Friday, January 17, 2014

አንድነት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማካለል ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይት ሊያደርግ ነው



ከያሬድ አማረ/ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

አንድነት ፓርቲ ጥር 18/2006ዓ.ም በኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ዙሪያ ከህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ማካለል በሚል በሁለቱ መንግስታት ብቻ በሚስጥር በተያዘው መርሀ ግብር ዙሪያ ከህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጧል፡፡
ፓርቲው በመጪው ጥር 18ቀን 2006ዓ.ም የሚያካሂደው ህዝባዊ ውይይት በኢትዮጵያ በመንግስትና በሱዳን መንግስት መካከል ይፋ ባልሆነው የድንበር ማካለሉ ሂደት ግልፅነት የጎደለው የድንበር ማካለል በሚል ሽፋን ሊደረግ የታሰበና በአካቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለሰቀቀን የዳረገ ከመሆኑም ባሻገር በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ መወያየት አስፈላጊ በመሆኑ ፓርቲው ከህዝብ ጋር ተወያይቶ ግልፅ አቋሙን የሚያሰቀምጥበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ በውይይቱ ላይ በመገኘት ሃሳቡን እንዲገልፅ አንድነት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በሌላ ዜና አንድነት ፓርቲ ለአማራ ክልል እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ በአጭር ግዜ ውስጥ ለህዝብ ግልፅ እንዲሆን በደብዳቤ አሳሰበ።

አንድነት ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ማካለል ዙሪያ ግልፅ የሆነ ማብራሪያ በአጭር ግዜ ውስጥ ለህዝብ እንዲሰጥ በደብዳቤ ጠይቋል።

የአንድነት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት ኢህአዴግ በሉአላዊ ግዛት ማስከበር ጉዳይ የግዴለሽ አመለካከት ያለው በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊጎዳ የሚችል እርምጃ ሲወስድ በመቆየቱና የተለማመድው በመሆኑ አሁንም በተለመደው ግብሩ ለህዝብ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ሊካሄድ የታቀደው የድንበር ማካለል የኢትዮጵያን ጥቅም ባላስጠበቀ መንገድ ሊፈፀም እንደሚችል ፓርቲው ከፍተኛ ስጋት ስላደረበት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለና በሚስጥር የያዘው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደርም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለ ድንበር ማካለሉ አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ ለህዝቡ በአጭር ግዜ ውስጥ ግልፅ የሆነ ማብራሪያ እንዲሰጥ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ገልፀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment