Wednesday, January 1, 2014

አይ የእኛ ነገር – የወገን ጩኸቱን አንቀማው (ነቢዩ ሲራክ)


ሰሞኑን ጠቃሚ መረጃ የምንለዋወጥባቸው ማህበራዊ ገጾቻችን በሙግት ንትርክ ማዕበል ተውጠው ተመለከትኩ … ከእምየ ምኒሊክ እሰከ በደሌ ቢራ ፣ ከድንቁ ትንታግ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ መግለጫ ፣ እርማት እስከተሰጠበት እንቁ መጽሔት ፣ ከታሪክ አዋቂው የሃገር ሽማግሌ ፕሮፊሰር ይስሐቅ የታሪክ ቀደምት ትንታኔ ታሪክ እስከ ማይጠቅመን የጁሃር መሃመድ ዘመቻ ሁሉም ሰሞነኛ ዝብሪት በየአይነቱ ሰማን ። ይህ ሁሉ ታዲያ በፈረንጆች አመት በዋዜማው ባይሆን ደስ ባለኝ! ይህም የእኛ ነገር ፣ የእኛ ኑሮ ነውና ምን ያደርጉታል?

ባለሁበት የሳውዲ ምድር በአለም እንደ ጨው የተበተንን የዚያች ሃገር ዜጎችን ትኩረት ሳቢ ብቻም ሳይሆን አስጨናቂ ቀንን ተፋጦ ማወጫ ያጣ ወገን ጩኸት ደምቆ እንዳይሰማ የእኛ ነገር አልተመቸውም ! ሌላው ቀርቶ ጥቂት “ያገባናል” ያልን መረጃን በቀላሉ እየተለዋወጥን በምንገኝባቸው ማህበራዊ ገጾች ከአንድ የአለም ጫፍ ወደ ሌላው የአለም ጫፍ በብርሃን ፍጥነት የሚሰራጨው የጥላቻ ፖለቲካ የመረጃ ቅብብል መተንፈሻ ፣ ጉዳታችን ለአለም መንገሪያ ሜዳችን እንዳያጨልምብን ሰጋሁ ! ከሁሉም የሚያሳዝነው የምንወዳቸውና የምናከብራቸው የተማሩ የተመራመሩት ወገኖቻችን ሳይቀሩ በዝብሪቱ አዙሪት ተጠልፈው መግባታቸውን እየታዘብን ነው ። …አዋቂዎች እንዳላዋቂ በማህበራዊ ገጾች የተበተነውን የጥላቻ መረጃ ከስርጭቱ ባህር እየጨለፉ ይረጩት ፣ እየተቀባበሉ ያጎኑት ይዘዋል ። እንዲህ እየሆነ …አንዱ ያሰራጨውን እነርሱም ተቀባብለው የታላቅነታቸው መገለጫ የሆነች አስተያየታቸውን ሞነጫጭረው አሳለፈው ይለጥፉ የጥላቻውን መርዝ ይነሰንሱት ይዘዋል ! የማይጠቅም የማይበጀንን … አይ …የእኛ ነገር!

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ያለው ወገናችን ወገናቸው ዛሬም አደጋ ላይ መሆኑን የረሱት ይመስላል ። በጅዳ የሽሜሲ መጠለያ ፣ በጅዳ አየር መንገድ ፣ በጅዳ፣ በጀዛን እና በሪያድ እስር ቤቶች በወህኒው እንግልት ፣ በኮንትራት መጥተው በአረብ አሰሪዎቻቸው ገወፍ የሚፈጸምባቸው ፣ ወደ ሃገር እንዳይገቡም ሆነ የፈለጉትን እንዳያደርጉ እንደ ግዞት የተያዙ በርካታ የጨነቃቸው ወገኖች ፣ የአረብ ቤት አጽድተው ባጠራቀሟት ገንዘብ ወደ ሃገር የላኩት እቃ በአንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገዳችን ካርጎ ለበርካታ ወራት ከሳውዲ ግልጋሎት መስጠት መቋረጥ የተበላሸባቸው ለኪሳራ የዳረጋቸው፣ ከአስርት አመታት በላይ በስደት ቆይተው ወደ ሃገር ሲገቡ የተገለገሉበትን እቃም ሆነ መደራጃ የምትሆን እቃ ይዘው ለመግባት የተቸገሩት እና በመሳሰሉት በድንገተኛ የስደት ኑሮ ውጣ ውረድ ድቀት ማዕበል የተመቱ ወገኖች ጩኸት እዚህም እዚያም ተበራክቷል … ! ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ከባቢ ያለን ወገኖች ከአፍንጫችን ስር ያሉትን ወገኖቻችን በሰላም ወደ ሃገር የሚገቡበትን መንገድ ከማፈላለግ ባለፈ አነሰም በዛ በዚህ ክፉ ቀን በወገን ድጋፍ የተሰማሩ ወገኖችን ስም እያነሳን ከመደቆስ ፣ የክፋት ፣ የጥላቻ መርዛችን በመርጨት ብቻ ሳይወሰን በአለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያውያንን ስራ ባላስፈታው የጥላቻ ፖለቲካ ተጠልፈናል ። የዝብሪቱን መረጃ እየተቀባበልን የመረጃ መቀበያ ማህበራዊ ገጻችን ማጉደፍ ይዘናል ! አይ ! የእኛ ነገር …

የእኛ ነገር እንዲህ ቢሆንም ፣ እንዲህ ሆኖ መቀጠል የለበትም ! ዛሬ ፋታ የማይሰጥ የወገን ጭንቀት ሊያስጨንቀን ፣ ህመሙ ሊያመን ፣ ቁስሉ ቁስላችን ፣ ሞቱ ሞታችን ሊሆን ይገባል ! ይህን ማድረግ ባይቻለንና በእውን ያሰብነው ተሳክቶ ፣ ግፉኡን ወገን ልንታደገው ባይቻለን ጩኸቱ እንዳይሰማ ግርዶሽ የሚሆነንን የጥላቻ ፖለቲካ አንከተል ! የክፊዎች ጭራ አንሁን ! እየተረጨ ያለውን ሰሞነኛ ዝብሪቱን እኛም ተቀብለን ትንታኔ ፣ ወግ እያሳመርን መርዙን መረጃ እያሽከረከርን የደማችን ከፋይ የወገናችን ጩኸቱን አናፍነው ! የወገናችን ጩኸቱን አንቀማው !

ሌላ ምን እላለሁ …

እስኪ እሱ ይታረቀን !

No comments:

Post a Comment