Friday, January 3, 2014

ለ18 ዓመታት በስራ ላይ የቆየው ሕግ ሕገመንግስትን ይጥሳል ተባለ

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ መላኩ ፈንታ የኢትዮጽያ
ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ በሚኒስትር ማዕረግ ሆነው ሲሰሩ ስለቆዩ የተከሰሱበት
ጉዳይ መታየት ያለበት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ነው ወይስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚለው ጭብጥ ላይ
የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በሃላ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር
25/88 አንቀጽ 8-1 እና የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7-1
የህገመንግስቱን አንቀጽ 20-6 ይጥሳሉ ወይስ አይጥሱም የሚለው ነጥብ ሕገመንግስታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል
በማለት ለሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ለምክርቤቱ በመራው መሠረት ጉዳዩ የፌዴሬሽን ምክርቤትን አባላትን
በዛሬው ዕለት ለሁለት ከፍሎ አከራክሮአል፡፡
በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት የሕገመንግስት አጣሪ ጉባዔ ጉዳዩን መርምሮ እነመላኩ ፈንታ ያነሱት ጭብጥ
የህገመንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል በሚል ውሳኔ ካሳለፈ በኃላ ከትላንት በስቲያ እና በትናትናው ዕለት በምክርቤቱ
የሕገመንግስትና የክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የደረሰበትን የውሳኔ ሃሳብ በዛሬው ዕለት
ለፌዴሬሽን ምክርቤት አቅርቧል፡፡
በውሳኔ ሃሳቡ ላይ እንደተመለከተው የህገመንግስት አጣሪ ጉባዔ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 84 እና በአዋጅ ቁጥር
789/2005 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተመራለት የትርጉም ጥያቄ መርምሮ ሰዎች የመንግስት ባለስልጣን
በመሆናቸው ብቻ ከሌሎች ተለይተው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ክሳቸው እንዲታይ ማድረግ የህገመንግስቱን አንቀጽ
20 -6 ማለትም ይግባኝ የማቅረብ መብትን ስለሚጥስ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ወንጀል ድርጊት የተከሰሱ ሰዎች
መካከል አንዱ የይግባኝ መብት እንዲያገኝ ሌላው ይህን መብት እንዳያገኝ የሚፈቅድ ሕግ በመሆኑ፣ በተጨማሪም
የህገመንግስቱ አንቀጽ 25 ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው ፣በማናቸውም ሁኔታ በመከሰሳቸው ልዩነት አይደረግም
የሚለውን የህገመንግስት ድንጋጌ መጣስ ስለሚሆን የአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8-1 እና የተሻሻለው የጸረ
ሙስና ልዩ የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7-1 ድንጋጌዎች በሕገመንግስቱ አንቀጽ 9-1
ማለትም ሕገመንግስቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆኑን የሚያሳውን ድንጋጌ ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ያደርጋል በማለት የውሳኔ
ሃሳቡን አቅርቧል፡፡
በዚህ መሰረት ቋሚ ኮምቴው ከአጣሪ ጉባዔውና በጹሑፍ ከቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በተጨማሪ የጉባዔው አባላት ቀርበው
ለቋሚ ኮምቴው እንዲያስረዱ ተደርጎ ቋሚ ኮምቴው በጉዳዩ ላይ በቂ ውይይት ካደረገ በሃላ የውሳኔው ሃሳብ በአብላጫ
ድምጽ እንደተቀበለው ታውቋል፡፡
ምክርቤቱ ዛሬ በጉዳዩ ላይ በተወያየበት ወቅት ምክርቤቱን ለሁለት የከፈሉ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ በተለይ አቶ
መላኩ ፈንታ ያቀረቡትን ጥያቄ ትክክለኝነቱን በማረጋገጥ የተሟገቱ ወገኖች እንዳስረዱት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች
ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8(1) ባለስጣናት ከስራ ጋር በተገናኘ ወንጀል ፈጽመው ሲገኙ ጉዳያቸው
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚታይ እንደሚደነግግ፣ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7(1) በተመሳሳይ ሁኔታ
ይህንኑ ድንጋጌ እውቅና እንደሚሰጥ፣ በተለይ አዋጅ ቁጥር 25/88 ከወጣ 18 ዓመታት የቆጠረ መሆኑን በማስታወስ
በዚህ ሕግ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔን ጨምሮ ሌሎች ባለሰልጣናት ጉዳያቸው የታየበት እንደነበር
አስታውሰዋል፡፡
ሕጉ በወቅቱ ሲወጣ መንፈሱ ባለስልጣናት የሕዝብ ጥቅም በሚጎዳ ወንጀል ውስጥ ገብተው ሲገኙ
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ጉዳያቸው ብቃት ባላቸው የፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት ዳኞች እንዲታይ፣ጉዳዩም በአፋጣኝ እንዲታይ
በማሰብ መሆኑን በመግለጽ ይህ ሁኔታ በምንም መልኩ የህገመንግስት ጥሰትን አያስከትልም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
አዋጆች ሲወጡ ተመክሮበት፣የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ተሳትፈውበት እንደሆነ ያስታወሱት የምክርቤቱ
አባላት ይህ አንቀጽ ከሕገመንግስቱ ጋር ይጋጫል ሲባልም ሕግ አውጪው አካል ሕገመንግስትን የሚጻረር ሕጎችን
በዘፈቀደ ያወጣል የሚል መልዕክት ያለው አደገኛ ውሳኔ ነው ያሉ ሲሆን ስህተት ነው ከተባለ በዚህ ሕግ ለተጎዱ
ወገኖች ተጠያቂው ወገን ማን ነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጪም በ1988 ዓ.ም የወጣ ሕግ እስካሁን
ቆይቶ ሕገመንግስቱን የጣሰ ነው እያልን ነው ወይ ሲሉም በአግራሞት ጠይቀዋል፡፡ አንዳንዶቹም ጉዳዩ እንደገና ጊዜ
ተሰጥቶት ቢታይ ይሻላል የሚል ሃሳብ አንጸባርቀዋል፡፡
አዋጅ ቁጥር 25/88 እና አዋጅ ቁጥር 434/97 ውስጥ የሚገኙት አንቀጾች ከህገመንግስቱ ጋር እንደሚጣረስ
የውሳኔ ሃሳብ ያቀረበው ቋሚ ኮምቴ አባላት አንቀጾቹ የይግባኝ መብትን የሚያሳጡ፣ የሰዎችን በሕግ ፊት እኩል
የመሆን ሕገመንግስታዊ ድንጋጌ የሚጥሱ መሆናቸውን በመጥቀስ የእነመላኩ ፈንታን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል፡፡
ምክርቤቱም በዚህ ጉዳይ ከተወያየ በሃላ አንቀጾቹ ከሕገመንግስቱ ጋር ይጻረራሉ በማለት በመወሰን የእነመላኩን
አቤቱታ ውድቅ አድርጓል፡፡ በዚሁ ውሳኔ መሰረት የአቶ መላኩ ክስ በነበረበት ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ
ወንጀል ችሎት እየታየ የሚቆይ ይሆናል፡፡
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 22/2006 ባስቻለው ችሎት በእነመላኩ ፈንታ መዝገብ
ላይ የተነሳውን የሕገ-መንግስት ትርጓሜ ተጣርቶ እንዳልደረሰውና የፌዴሬሽን ምክርቤት ለታህሳስ 24 ቀን 2006
ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን በደብዳቤ እንደተገለጸለት፣ ውጤቱም ታውቆ ወደ ክርክር
ለመግባት እንዲያስችል የነብዩ መሐመድ ልደት(መውሊድ) በማይውልበት ጥር 5 ወይም 6 ቀን 2006 ዓ.ም በጉዳዩ
ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment