Saturday, January 18, 2014

ይህ እኮ የእኔ እንጂ የአንተ አገር አይደለም!


ፀሐፊ [ሞረሽ] ምድብ [ኑሮና ፖለቲካ]
በዚህ ልንጨርሰው ባገባደድነው አመት ጥቅምት ወር ውስጥ ለስራ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ተነስቼ ወደ ሀገሪቱ ምዕራብ ክፍል መዳረሻየን ጋምቤላ ክልል ወደ ምትገኝ ዲማ ከምትባል ትንሽ የገጠር ከተማ አድርጌ ተጉዤ ነበር። በመጀመሪያው ጉዞየ ከአዲስ አበባ ተነስቼ ጂማ አደርኩ። በሚቀጥለው ቀን ደግሞ በሌላ የህዝብ ማመላለሻ መኪና ተሳፍሬ ጉዞየን ወደ ሚዛን ከተማ ቀጠልኩ። ከጂማ እስከ ሚዛን ያለው ጉዞ ስምንት ያህል ሰዓት ፈጀብን። ከጂማ – ሚዛን ያለው መንገድ የአስፓልት ንጣፍ ቢጀመርለትም አብዛሃኛው የመንገዱ ክፍል በፒስታ የተሸፈነ በመሆኑና ኮረኮንቻማ ስለሆነ ጉዞው በጣም አድካሚ ነበር።
መዳረሻዬ ወዳደረኳት ዲማ ከተማ ደርሼ ቶሎ ለመመለስ ስለፈለኩ ሚዛን አውቶብስ ተራ ከወረድኩ በሗላ ቀጥታ ወደ ዲማ የሚወስደኝን መኪና ነበር ማፈላለግ የጀመረኩት ። የዕለቱን የምሳ መርሃ-ግብርም የፈፀምኩት መኪናውን ካገኘሁት በሗላ ነው ። ይህ ከላይ ሳወጋችሁ የቆየሁት ዋናው የጉዞ ትውስታዬ አይደለም። እንድሁ አነሳሴንና ዋና ዋና ያልኳቸውን የጉዞ ትውስታዎች እስኪያጋጥሙኝ ድረስ ያለፍኩበትን በደምሳሳው ለማሳዬት እንጂ ።
የመጀመሪያ ገጠመኜ የተሳፋሪን ትኬት ከመቁረጥ ይጀምራል ። የመኪናው ረዳት ትኬቱን ቆርጦ ሲሰጠኝ ከሚዛን-ዲማ ለመድረስ 47 ብር አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃል ፤ ትኬቱ ። እኔም ይህን ካየሁ በሗላ የሀምሳ ብር ኖት አውጥቼ ሰጠሁት ። ረዳቱ ዝርዝር ብሮችን ማለት የአንድ አንድ ብር ኖቶችን ይዞ ስላየሁት ሶስት ብር መልስ ይሰጠኛል ብየ ስጠብቅ ዝም ብሎኝ ሄዴ ። ‘ ቆይ ይሄ ረዳት ሶስት ብር አሁን መስጠት እየቻለ ለምንድነው የሚያዘገየው’ ስል አሰብኩ። የአንዳንድ ረዳቶች ተንኮልም ታወሰኝ ። እናም ተንኮል አስቦ ይሆናል ብየ ወዲያውኑ ሳይረሳው ለመጠየቅ ወሰንኩ ። ጠራሁት፤ ሶስት ብር መልስ እንዳለኝና እንድሰጠኝ ጠየቅሁት ። እሱ ግን በደንታ ቢስነት “ሶስት ብሩ እኮ የአጃቢ ነው” አለኝ ። እኔ በሱ መልስ እያሾፈብኝ ነው ብዬ ገምቼ ስለተበሳጨሁ “ እኔ’ኮ እዚህ የመጣሁት ላገባ አይደለም፤ እያገባሁም አይደለም፤ እናም አጃቢ አያሰፈልገኝም ።” አልኩት ትንሽ እንዴ መቆጣት ብዬ ። እሱ ግን ወይ ፍንክች ፣ አሁንም በግደለሽነት “ ሶስት ብሩ የአጃቢ ነው ብየሃለሁ።” አለኝና ትኬት ላልያዙት ትኬት መቁረጡን ተያያዘው ። የእኔና የእሱን ክርክር