Thursday, January 16, 2014

“ወሬ አይደለም፤ አገር ቤት አንገባለን” ሌንጮ ለታ ..


ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ “መረጃ የለኝም”
odf lencho

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ከፍተኛ አመራርና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ አዲስ ያቋቋሙትን ድርጅት ይዘው አዲስ አበባ እንደሚገቡ አስረግጠው ተናገሩ። አቶ ሌንጮ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ገብቶ ለመታገል መወሰኑ ለምን ወሬ እንደሚባል እንዳልገባቸውም አመላክተዋል። በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ኢትዮጵያ መግባታቸውን ኦነግ እንደሚቀበለው ተጠይቀው “ኦነግን ጠይቅ” በሚል ጠበቅ ያለ መልስ ሰንዝረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሌለው አመልክቷል።
ጥር 5 ቀን ከጀርመን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ሌንጮ “ኖርዌይ ተቀምጠን ምን እናደርጋለን? ሃገር ቤት ገብተን እንታገላለን” ሲሉ ወደ አገር ቤት ለመመለስ መወሰናቸውን ግልጽ አድርገዋል። “ይሳካል?” በማለት ጠያቂው ላቀረበው “ይሳካል አይሳካም ተብሎ ወደ ትግል አይገባም” በማለት አቶ ሌንጮ ማምረራቸውን በሚያሳብቅ ሁኔታ መልስ ሰጥተዋል።
ህወሃት የዘረጋውን የፌዴራል ሲስተም እንደሚቀበሉትና የኦሮሞ ህዝቦች ጥያቄም በዚያው ውስጥ ሊመለስ እንደሚችል ያመለከቱት አቶ ሌንጮ፣ “በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ የተመሰረተ ሳይሆን በህግና በህገመንግሥት በተደነገገ የህዝቦች አንድነት እናምናለን” ብለዋል። የግለሰብ መብት ከብሔር መብት መቅደም አለበት፣ የብሔር መብት አስቀድሞ ሊከበር ይገባዋል በሚል ሁለት አቋም ከሚያራምዱት የተለየ ፕሮግራም እንዳላቸውም አቶ ሌንጮ አስታውቀዋል። የግለሰብም ሆነ የቡድን መብት መከበር አለበት የሚል ፕሮግራም ያለው አዲሱ ድርጅታቸው በዚህ አቋሙ ከሌሎች እንደሚለይ አመልክተዋል።
በምርጫ የመሳተፍን ጉዳይ አስመልክቶ የእሳቸው ድርጅት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ምርጫ ቢገቡ ፍላጎታቸው መሆኑንን አቶ ሌንጮ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከምርጫ በፊት ብዙ ጥያቄዎች እንዳሉ አመልክተዋል። ዴሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፈት ምርጫ ብቻውን መፍትሔ እንዳልሆነም ጠቁመዋል። ህዝብን አገር ቤት ገብቶ ማስተማር፣ መቀስቀስና ማብቃት በዋናነት አስፈላጊ እንደሆነም አስምረውበታል።
ከኢህአዴግ ጋር ድርድር ስለማድረጋቸው ለተጠየቁት፣ እስካሁን የተደረገ ድርድር እንደሌለ አቶ ሌንጮ ጠቁመዋል። አያይዘውም ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋርም የመደራደር እቅድ እንዳላቸው አመልክተዋል። አቶ ሌንጮ በተደጋጋሚ አገር ቤት መሄዳቸው መገለጹንም በማንሳት አስተባብለውታል። አቶ ሌንጮ ድርድር ስለመደረጉ ባያምኑም በተለያዩ ጊዜያት በኖርዌይና በተለያዩ አገራት ከኢህአዴግ መልዕክተኞች ጋር አሁን ይፋ ባደረጉት ጉዳይ ዙሪያ መነጋገራቸው መዘገቡ ይታወሳል። ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣም በቅርቡ ኢህአዴግ ብሔር ተኮር ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑንና ከሌሎች ማናቸውም ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ሃሳብ እንደሌለው ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡይታወሳል።
አቶ ሌንጮ የሚመሩት ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት መወሰኑን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ “መረጃ የለኝም፤ የድርጅት ሰዎች ብትጠይቅ የተሻለ ነው” በማለት ዜናውን ይፋ ላደረገው የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ተናግረዋል።lencho and melesየሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘትና በሪፖርቱ ለማካተት እንዳልተቻለ ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል። አብዛኛው የኦነግ ደጋፊዎች የነበሩ በድርጅቱ የትግል ጉዞና ውጤታማ አለመሆን መማረራቸውን የተለያዩ ድረገጾች በስፋት ይዘግቡ ነበር።
ለአቶ መለስ ቅርብ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አቶ ሌንጮ “አገር ቤት ገብተው ይሳካላቸው ይሆን?” የሚለውን ለመናገር “ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ተቀብዬ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ተስማምቼና ወድጄ ወደ አገር ቤት ለመግባት ችያለሁ” በማለት ኢቲቪ ዜናውን ይፋ ሲያደርገውና “ያሳዘነውን መንግስትና ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ሲሉ ከተደመጠ በኋላ እንጂ ከወዲሁ አስተያየት መስጠት እንደሚቸግራቸው አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው ተናግረዋል። “ውሳኔውን ተፈጥሯዊ ጫና” ነው ያሉም አሉ።

No comments:

Post a Comment