞ የነበረ ሁሉ ነገር እርኩስ፣ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ያመጡት ሁሉ ቅዱስ ይመስላቸዋል፡፡ በአስራ ሰባት አመት ግፈኛ አገዛዝና በሶስት ሺህ ዘመን ሀገራዊ ቅርስና ታሪክ መካከል ያለው ድንበር የደበዘዘባቸው ይመስለኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ይመስለኛል ደርግን አሸንፎ መጣል፣ የቀደመውን እሴት ሁሉ የለመጣል ጋራንቲ የሚመስላቸው፡፡ በዚህ አስተሳሰብ የተነሳ የተቻለው ሁሉ ተለውጧል፡፡ አይለወጤ የሆነው (ሆኖ ያስቸገረው) ዜግነታችን ነው – ኢትዮጵያዊነታችን፡፡
ኢትዮጵያዊነታችንን ከሃያ አመት በፊት በተጻፈ ህገ-መንግስት ለመስፈር በአቦይ ስብሃት የተደረገው ድፍረትም ከዚሁ የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ውቅያኖስ ላይ ሃያ አመት ጠብታ ነው- ያውም የውሽንፍር፡፡ ኢትዮጵያዊነት እኮ እድሜው የትየለሌ፣ ጫፉ ብዙ ነው፡፡ ከንግስተ ሳባ ጋር እየሩሳሌም ድረስ፣ ከኦሮሞ ስደት ጋር ኬንያ ድረስ . . . ወዘተ. የሚዘረጉ ጫፎች ያሉት፣ ሁለንተናዊ ጥሪት ነው፡፡ ጉድፉ ሊነቀስ እንጂ ጨርሶ ሊገሰስ አይችልም፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያዊነት በአብዛኞቹ የአለም ሀገሮች (አቦይ ስብሀት እንደነገሩን ከኤርትራ በስተቀር) ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ዜግነት ነው፡፡ ለመሰደድ በየኮንቴይነሩ ታጭቀው፣ ታፍነው የሚሞቱት፣ በየበረሃው አሸዋ ጠብሶ የሚያስቀራቸው፣ በተሰደዱበት ሀገር ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ከጉሮሮ የማይወርድ መና ሰጥቶ፣ ሽፍል የማያረጥብ እንባ ረጭቶ ሬዲዮና ቲቪ ላይ አስጥቶ ለፖለቲካው ድርጎ የሚያውላቸው እንጂ፣ ከልቡ የሚረዳቸውና የሚሟገትላቸው መንግስት ያለን አይመስለኝም፡፡
አቦይ መቼም እርሶ ብቻ ሳይሆኑ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ ኢትዮጵያዊነታችንን ዝቅ የሚያደርግ (ስለ ባንዲራ፣ የአክሱም ሀውልት፣… ወዘተ.) ብዙ እንደተባለ ያውቃሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ፈተና ኢትዮጵያዊነት ሳይጠፋ በመቆየቱ ህዝቡ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ የሚገባው አይመስለኝም፡፡ ከተወቀስንም እንደ መንግስት ፍላጎት ኢትዮጵያዊነት ባለመሞቱና ባለመቀበሩ መሆን አለበት፡፡
ለመግቢያ በተጠቀምኩበት የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ አባባል እንደተገለፀው ንጉሱና ደርግ ስለኢትዮጵያዊነት አብዝተው አንዳንዴም አግንነው (ማጋነኑ ችግር ቢኖረውም) ያስተምሩ ነበር፡፡ ህዝቡ ከሁለቱ መንግስታት ስለሀገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ብዙ ተምሯል፡፡ በኢህአዴግስ? በኢህአዴግ መዝገበ ቃላት ውስጥ የሀገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት የተፃፉ አይመስለኝም፡፡ እና ሃያ አመት ሙሉ እኛ ኢህአዴግ በመዝገበ ቃላቱ ኢትዮጵያዊነትን እንዲጽፍ ስናሳስብ፣ ኢህአዴግ እንደ መዝገበ ቃላቱ ሁሉ፣ ከእኛም ጭንቅላት ሊያጠፋው ሲታገል – ስንጎሻሽም ሀያ አመት አሳለፍን፡፡ እንግዲህ እግዜር ያሳያችሁ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነትና ሃላፊነት ያላቸው (ቢያንስ የነበራቸው) አቦይ ስብሃት ስለኢትዮጵያዊነታችን ማነስ የሚወነጅሉን፡፡
ኢህአዴግ በሀገር ፍቅርና በኢትዮጵያዊነት ላይ ባራመደው አቋም ያተረፈው አለመታመንን ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ምስክሩ ደግሞ በምርጫ 97 በተለያዩ ቦታዎች፣ በቅርቡ በአክራሪዎች የደረሱ አደጋዎችን፣ አብዛኛው ህዝብ በመንግስት በራሱ የተፈፀሙ ናቸው፣ በሚል ጥርጣሬ መመልከቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በናይጄሪያ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እለት ስለደረሰው አደጋ በዚያው ሰሞን በኢቲቪ የቀረበ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ‹‹አንዳንድ ሰዎች መንግስት ነው ያደረገው ይላሉ፤ መንግስት እንዴት በገዛ ዜጎቹ ላይ ይህን ያደርጋል››፣ የሚል አስተያየት መሰንዘሩ ለዚህ የቅርብ እማኝ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ እንደመንግስት ኢህአዴግ ከኢትዮጵያዊነት ወድቋል፤ እንደ ታላቅ ታጋይና የፖለቲካ ሰው ደግሞ አቦይ ስብሀት ነጋ፡፡

No comments:

Post a Comment