ሲያደምጡ ከነበሩ ወያላዎች አንዱ “ ፍሬንድ ላገሩ እነግዳ ነሽ እንዴ ?” ሲል ጠየቀኝ ። በሱ ጥያቄ ውስጥ አንድ ለኔ ግልፅ ያልሆነ የማላውቀው የአሰራር ባህል ሊኖር እንደሚችል ገመትኩ ። ደግሞ ሳስታውሰው እንደኔው ሃምሳ ሃምሳ ብር ሲከፍሉ ያየሗቸው ተሳፋሪዎች መልስ አልጠየቁም፤ እኔ ስጨቃጨቅ እንኳን ዝም ከማለት ውጭ ምንም አላደረጉም ። እናም እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ አስገብቼ የማላውቀው አሰራር ሊኖር ይችላል በሚል ግምት ለአገሩ አዲስ መሆኔን ተናገርኩ ።ከዚያም ጥያቄውን ያቀረበልኝ ወያላ “ የአጃቢ ካልከፈልክ ጥይት እንደ ቆሎ ባፍህ ትቅማለህ “ ብሎ ሲናገር የጥይትን ባፍ መግባት ልክ ቆሎ እንደመቃም ነው አቅልሎ ያየው ።
ከዚያም በሗላ ቢሆን አነጋገሩ ግርታን ፈጠረብኝ እንጅ ግልፅ አልሆነልኝም ። ‘እሺ ቃሚው እኔ ልሆን እችላለሁ፤ አስቃሚውስ “ ስል ራሴን ጠየቅኩ ። የእኔን በነገሩ መደነጋገር የፊቴን ገፅ በማየት የተረዳው ሌላው ወያላ አጭር ማብራሪያ አደረገልኝ ። እንደ ወያላው ማብራሪያ የጉዞአችንን አብዛሃኛውን ክፍል ከጨረስን በሗላ ጥቅጥቅ ወዳለ ደንና ሰው በቋሚነት ወደ ማይኖርበት ጫካ እንገባለን። ያኔ ታዲያ በጫካው ውስጥ በዘላንነት የሚኖሩት ‘ሱርማ’ የሚባሉ ብሔረሰቦች ጥቃት ሊፈፅሙብን እንደሚችሉና ከዚሁ ጥቃት ለመዳን ደግሞ ጥበቃ እነደሚያሰፈለገን፤ ለጥበቃዎች አበል የሚሆን እያንዳንዱ ተሳፋሪ ሶስት ሶስት ብር ማዋጣት እንዳለበት፤ ከዚያም ደህንነታችን ተጠብቆ ልንሄድ እንደምችል አብራራልኝ። እናም እንደ አካባቢው ልማድና ባህል ወደ ዲማ የምናደርገው ጉዞ በአጃቢዎች ታግዞ ቀጠለ ።
በዚችው በሚዛን ተፈሪ ከተማ ሌላም ነገር ታዝቢያለሁ። ይህኛው ትዝብቴ የሃገሪቱን የወቅቱን ፖለቲካ ሊያሳይ የሚችልና እየተከተልነው ያለው ያልተማከለ አስተዳደር ስርዓት በየት በኩል እየተተረጎመ እንዳለና በህዝቦቻችን ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ የሚያመላክት ነው ። ነገሩ እንድህ ነው፤ በመኪናችን ረዳትና በአንድ ተሳፋሪ መካከል ጭቅጭቅ ይነሳል። የጭቅጭቃቸው ምክንያት ተሳፋሪው ሰውየ ከመኪናው ኮርቶ መጋላ ላይ የጫነው እቃ ነው። እቃው ለምን ተጫነ ሳይሆን የሚያጨቃጭቃቸው እቃውን የመጫኛ ዋጋ አልተስማማንም ፤ተስማምተናል በሚል ነው። እንደተሳፋሪው አባባል ከሆነ እቃውን ረዳቱ አይቶ ፣ ዋጋውን ተምኖ ተስማምተው እንደጫኑት ነው። ረዳቱ ደግሞ እቃውን ማየቱን ቢያምንም በዋጋ ግን እንዳልተስማሙ ነው የሚናገረው። ተሳፋሪው ሰውየ ረዳቱን በዋጋ ተስማምተው እንደነበረ ይነግረዋል ፤ አይሆንም ከተስማማነው በላይ ጨምር የምትለኝ ከሆነ ያስጫንኩበትን ክፈለኝና ዕቃውንም በራስህ ወጭ አስወርድ ይለዋል ። በተቃራኒው ረዳቱ ደግሞ ምንም አይነት ወጭ እንደማይሸፍንና ዕቃውን በራሱ ወጪ ማውረድ እንደሚችል ይነግረዋል ። ሰውየው ዕቃውን አላወርድም ካለም ራሱ መውረድ እንዳለበትና እንዳይረብሽ ፤ ከጉዞውም እንዳያሰናክለው ያስጠነቅቀዋል ። በዚህ መሃል ተሳፋሪው ሰውየ ፖሊስ አመጣለሁ ብሎ ሲናገር ፤ ረዳቱ ከት ብሎ ሳቀና “ ይህ እኮ የእኔ እንጂ የአንተ አገር አይደለም ፤ ፖሊሶችም ወገኖቼ ናቸው ።”ሲል መለሰለት ። ይሄኔ ነው የሁለቱን ሰዎች ማንነት ለመለየት ጥረት ማድረግ የጀመርኩት ። መቸም ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ የማንነት መገለጫ ብሄር ሆኗል ። እኔም ማንነታቸውን ማጥናት ጀመርኩ ስላችሁ ብሄራቸውን ማለቴ እንጂ ሌላ ሰዋዊ ማንነታቸውን ማለቴ አይደለም ፤ ያማ እኮ ድሮ ቀረ ። እናም ተሳፋሪው ሰውየ አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋው መሆኑንና ከወደ ሰሜኑ የሃገራችን ክፍል እንደመጣ መረዳት ቻልኩ ። ረዳቱ ልጅ ደግሞ የፊት ገፅታውን በማየትና የሚናገረውን ቋንቋ በማድመጥ የአካባቢው ተወላጅ መሆኑን መገመት ቀላል ነው።
ሁለት የእምየ ኢትዮጵያ ልጆች በማይረባ ነገር አንዱ ሌላውን እንደ ባዕድ ሲቆጠረው አያሳዝንም ። ይህ አጋጣሚ ትክክለኛ የወቅቱ ፖለቲካ ነፀብራቅ ነው ። ሌለኛው በዚሁ ጉዞየ ላይ የታዘብኩት ነገር ያጋጠመኝ ደግሞ ከሚዛን -ዲማ የሚወስደንን መንገድ ጀምረን በደቡብ ክልል የምትገኘዋን የቤንች ማጂ ዞን ጨርሰን ወደ ጋምቤላ ክልል መግቢያ ኬላ ላይ ስንደርስ ነበር ።
ኬላው ጋ ስንደርስ መኪናችን እንድቆም ከተደረገ በሗላ የኬላው ፖሊስ ወደ መኪናችን ዘልቆ ሁላችንም የመታወቂያ ወረቀቶቻችንን እንድናወጣና እንድናሳይ ታዘዝን ። መጀመሪያ ጉዟችንን ልንጀምር ስንል ከረዳቱ ጋር ሲጨቃጨቅ የነበረው ሰውየ ከፖሊሱ ጋር ትውውቅ ስለነበረው በዙሪያው ያሉ አምስት ሰዎችን ዘመዶቹ መሆናቸውን ገልፆ አድስ ለሰራው ቤት ምርቃት ከሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የመጡ መሆናቸውን ለፖሊሱ ስላሰረዳ መታወቂያ ሳይጠይቃቸው አለፈ ።
የሌሎቻችንን የመታወቂያ ወረቀቶች ተቀብሎ እያየ የብዞቻችንን ከመለሰ በሗላ የስምንት ሰዎችን መታወቂያ ወረቀት ይዞ ወረደ። ከወረደ በሗላ መለስ አለና መታወቂያ የተወሰደባቸው እንድወረዱ አዘዘ። ይህኔ የመኪናው ሾፌር ወደተሳፋሪዎች መጣና መታወቂያ የተወሰደባቸው ሀምሳ ሀምሳ ብር እንዲያዋጡ አላዋጣም ካሉ መውረድ እንዳለባቸው፤ ሲወርዱም እስር እንደሚጠብቃቸው ነገራቸው ። ስምንቱም መታወቂያ የተወሰደባቸው ሀምሳ ሀምሳ ብር ለሾፌሩ ሰጡ ። ሾፌሩ ከመኪናው ወርዶ ከፖሊሱ ጋር ለብቻቸው ሄደው ጥቂት ካወሩና ከተንሾካሾኩ በሗላ የሰበሰበውን ብር በኪሱ ሸጉጦለት መታወቂያቸውን ይዞ ተመለሰ ።
