Tuesday, January 14, 2014

የመረጃ ነፃነት ?…

January 13/2014


ይድነቃቸው ከበደ
ማስታወሻ፡- ይህ ፁሁፍ በግል የቀረበ እንጂ በሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሃላፊነቴ አለመሆኑ ይታወቅልኝ በመሆኑም ስሜ ብቻ ይገልፅ ፁሁፉ ለእናተ በቂ መስሎ ከታያችሁ፡፡

ከከበረ ሠላምታ ጋር መልዕክቴ ይድረሳችሁ!!!!


‹‹ ሕዝቡ እኔ ማን እንደሆንሁ ይላል ? ›› በማለት እየሱስ ክርስቶስ መረጃ ይጠይቃል ፤ ደቀመዛምርቶችም ስለሱ የተባለውን አንድም ሳያስቀሩ ይነግሩታል፡፡ እሱም መልሱ እንዲህ ይላቸዋል ‹‹ እናንተስ እኔ ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ ? ››አላቸው ፡፡ እነሱም መለሱለት፡፡ ሙሉ ታሪኩ ሉቃስ 9ቁ 18 ላይ ይገኛል ፡፡

መረጃ አይናቅም አይደነቅም ማለት እንዲህ ነው፡፡ በመሰረቱ ክርስቶስ ሰዎች ስለሱ ምን እንዳሉ ብቻ ሳይሆን ምን እያሰብ እንደነበር የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ ግን መጠየቅ እና መመለስ አሳብን መግለፅ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶ እንደሰው በምድር በተመላለሰበት ወቅት መረጃ ይጠይቅ የነበረው እሱም ስለራሱ መረጃ ይሰጥ የነበረው፡፡ እርግጥ ነው ክርስቶስ ይህን ሲጠይቅ የራሱ ምክንያት አለው፡፡

በመሆኑም ሃሳብ መግለፅ ተፍጥራዊ መብት ነው ወደሚለው ዓለም አቀፍ ስምምነት በመደረሱ የመናገር ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት የዲሞክራሲ ዋና የድም ስር ነው የተባለው፡፡ ስለዚህም ተሰባስቦ መቃወም እንዲሁም መደገፍ ፣ አንድ ሰው የሚመስለውን ሃሳብ በፈለገው መንገድ መግለፅ፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ መንግስትን የመተቸት፣ በራስ ፍቃድ የመናገረ እና ያለመናገር ፣ በዓልንና አይማኖትን መከተልና ማስፋፋት እንዲሁም ህግ ለሁሉም የሚሰራ ስለመሆኑ መረጋገጥ እና የመሳሰሉት ሁሉ ተግባራዊ የሚሆነው ተአቅቦ ያልተደረገበት የመናገርና የመረጃ መብት ልውውጥ ተግባሪዊ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ለመደርደሪያነት የዚህን ያኸል ከተባለ ወደ ዋናው ጉዳይ አስፈቅደን ሳይሆን ፈቅደን እንገባለን፡፡ ያነሳነው አሳብ ‹‹ መረጃ ›› እንደመሆኑ መጠን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ተፍጥሯዊ መብታችን በፈለግነውና በፈቀድነው መንገድ እንገልፃለን፡፡ እኛ ስል ለመረጃ ነፃነት የቆምነው ሁላችንም ማለቴ ነው፡፡

ሰው በመናገሩ አና በመፃፉ ብቻ ለእስር እና ለስደት የሚዳረግበት አገር በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዶ ናት፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የመግለፅ ነፃነት አለው፡፡የሚለው በኢትዮጵያ ህገመንግስቱ አንቀፅ 29 ተፅፎ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ይህ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል በህገ መንግስቱ ላይ ተገልፆ የተቀመጠ ሲሆን ገደብ ግን መሠረታዊ የሆነውን መረጃን የመስጠት እና የማግኘት እንዲሁም አስተሳሰብ ላይ ወይም አመለካከት ላይ ውጤት እንደማይኖረው በህገመንግስቱ ተገልፆ ይገኛል፡፡


ይሁን እንጂ አሳብን በነፃ ማሰብና ማንሸራሸር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አዳጋች ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ አልፎ ተርፎ በአስተሳሰብ ወይም በአመለካከት ላይ ተፅኖ እስከመፍጠር ተደርሶኦል ፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ለህግም ሆነ ለሞራል ተቃራኒ እንደመሆኑ መጠን የፈጀውን ፈጅቶ ወደነበረበት መመለሱ የማይቀር ሃቅ ነው፡፡ ነፃ አሳብ የሚንሸራሸርባቸው ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ምን ያህል አሉ ? ያሉት ጋዜጦች እና መፅሔቶች እየደረሰባቸው ያለው ማስፈራሪያና ዛቻ ደረጃው ምን ያኸል ደርሶአል የሚለውን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አክራሪነትና ፅፈኝነት የሚያበረታቱና የሚያሰራጩ በማለት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለህዝቡ ተገቢውን መረጃ እያስተላለፉ ያሉ የእትመት ውጤቶችን ከገቢያ ለማውጣትና ፈርጆ ለመክሰስ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ሌላው ማሳያ ነው፡፡ጋዜጠኞችን በማሰቃየት፣በማሰር እና እንዲሰደዱ በማደረግ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በሁለተኝነት ደረጃ ላይ ትገኛለች ፡፡መንግስትን ተችቶ የፃፈና ፁሁፉ የወጣበት ጋዜጣ ወይም መፅሔት ጨምሮ ሁሉም ለእስር የሚዳረግበት ወይም አደገኛ ዛቻና መስጠንቀቂያ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

በዲሞክራሳዊ ሥርዓተ ዜጎች የሚኖሩት ግልፅ በሆነ የሃሳብ ልውውጥ ነው፡፡ የትኛውም አይነት ሃሳብ ከማንም ሊመጣ ይችላል ቁም ነገሩ መሆን ያለበት የሚመጣው ሃሳብ የሚመከተው በምንድነው የሚለው ነው፡፡ ለነፃ ንግግር ችግር የተሻለው መንገድ የበለጠ ነፃ ንግግር ነው፤ በመናገር መብት ላይ የሚደረግ ማናቸውም ተፅእኖ ሲውል ሲያድር በእያንዳንዱ ግለሰብ የመናገር መብት ላይ ስጋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ለዚህም ነው ወደነበረበት መመለሱ የማይቀር ነው ለማለት የሚያስደፍረው፡፡ምክንያቱ ደግሞ ማንም ሰው በስጋት ውስጥ መኖርን ስለማይፈልግ ነው፡፡

በመሆኑም በአገራችን እየከሰመ ያለው ሃሳብን በነፃ የመግልፅ እና መረጃ የማግኘት መብት በገዥው መንግስት መልካም ፍቃድ ላይ የተመሠረት ወደመሆን ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ለዚህም እንደማሳያ ከሰሞኑ የህዝብ ሳይሆን የገዥው መንግስት አንደበት በሆነው በኢቲቪ በተላለፈው የዘጋቢ ፊልም ግለሰቦችም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይ ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲ ለኢሳት መረጃ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ምክር መሰል ማስጠንቀቂያ ተላልፏል፡፡

ለዚህም እንደምክንያት የቀረበው ኢሳት የተባለው የመገናኛ ብዙሃን በሽብርተኛ ድርጅት የሚደገፍ ነው የሚል ምክንያት ነው፡፡ ኢቲቪ በኢህአዴግ እንደሚደገፍ ሁሉ ኢሳት በማንም ሊደገፍ ይችላል፤ ቁም ነገር ሆኖ መታየት ያለበት ኢቲቪ ሆነም ኢሳት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድነው ፡፡ በተጨማሪ መልዕክቱ ለህግም ሆነ ለሞራል ምን ያኸል ተቃራኒ ነው የሚለውን ነው፡፡ በተጨማሪ ኢቲቪ እንዲሁም ኢሳት በህግ መደመጥ እንዲሁም መሰማት የተከለከሉ የመገናኛ ብዙሃን ናቸው ወይ ተብሎ መጠየቅና መልስ ሊሰጥባቸው የሚገባ አሳቦች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ወደ መልሱ ስናመራ ኢቲቪ እንዲሁም ኢሳት በህግ የተከለኩ አይደሉም ዋንኛው እና አስፈላጊው ነገር ይሄ ነው ሌላው የህጉ ደጋፊ ሃሳብ ነው፡፡

