Wednesday, January 15, 2014

ፓርቲዎች ይወሃዱ፤ ህዝቦችም አንድነታቸው ያጠናክሩ! ፓርቲዎች በተናጠል የሚያመጡት አዎንታዊ ለውጥ የለም።



ፓርቲዎች ይወሃዱ፤ ህዝቦችም አንድነታቸው ያጠናክሩ! -ፓርቲዎች በተናጠል የሚያመጡት አዎንታዊ ለውጥ የለም። መወሃድ አለባቸው፤ ጠንካራ ተፎካካሪና አማራጭ አቅራቢ እንዲሆኑ። ህዝቦችም አንድነት ይኑራቸው፤ ከዉስጥም ከዉጭም ጠላቶች ራሳቸው እንዲጠብቁ። ስለ ዉህደት ስናስብ ማንነትን ስለ ማጥፋት አይደለም። ማንነት በዉህደት አይጠፋም፤ ይጠነክራል እንጂ። ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን መጠበቅ የምንችለው በጋራ ለጋራ ዓላማ ስንነሳ ነው። ሀገራዊ አንድነት ያስፈልገናል። ሀገራዊ አንድነት የሚያስፈልገን ጠንካራ ሁነን ለመዝለቅ ነው። ስለ አንድነት የምናወራው የወገኖቻችንን ማንነት ለመጨፍለቅ አይደለም። የሚጨፈለቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለንም። ኢትዮጵያዊ ማንነት የሁላችን ማንነት ድምር ዉጤት ነውና። "ኢትዮጵያውያን አንድ ነን" ስንል "የተለያየን ነን" አትበሉን። ምክንያቱም መለያየታችንማ ግልፅ ነው። የተለያየን ስለሆንን ነው ስለ አንድነታችን የምናወራው። የተለያየን ባንሆን ኑሮ ስለ አንድነታችን ማውራት ባላስፈለገን ነበር። አዎ! የተለያየን ሁነን ግን ስለ አንድነት እናወራለን። አሜሪካውያን ስለ አንድነት የሚያወሩ ከኢትዮጵያውያን በላይ በአካል ስለሚመሳሰሉ አይደለም። አሜሪካውያን በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ወዘተ የተለያዩ ናቸው (ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ኤስያ፣ ላቲን አሜሪካ ወዘተ የተውጣጡ ናቸው)። ግን በአንድ አሜሪካዊ ሀገር ማንነትና አንድነት ያምናሉ። ሁሉም አሜሪካዊ ማንነታቸው ይቀበላሉ። ሁሉም አንድ ናቸው ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያውያንም "አንድ ነን" ስንል የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ብሄሮች ወዘተ የሉም ማለት አይደለም። ልዩነታችን እንዳለ ሁኖ ግን ኢትዮጵያዊ የሆነ የጋራ ማንነታችን መጠበቅና ማራመድ እንችላለን። ልዩነታችን ለጋራ አንድነታችን ዕንቅፋት ሊሆን አይገባም። የተለያየን ነን ካልን ግን ያው በብሄር ብቻ አይደለም የምንለያየው፤ በክልል እንለያያለን፣ በወረዳ እንለያያለን፣ በቀበሌ እንለያያለን፣ በመንደር እንለያያለን፣ በቤተሰብ እንለያያለን፣ በግለሰብ ደረጃም እንለያያለን። እኔ ከእናቴ፣ አባቴ፣ ወንድሜና እህቴ ጋር አንድ አይደለንም፤ እንለያያለን። እንዲህ ልዩነታችንን የምንቆጥር ከሆነ እንኳን አንድ ሀገር ሊኖረን አንድ ቤተሰብም ሊኖረን አይችልም። በዚሁ እሳቤ አንድ ግለሰብ ብቻ ነው ሊኖረን የሚችለው። ኢትዮጵያውያን አንድ ካልሆነን ሁላችን አንድ አይደለንም። ከአንድ በላይ አንድ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ሊኖሩን አይችሉም። ስለዚህ ስለ አንድነት ስናወራ ልዩነታችንን ግምት ዉስጥ ያስገባ ነው። አሁንም አንድነት ለሕብረት፤ አንድነት ለዕድገት፤ አንድነት ለጠንካራ ማህበረሰብ። የኢትዮጵያውያንን አንድነት መጠበቅ የሁላችን ስራ መሆን አለበት፤ ለህልውናችን አስፈላጊ ነውና። ስለዚህ ፓርቲዎች ይወሃዱ፤ ህዝቦችም አንድነታቸው ያጠናክሩ። It is so!!!
Abraha Desta

No comments:

Post a Comment