ነገሩ ግራ ገብቶኝ ቆይቼ ፤ ውጥረቱ ረግቦ ፣ ሰላም ሰፈኖ ጉዞ ከጀመርን በሗላ ከጎኔ የተቀመጠውን ወጣት ስለጉዳዩ ምንነት ጠየቅሁት። ከጎኔ የተቀመጠው ወጣት የምንሄድባት ዲማ ከተማ ነዋሪ ስለሆነ ከሚዛን- ዲማ በተመላለሰ ቁጥር ይህን አይነት ድርጊት ሲፈፀም ስለሚያይ ነገሩን በቅርበት እንደሚያውቀው ገልፆልኝ እንድህ ሲል አስረዳኝ ። መታወቂያቸው የአማራ ክልል ነዋሪ መሆናቸውን ካስረዳ ከመኪናው ወርደው ለተወሰነ ቀን ይታሰሩና ከዚያም ወደመጡበት እንድመለሱ ይገደዳሉ አለኝ ።
ይታያችሁ እንግድህ ሰው በሃገሩ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ ገደብ ሲጣልበት፣ እንድህ አይነት የወረደ ህግ ማወጣት የፖለቲከኞቻችንን የላሸቀ አእምሮ ነው የሚያሳየው ። በአሁኑ ሰዓት አውሮፓዊያን እርስ በርስ ያላቸው ግኑኝነት (በሀገሮቹ መካከል) ከእኛ የክልል ክልል ግኑኝነት የበለጠ ነው ። ምራባዊያን ፖለቲከኞች ስለሰው ልጅ አንድነትና አንድት አለምን ለመፍጠር እየታተሩ ባለበት በዚህ በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የእኛዎቹ መሪዎች ደግሞ እንደገና ወደሗላ ሊመልሱን ይታገላሉ ። የሰው ልጅ በታሪኩ እየተሻሻለ ወደፊት ይሄዳል እንጂ ወደሗላ ተመልሶ አያውቅም ። የጋርዮሽ ዘመንን አልፎ ነው እዚህ የደረሰው ። በአሁኑ ሰዓት ግን የግለሰብ መብትና ነፃነት የበላይነት የተቀዳጀበት ሁኔታ እያለ የእኛው መንግስት ደግሞ እንደገና ወደሗላ ተመልሶ ስለ ቡድን መብት መከበርና የቡድን መብት በግለሰብ መብት ላይ ያለውን የበላይነት ሊያሳየን ይሞክራል ።
የኢፌዲሪ ህገ-መንግሰት አንቀፅ 32(1) እንደሚያሰረዳው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት መብት አለው ። ይህ መብቱ ግን አንድ የክልል ባለስልጣን ባወጣው ህግ ሲገፈፍ ፣ አንድ የክልል ባለስልጣን ህገ-መንግስታዊ መብቱን ሲነጥቀው፤ ያ ለህገ-መንግስቱና ለህገ-መንግስታዊ ስረዓቱ ቆሚያለሁ እያለ ጧት ማታ የሚፎክርብን መንግስት ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለት ውጭ ያለው ነገር የለም ። ወትሮም ይህ መንግስት ለስልጣኑ እንጅ ለዜጎቹ ቀናኢ አይደለም።

No comments:

Post a Comment