Friday, January 3, 2014

ጄነራል ሳሞራ የኑስ የወጠኑት ሴራ የጄነራል አበባ ታደሰን ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።


ከተወሰኑት ወራት በፊት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ አዛዦች የሆኑት ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ጄኔራል ሞላ ሃይለማርያምና ጄ/ል ሰአረ መኮንን ማእረጋቸው ሳይነካ ከተወሰኑ የሀላፊነት ቦታቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ መወሰኑ የጦሩ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በሶስቱ ጎምቱ አዛዦች እና ውሳኔውን ባስተላለፉት በኢታማጆር ሹሙ በጄኔራል ሳሞራ የኑስ የተፈጠረው አለመግባባት መንስኤ ለብዙዎቹ ግልጽ አልነበረም። እነሆ ከወራት በሁዋላ ኢሳት የተወሰኑ የመከላከያ ሰራዊት አዛዦችን በማነጋገር ያጠናከረውን ሪፖርት ያቀርባል። የመረጃ ምንጮቻችን በኮሎኔልነት ማእረግ ደረጃ ያሉ ናቸው። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እና ድምጻቸው እንዲካተት ፈቃደኛ አልሆኑም፣ ጊዜው ሲፈቅድ አዛዦቹ እራሳቸው ታሪኩን ይፋ እንደሚያወጡት ቃል በመግባታቸው እስከዛው በእነሱ በኩል ያለውን እይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋልን።
ዊክሊክስ ከ2 አመታት በፊት ይፋ ባደረገው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ በህወሀት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ወግ አጥባቂና ለዘብተኛ የሚባሉ መሪዎች እንዳሉ ገልጿል። ወግ አጥባቂ የሚባሉት አመራሮች የህወሀት ወይም የትግራይ የበላይነት ተጠብቆ እንዲቆይ የሚፈልጉ ሲሆኑ ለዘብተኞች ደግሞ ይህ አካሄድ ለህወሀትም ሆነ ለኢትዮጵያ ህልውና አደገኛ በመሆኑ በፌደራል ደረጃ የህወሀት ሰዎች ከጀርባ ሆነው ስራዎችን ቢሰሩ ይሻላል ብለው የሚያምኑ ናቸው።
ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መከላከያው ከህወሀት እጅ እስካልወጣ ድረስ በሌሎች ቦታዎች ላይ የሌሎች ብሄር ሰዎች ፊት ሆነው ቢታዩና የህወሀት ሰዎች ከጀርባ ሆነው አመራር ቢሰጡ ይሻላል ከሚሉት ወገኖች መካከል ነበሩ። በዚህም እምነታቸው እርሳቸውን እንዲተኩ የደህኢህዴጉን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለምክትል ጠ/ሚኒስትር አጩዋቸው፣ እርሳቸውም ሲያርፉ አቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚኒስትር ሆኑ።
የአቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚ ሆኖ መሾም አክራሪ የሚባሉትን ወታደራዊ አዛዦችና የደህንነት ሰራተኞችን እንዲሁም በህወሀት ውስጥ ያሉ ጠንካራ ካድሬዎችን አላስደሰተም ። በብአዴን እና በሌሎች ኢህአዴግን በመሰረቱ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች በመከላከያ ውስጥም የመተካካት ስራ ይጀመር በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ መከላከያ ከፖለቲካው ውጭ ነው በሚል ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ መከላከያን በበላይነት የሚመሩት ጄኔራል ሳሞራ ከእድሜ እና ከጤና ጋር በተያያዘ ሃላፊነታቸውን የሚያስረክቡበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ፣ ህወሃቶች እርሳቸውን ሊተካ የሚችል ሰው ማፈላለግ ነበረባቸው። የመከላከያ አዛዦች እንደሚሉት በአግልግሎትም በብቃትም ሳሞራን ሊተኩ የሚችሉት ጄኔራል አበባው ታደሰ ናቸው።
ጄኔራል አበባው የብአዴን ነባር ታጋይ ቢሆኑም፣ በብአዴን ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ አዛዦች ተገቢ የአዛዥነት ቦታ እንዲሰጣቸውና የህወሀት የበላይነት እንዲያበቃና ሁሉም በችሎታው የሚሾምበት አሰራር እንዲመጣ ሲጠይቁ ጄኔራሉ ከህወሀት አዛዦች ጎን በመቆም ከፍተኛ ውለታ እንደሰሩ ይቅርብ ሰዎች ይናገራሉ። ምንም እንኳ በዚህ አገልግሎታቸው በህወሀቶች ዘንድ እንደታማኝ መኮንን ቢታዩም ፣ የጄነራል ሳሞራን ቦታ የመውሰዱን ሃሰብ ግን አክራሪዎቹ የህወሀቶች መሪዎች የሚቀበሉት አይደለም። ወታደራዊ አዞዦቹ አራት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። በቅድሚያ መለስ ህወሀት ያልሆነ ሰው በጠ/ሚንስትር መሾማቸው ስህተት ሰርቷል ብለው ያምናሉ። ሁለተኛ ጄኔራል አበባው ለብአዴን ያላቸው ታማኝነት የህወሀትን የበላይነት ሊያጠፋውና ብአዴንን ወደ ላይ ሊያመጣው ይችላል ብለው ይሰጋሉ። ሶስተኛው ደግሞ 98 በመቶ የሚሆነውን የወታደራዊ አዛዥነት ቦታዎች የተቆጣጠሩት ህወሀቶች በመሆናቸው፣ ጄ/ል አበባው ይህን ለማስተካከል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ብለው ይሰጋሉ። በአራተኛ ደረጃና ዋናው ምክንያት ብለው የሚያስቀምጡት ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ለተንሰራፋው ተስፋ ማጣትና መዳከም ዋናው መንስኤ ሙስና ነው በሚል ጄኔራል አበባው በሙስና ላይ እርምጃ ከወሰዱ ከብዙ የህወሀት አመራሮች ጋር ሊያላትማቸው ይችላል የሚል ነው። በተለይም በብዙ ቢሊዮን ብር በተገናባው ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ( ብኢኮ) እየተባለ በሚጠራው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ ሙስና በጄ/ል ሳሞራ እውቅና የሚካሄድ መሆኑና በዚህም ሙስና ውስጥ የተዘፈቁት ጥቂት የህወሀት ከፍተኛ አመራሮች በመሆናቸው፣ ጄ/ል አበባው እርምጃ ለመውሰድ ሊነሳሱና ይህን የሙስና ሰንሰለት ሊበጥሱት ይችላሉ የሚል ነው።
ጄኔራል ሳሞራ የኑስ የመከላከያ አዛዥነቱን ቦታ ከህወሀት ውጭ ለሆነ ሰው በመስጠት ህወሀትን ማዳከምና ያልታሰበ ጣጣ ማምጣት አልፈለጉም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የስልጣን ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ጄ/ል አበባው ታደሰን የብአዴን አባላት በማይከፉበት፣ የእርሳቸው ደጋፊዎች ተቃውሞ በማያነሱበት እንዲሁም ምንም የዘር ፖለቲካ ባህሪ በሌለው መልኩ ማከናወን አለባቸው። የህወሀት አመራሮች ምንም ነገር ኮሽ ሳይል የወጠኑት እቅድ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ጄ/ል ሞላ ሐይለማርያምንና ጄ/ል ሳእረ መኮንንን ለመጠቀም መወሰናቸውን ወታደራዊ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።
በመጀመሪያ ጄኔራል ሞላ ጄኔራል አበባውን በመቅረብ፣ " ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በኢንጂነሪንግና ብረታብረት ኮርፖሬሽን ( ብኢኮ) ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ ሙስና ለመዋጋት ባለመቻሉ መከላከያ የተገነባበት ዋና መሰረት እየተናጋ ነው። ይህንን ጉዳይ ቶሎ ካላስቆምነው መከላከያ ውስጥ ችግር ከመፈጠሩ አይቀሬ ነው " በሚል ሀሳባቸውን አካፈሉዋቸው። ጄ/ል አበባውም ሀሳቡ ትክክል መሆኑን በመቀበል ከጄኔራል ሞላ ጋር ለወደፊት ስለሚወስዱት እርምጃ ተወያዩ። በዚህ ሂደት ጄል ሳእረ እንዲገባበት ጄል ሞላ ሀይለማርያም ሃሳብ ያቀርባሉ። ጄ/ል ሳእረም በሀሳቡ በመስማማት ከሶስቱ ጄኔራሎች ጋር ምክክር ማድረግ ጀመሩ። ሶስቱ ጄኔራሎች ሌሎች ጄኔራሎችንና አንዳንድ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦችን ለማሳተፍ ወስነው እንቅስቃሴ ጀመሩ። የእንቅስቀሴው አላማ ጄ/ል ሳሞራ ስራቸውን በተገቢው አልተወጡም በሚል ግምገማ ከማካሄድ እንዳያልፍ ተስማምተዋል። በዚህም መሰረት ጄኔራሎቹ ብዙ ደጋፊዎችን አገኙ።
በቂ ምስክሮች መገኘታቸው ሲታወቅ፣ ከመካሪዎች መካከል አንዱ መረጃውን አሾልኮ አወጣ። በዚህን ጊዜ መረጃውን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደረገ። ሶስቱ ጄኔራሎች ቀደም ብለው ያማከሩዋቸው ሰዎች ምስክርነታቸው ለኮሚቴው አባላት ሰጡ። የኮሚቴዎቹ የምርመራ ውጤት ሶስቱም ጄኔራሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጄል ሳሞራ የኑስ ላይ ተቃውሞ እንዲያሰሙ አድማ ማድረጋቸውን አመላከተ። ጄ/ል ሳሞራ የኮሚቴውን ሪፖርት አንድ በአንድ ለሶስቱም ጄኔራሎች አነበቡላቸው። ሶስቱም ጄኔራሎች በሃላፊነት ቦታቸው ላይ እንዲቆዩ ቢደረጉም ከእድገት እንደታገዱና ከአንዳንድ ሃላፊነት ቦታቸው እንደተነሱ ተነገራቸው።
ጄ/ል አበባው የጄ/ል ሳሞራ የኑስን ቦታ የመውሰድ ህልም ተጨናገፈ። ድራማው ምንም የዘር ፖለቲካ ያለበት ሳይመስል በድል ተጠናቀቀ። ጄ/ል ሞላ ሀይለማርያምና ጄ/ል ሳእረ መኮንንም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የቀየሱት መንገድ ተሳካ። ቀጣዩ ኢታማዦር ሹም የህወሀቱ ሌ/ት ጄ/ል ዮሀንስ ገብረመስቀል ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሶስቱንም ጄኔራሎች አስተያየት ለማከተት ላለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ብንቆይም ሊሳካልን አልቻልም። መረጃውን በማካፈል በኩል የተባበሩንን ወታደራዊ አዛዦች ለማስገን እንወዳለን።
via:ESAT

No comments:

Post a Comment