በመሆኑም ከዚህ በኋላ የህግ ጉዳይ ሳይሆን የፍላጎት ምርጫ ነው የሚሆነው፡፡ የፈለጉትን መስማት እና ማዳመጥ እንዲሁም በፈለጉት የመገናኛ ብዙሃን መንገድ ሃሳብን መግለፅ እና መረጃን ማግኘት ግለሰብ ከሆነ እንደግለሰቡ፣ ተቋም እንደተቋም እንዲሁም ፓርቲ እንደ ፓርቲ የመምረጥ የራስ መብት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንዱ የዲሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኢቲቪ ኢሳት ከአዲስ ዘመን አዲስ አድማስ የዝወትር ፍላጎታቸው ለሆነ እንዲሁም በተመሳሳይ ከኢሳት ኢቲቪ ከአዲስ አድማስ አዲስ ዘመን ለመረጡ ምርጫቸውን ማክበረ ነው፡፡

ሌላው እና አሳሳቢ ሊሆን የሚገባው ሰው የመረጠውን መስማትና ማዳመጥ እንዲሁም ማንበብ መብቱ እንደጠጠበቀ ሆኖ ግለሰበ ወይም ተቋም ሃሳቡን እንዴት የመግለፅ መብት እና ግዴታ አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ተቋም ወይም ግለሰብ ሃሳብን ወይም መረጃን በማንኛውም መንገድ የመገልፅ ሙሉ መበት በህግ የተጠበቀ ነው ፡፡እንዲኹም የዚህ መብት ተቃራኒ የሆኑ ማናቸውም ነገሮች ተቀባይነት እንደሌላቸው በህገመንግስቱ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት በኢሳት ሆነ በማናቸውም የመገናኛ ብዙሃን ሃሳብን መግለፅ እና መረጃን መስጠጥ በራሱ ወንጀል ወይም ጥፋት አይደለም ይህ የሆነው ደግሞ መብት ከመሆኑ አንፃር ነው፡፡


ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሃሳብን በመግለፅ እና መረጃን በመስጠት ዙሪያ ግዴታ ሊያመጣ የሚችለው ምንድነው የሚለው ነው፡፡ ግለሰቡ ወይንም ተቋሙ በግልፅ በህግ የተከለከለ መረጃ ወይም ሃሳብ የገለፀ እንደሆነ ግዴታው ተጠያቂነትን ስለሚያመጣ በህጉ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይህ የህግ ተጠያቂነት አዱላዊነት የሌለበት ለሁሉም በሁሉም ቦታ እኩል የሚሰራ ነው፡፡ ይህም ማለት በህግ የሚያስጠይቅ ንግግር በኢሳትም ሆነ በኢቲቪ እንዲሁም በቢቢሲ ያደረግ በህግ ከመጠየቅ ንግግር ያደረገበት የብዙሃን መገኛኛ ሊታደገው አይችልም እንደማለት ነው፡፡
በመሆኑም በኢሳት ሃሳብን መግለፅ እንዲሁም መረጃ መስጠት አልፈልግም ማለት መብት ነው፡፡ ነገር ግን በኢሳት አሳባችሁን አትግለፁ መረጃም አትስጡ ማለት ከፍላጎት የመነጨ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የለየለት የእብሪት ተግባር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ አሰፋሪ ምኞት እና ተግባር የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ተምሮ ያለመለወጥ ልክፍትም ጭምር ነው! በተለይ በመንግስት ደረጃ ሲታሰብ እጅግ በጣም ያሳፍራል፡፡
 ዘ-ሐበሻ

No comments:

Post a Comment