Wednesday, January 1, 2014

በኢትዮጵያ የተወሰኑ የቻይና ኩባንያዎች ከባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ስራ እየከለከሉን ነው ሲሉ 18 የቻይና ኩባንያዎች አመለከቱ

January 1/2014ሪፖርተር ባወጣው ዘገባ 18 የቻይና ኩባንያዎች ቤጂንግ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በላኩት ደብዳቤ ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የቻይና ኩባንያዎች ከአንዳንድ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ስራ እንዳናገኝ እንቅፋት ፈጥረዋል ብለዋል።
ኩባንያዎቹ የተሰማሩባቸው መስኮች የኃይል፣ የመስኖ፣ የመንገድና የንፁህ የመጠጥ ውኃ ግንባታዎች መሆናቸውን የዘገበው ጋዜጣው፣ በእነዚህ የመሠረተ ልማት ዘርፎች የተሰማሩት የቻይና ኩባንያዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰኑ ባለሥልጣናት ቀደም ብለው ለገቡ የቻይና ኩባንያዎች ያለ ውድድር ሥራ እንደሚሰጡዋቸው፣ ደካማ የሥራ አፈጻጸም እያለባቸውም አንዱን ሥራ ሳይጨርሱ ተጨማሪ ሥራዎችን በላይ በላዩ ይሰጧቸዋል የሚል ቅሬታቸውን ዘርዝርው ለመንግስት አቅርበዋል።


ጥቂት ነባር የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ገንዘብ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን የመያዝ እንዲሁም ከቻይና መንግሥት በሚገኝ ብድር የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን የመቆጣጠር አዝማሚያ እያሳዩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ነባር ኩባንያዎች ሥራዎችን የሚያገኙት ከተወሰኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ነው የሚሉት አዲሶቹ ኩባንያዎች፣ ለሌሎች ኩባንያዎች ክፍት ሳይደረግ በቀላሉ በቢሊዮን የሚቆጠር ዋጋ ያለው ሥራ እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት አንዳንድ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ቻይና ኤምባሲ ውስጥ ቦታ ያላቸው ግለሰቦችም ለተወሰኑ የቻይና ኩባንያዎች እንደሚያዳሉ ያስረዳሉ ሲል ዘገባው ጠቅሷል፡፡
ሌሎቹን በመግፋት የተወሰኑትን የሚተባበሩ በመሆኑ ብዙኃኑ የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ማግኘት እንዳይችሉ መደረጉንም በመግለጽ መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያጣ ከመደረጉም በላይ፣ ተስፋ የተጣለባቸው ፕሮጀክቶች ደካማ አፈጻጸም ባላቸው ኩባንያዎች እጅ እየወደቁ እንደሚገኙ ተገልጿል።


አዲሶቹ ኩባንያዎች እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡት አብዛኞቹ የቻይና ኩባንያዎች አነስተኛና መለስተኛ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ጉዳዩን የቻይናና የኢትዮጵያ መንግሥታት ተረድተው መፍትሔ እንዲሰጧቸው አዲሶቹ ኩባንያዎች ጠይቀዋል።
ዘገባውን ተከትሎ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ታደሰ ብሩ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነቡ በጥራት ጉድለት ምክንያት ለሚፈርሱት መንገዶችና ህንጻዎች ከቻይና ኩባንዎች በላይ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ናቸው ብለዋል። ዘገባው በከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና በቻይና ኩባንያዎች መካከል ያለውን የሙስና ትስስር ያሳያል በማለት ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል

ኢሳት

No comments:

Post a Comment