Wednesday, January 1, 2014

“አንድነት” ከ1ሺ በላይ የቁጫ ነዋሪዎች መታሰራቸውን ተቃወመ


ፓርቲው ዛሬና ነገ አዲሱን ፕሬዚዳንት ይመርጣል
በደቡብ ክልል፣ በጋሞ ዞን በቁጫ ወረዳ፣ ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከ1ሺ በላይ ነዋሪዎች መታሰራቸውን “አንድነት” ፓርቲ ተቃወመ፡፡ በቁጫ ማህበረሰብ ላይ የሚደርሰው የመብት ረገጣ እንዲቆም ለማሳሰብ ሰላማዊ ሰልፍ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ከትላንት በስቲያ ፓርቲው በፅ/ቤቱ “የቁጫ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው የዜጎች መብት ሲከበር ነው” በሚል በሰጠው መግለጫ፤ በቁጫ ወረዳ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሚመራ ቡድን ወደ ሥፍራው በመላክ መረጃ ካሰባሰበ በኋላ፣ በወረዳው ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት መርምሮ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቁሟል፡፡ በፓርቲው ብሄራዊ ኮሚቴ ፀሀፊ እና የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል በአቶ ትእግስቱ አወል የተመራው ቡድኑ፤ በቁጫ ለአራት ቀናት ባደረገው የመረጃ ማሰባሰብ ስራ 1015 ሰዎች በሰላም በር ፖሊስ ጣቢያ፣ በአርባ ምንጭና በጨንቻ ወህኒ ቤቶች እንደታሰሩ ማረጋገጡ ተገልጿል፡፡ ህዳር 14 ቀን 2006 ዓ.ም አቶ ዛራ ዛላ የተባሉ የሁለት ልጆች አባት፣ ኮዶ ኮኖ በተባለ ቀበሌ ውስጥ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉን የገለፁት የቡድኑ መሪ፤ አባወራው በጥይት ሲመቱ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ የስጋት ሳንታ፣ የገዢው ፓርቲ የወረዳው ድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ አሸብር ደምሴ እና የወረዳው የፀጥታ ሀላፊ አቶ አያኖ መለና በስፍራው እንደነበሩ ከአይን እማኞች መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
የወረዳው ህዝብ በአካባቢው ምንም አይነት ልማት ባለመካሄዱና በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲሳተፍ ዕድል ባለማግኘቱ፣ በቁጭት የማንነትና የመብት ጥያቄ ማንሳቱን የገለፁት አቶ ትዕግስቱ፤ ይሄን ተከትሎም የመብት ረገጣና የማፈናቀል ተግባር እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል፡፡ የፓርቲው የብሄራዊ ም/ቤት አባል፣ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊና የደቡብ ቀጠና ሀላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በበኩላቸው፤ “የወረዳው ህዝብ ተወላጅ እንደመሆኔ የአካባቢውን ህዝብ እንግልትና የመብት ጥሰት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ” ካሉ በኋላ፤ የመብት ጥሰቱ እንዲቆም የአካባቢው ሽማግሌዎች ጠ/ሚኒስትሩን ለማነጋገር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ሰሚ በማጣት መመለሳቸውን ተናግረዋል።
“በህዝቡ ላይ በሚደርስበት እንግልት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መፍትሄ ለማፈላለግ እንቅስቃሴ ሳደርግ ከአካባቢው ባለስልጣናት ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብኛል” ብለዋል-አቶ ዳንኤል፡፡ የመብቱ ጥሰቱ እንዲቆም መንግስት እርምጃ መውሰድ አለበት ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ይሄ ካልሆነ ግን ፓርቲያቸው በቁጫ ወረዳ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ማቀዱን ገልፀዋል፡፡ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊና የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት በክልል ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም መባባሱን ጠቅሰው፤ ዛሬና ነገ ፓርቲው ለጠራው ጠቅላላ ጉባኤ አዳራሽ ለማግኘት ብርቱ ፈተና እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡
የልኡካኑ መሪ አቶ ትዕግስቱ አወልን ጨምሮ ሰባት አባላት በአካባቢው ባለስልጣናት “አፍራሽ ተልዕኮ ይዛችሁ መጥታችሁ ስለሚሆን እንጠረጥራችኋለን” ተብለው ከአራት ሰዓታት በላይ መታሰራቸውን ገልፀዋል፡፡ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ልዑካን ባቀረቡት ሰፊ ሪፖርት ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ፓርቲው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ “በቁጫ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ረገጣ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ ወገን እንዲቋቋምና እንዲጣራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወስን፤ ቁሳዊ፣ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጐች የሞራል ካሳ እንዲከፈላቸው፣ የቁጫ ወረዳ ተወላጅ በሆነው የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር ላይ እየደረሰ ያለው ማሳደድና ማዋከብ በአስቸኳይ እንዲቆም” ሲል በአቋም መግለጫው የጠየቀው ፓርቲው፤ ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት ተቃውሞውን እንደሚገልፅ አስታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርቲው ዛሬና ነገ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን፣ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርትን የሚያዳምጥ ሲሆን የውሳኔ ሃሳቦችንም እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ፓርቲው በሁለቱ ቀናት ጉባኤ አዲሱን ፕሬዚዳንት እንዲሁም የምክር ቤትና የኦዲት ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን እንደሚመርጥ የተገለፀ ሲሆን የፓርቲውን ፕሮግራምና ደንብ የማሻሻያ ረቂቆች መርምሮም እንደሚያፀድቅ ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment