Thursday, January 9, 2014


አንዷለም አራጌን ለመጠየቅ የትኛው ፓርቲ አባል እንሁን ? --------- ቃሊቲ ቅጣት ቤት የተወረወረውን ታላቁን ሰላማዊ ሰው አንዷለም አራጌን ለመጎብኘት ቃሊቲ ደርሻለሁ ፡፡በር ላይ ጠያቂዎችን እየተቀበለች የምትመዘግብ ፖሊስ ማንን ለመጠየቅ እንደምፈልግ ጠየቀችኝ ‹‹አንዷለም አራጌን›› አልኩ፡፡ ከወንበሯ ተነስታ አንድ ሃላፊን ‹‹አንዷለምን እጠይቃለሁ የሚል ሰው መጥቷል›› አለችው፡፡ ፖሊሱ ሌላኛዋን ፖሊስ በመጥራት‹ ‹ይህን ሰው ቢሮ ወስደህ ከሐጎስ ጋር አገናኚው›› አላት፡፡ ግቢው ውስጥ ዘልቄ ለአንዷለም ለመግዛት ያሰብኩትን የታሸገ ውሃ ከእስረኛ አከፋፋዮች ላይ በመግዛት ያዝኩ፣ የግቢው ሀላፊ እንደሆነ ወደገመትኩት ሐጎስ ቢሮ በፖሊሷ አማካኝነት አመራሁ፡፡ ሐጎስ ቢሮው የለም፡፡ ሌላ ልጅ እግር ፖሊስ ያመጣችኝን ፖሊስ አንዷለም ወደሚገኝበት ቅጣት ቤት እንድትወስደኝ ፈቀደላት፡፡ አንዷለም የሚገኝበት ቅጣት ቤት ከሁሉም ለየት ያለ የእስር ቤት ድባብ ያለው ነው፡፡ ውሃዬን በሽቦ መሃል በተከፈተችውና የእንጨት ርብራብ በተሰራላት መስኮት ላይ አስቀመጥኩና ብረቱን በር ለሚከፍተው ጠባቂ የአንዷለም ጠያቂ መሆኔን ነገርኩት፡፡ ለወትሮው በሩን (በሁለት ቁልፍ የሚከረቸም የብረት ነው፡፡) ለመክፈት የማያመነታው ጠባቂ በሩ በደንብ መቆለፉን ካረጋገጠ በኋላ ጠብቀኝ በማለት የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ ከረዘሙ ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላ የወታደር ተክለ ሰውነት የተላበሰና ትከሻው ላይ ማዕረግ የደረደረ ኮስታራ ሰው አጠገቤ ተከምሮ ‹‹ማነው ስምህ›› አለኝ፡፡ ነገርኩት፡፡ “መታወቂያህን አምጣ” “መታወቂያዬ በር ላይ ያሉት ጠባቂዎች ጋር ነው” “ አንዷለም ምንህ ነው?” “ጓደኛዬ ነው፡፡” “ከየትኛው ፓርቲ ነው የመጣህኸው?” አንዷለምን ለመጠየቅ የፓርቲ ስም መጥራት ማስፈለጉ ግራ ቢያጋባኝም ‹‹ከአንድነት›› አልኩት፡፡ ‹‹ና ውጣ›› ወጣሁ፡፡ ሀላፊው በዚህ ብቻ ሊተወኝ አልፈቀደም፡፡ መታወቂያውን አምጡልኝ ብሎ ፖሊሶች መሐል ትቶኝ ወጣ፡፡ መታወቂያዬ ምን እንደተደረገች ባላውቅም ተመለሰችልኝ፡፡ አበበ ሲባል የሰማሁት ትሁት ፖሊስ ከኋላዬ ተከትሎኝ ‹‹ያስቀመጥከውን እሽግ ውሃ ውሰድ አለኝ››፡፡ውሃውን የገዛሁት በ65 ብር ነው ተሸክሜ መውሰድ አልችልም እናም ‹‹ለአንዷለም አስገባልኝ ካልሆነ ደግሞ ለአንዱ እስረኛ ስጥልኝ›› አልኩት፡፡ አንዷለምን ለመጠየቅ በፓርቲው ስም አልሄድኩም ግን ከየት ነህ ተባልኩ ኢህአዴግ ነኝ ብዬው ቢሆንስ ወይም የፓርቲ አባል አይደለሁም ብለው ኖሮስ ?፡፡ የፓርቲ አባልነት በደምሳሳው ወንጀል ሆነ ማለት ይሆን? አይ አንቺ አገር!

No comments:

Post a Comment