Friday, January 17, 2014

ለሕዝብ ግልፅ ያልሆነው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ


  በቅርቡ ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጋር በተያያዘ የተለያዩ ኀሳቦች እየተነሱ ነው። በተለይ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ካርቱምን ከጎበኙ በኋላ ከሌሎች ጉዳዮች በበለጠ የድንበሩ ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል። የካርቱም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የድንበር ማካለል አለመግባባት (Demarcation disputes) በቅርቡ መፍትሄ እንደሚያገኝ ዘግበዋል። የሱዳኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዓሊ ከርቲ ሁለቱ አገሮች የድንበር ማካለል ችግራቸውን ለመፍታት መስማማታቸውን ገልፀዋል። ሱዳኖቹ “ፍሻጋ” በማለት በሚጠሩት አካባቢ ያለው የድንበር ችግር ይፈታል ብለው እንደሚያስቡ እየገለፁ ነው። በሌላ ወገን በርካታ ኢትዮጵያውያን መሬት ከኢትዮጵያ ተቆርጦ ለሱዳን ሊሰጥ ነው በሚል ቅሬታ እያሰሙ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የሰጠው መረጃ የለም። በቅርቡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሁለቱም አገሮች ሰላማዊ የድንበር ቀጠና እንዲኖራቸው እየሰሩ ነው ከማለታቸው ባለፈ፤ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም። በቀጣይም በሀገር ውስጥና በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እውነታውን ይገልፃሉ ተብሎም ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ይሄው ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት በመሳቡ በፓርላማው ቀርበው ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱ ሀገሮች ድንበር ችግር ያለበት መሆኑን በመጥቀስ የማካለል ስራው እንደሚከናወን መግለፃቸው አይዘነጋም። ይኼው የድንበር ማካለል ከጥቂት ወራት በኋላ ሊከናወን እንደሚችል እየተነገረ ነው። ነገር ግን የማካለል ሂደቱ በምን መልኩ እንደሚፈፀም የታወቀ ነገር የለም። በሀገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ግን የድንበር ማካለሉ ሂደት ግልፅነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ በመንግስት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ አረናም ሆነ አንድነት ቅሬታቸውን ገልፀዋል። የአረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃ ደስታ ጉዳዩን በተመለከተ ፓርቲው እንደ ፓርቲ መረጃ እንደሌለው ገልፀዋል። ነገር ግን በግል በሁመራ ከሚገኙ ነዋሪዎች መረጃውን ለማጣራት ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል። በሁመራ የሚኖሩ አንዳንድ ግለሰብ ነዋሪዎች “መሬቱ ለሱዳን ይሰጣል” ተብሎ እየተወራ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል። በተጨማሪም የአካባቢው ባለስልጣናትን ስለጉዳዩ ለመጠየቅ ሙከራ ማድረጋቸውንም የሚገልፁት አቶ አብርሃ ባለስልጣናቱም “የምናውቀው ነገር የለም” እንዷላቸውም ነው የገለፁት። ፓርቲው ጉዳዩ የሀገር ጉዳይ እንደመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት እያጣራ መሆኑን የገለፁት አቶ አብርሃ፤ ከስርዓቱ ባህሪ በመነሳት በድንበር ማካለሉ ላይ እምነት መያዙ አስቸጋሪ ነው ይላሉ። “ሥርዓቱ ለስልጣን ብሎ እንጂ የሀገር ድንበር ለመጠበቅ አይደለም። ከዚህ ጉዳይ ተነስቶ የኤርትራን ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የሱዳንም ጉዳይ ሊያጠራጥር ይችላል። ምክንያቱም ሥርዓቱ ለኢትዮጵያ ያለው ተአማኒነት ላይ ጥርጣሬ አለን። ሥርዓቱ ዳርድንበር ከመጠበቅ ባለፈ፤ የውጪ ኃይሎችም ጋር ቢሆን በስልጣን የሚቆይበትን መንገድ ሊያፈላልግ ይችላል” በማለት ጥርጣሬአቸውን ገልፀዋል። የሱዳን መንግስት የአባይን ግድብ በመደገፉ በምትኩ ከኢትዮጵያ መሬት ተቆርሶ ተሰጥቶት ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥርጣሬም በተመለከተ አቶ አብርሃ ሲመልሱ፤ “የሱዳን መንግስት የአባይን ግድብ መደገፉ ጥሩ ነው። ነገር ግን የሱዳን መንግስት የአባይን ግድብ ቢደግፈውም፣ ባይደግፈውም የእኛ ግድብ ነው። የሱዳን መንግስት የአባይን ግድብ መደገፉ ጥሩና የምንፈልገው ቢሆንም፤ ስለደገፈ ተብሎ የሚሰጥ መሬት ሊኖር አይገባም። ከአባት፣ አያቶቻችን የተረከብነው መሬት ለሌላ አካል ሊሰጥ አይገባም። ድርጊቱ ተፈፅሞ ከሆነ እንታገለዋለን” ሲሉ መልሰዋል። “መንግስት በጉዳዩ ላይ ግልፅ መሆን አለበት” የሚሉት አቶ አብርሃ፤ በጉዳዩ ላይ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ግልፅ መደረግ አለበት ብለዋል። ድንበሩ ሲካለልም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሳተፍ አለባቸው ብለዋል። “የድንበር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም። ኢህአዴግ በመንግስትነቱ ሳይሆን በፓርቲነቱ ስለሚሰራ ጥርጣሬ አለን” የሚሉት አቶ አብርሃ ስለሆነም ለጉዳዩ ማረጋገጫ የሚሆን ግልፅ መረጃ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ቀጠናው የተረጋጋ ባለመሆኑ የድንበር መካለል እንደሌለበት የጠቀሱት አቶ አብርሃ የድንበር ማካለሉ ሂደት ተጀምሮም ከሆነ መቆም አለበት ብለዋል። በደቡብ ሱዳንና በሰሜን ሱዳን አንዳንድ አካባቢዎች መረጋጋት በሌለበት በድብብቆሽ ወደ ድንበር መካከል መገባት የለበትም ሲሉም አሳስበዋል። የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ጫኔ ታደሰም እንደ አቶ አብርሃ በጉዳዩ ላይ ከመንግስት ግልፅ የሆነ መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀው፤ ነገር ግን መንግስት በውጪ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ዙሪያ ላይ ጠንከር ያለና ኢትዮጵያውያንን ለሚጠቅም ተግባር ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ለዚህ ደግሞ የድንበር ጉዳይ የሕዝብ ጉዳይ እንደመሆኑ ግልፅ አሰራርን መከተል አለበት ብለዋል። ከመንግስት ባለፈ ሚዲያውም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። አቶ ጫኔ በመንግስት በኩል የሀገር ድንበርን በተመለከተ የመድበስበስ አካሄድ መኖር የራሱ አደጋ እንዳለው ይገልፃሉ። ፓርቲያቸውም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊና እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚያሳስበው እንደሆነና በጉዳዩም ላይ ተጨባጭ መረጃ ለማግኘት እየጣረ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ፓርቲም በአካባቢው ከሚገኙ አባሎቹም መረጃ የማሰባሰብ ስራም እያከናወነ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ኢዴፓ ከኢህአዴግ ጋር የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ልዩነት እንዳለውም ጠቅሰዋል። ከድንበር ማካለል ጋር በተያያዘም ያሉ ችግሮች የኢህአዴግ የውጪ ፖሊሲ ችግሮች የሚመነጭ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም በመንግስት በኩል የኢትዮ ሱዳንን ድንበር ማካለል ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚጎዳ መልኩ የሚፈፀም ከሆነ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመን የማጋለጥና የመቃወም ስራ እንሰራለን ብለዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በጉዳዩ ላይ አቋም መወሰዱን ይናገራሉ። ፓርቲው የወሰደው አቋም፤ ጉዳዩን የማጋለጥና ሕዝቡ እንዲያውቀው የማድረግ መሆኑን ገልፀዋል። “የኢትዮጵያ መንግስት ከሕዝቡ ጀርባ ሆኖ ድንበር የማካለል ስራ እየተሰራ በመሆኑ እንቃወመዋለን። ጉዳዩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያውቀው አይመስለንም። ምን ያህል መሬት ለሱዳን ይሰጣል? ለምንስ ይሰጣል? ታሪካዊ ባለቤትነቱ የማነው? የሚለው መታየት አለበት የሚሉት አቶ ስለሺ፤ ድንበሩን በድብብቆሽ የማካለሉ ተግባር ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ፓርቲው ከልዩ ልዩ ምሁራንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሰዎች እንደተረዳው የኢትዮ ሱዳን የድንበር ማካለል ባለፉት ሰርዓቶች ቢነሳም ጉዳዩ ሳያስተናግዱት መቆየታቸውን አስታውሰው ኢህአዴግ ግን መነሻው ግልፅ ባልሆነ መንገድ የድንበር ማካለል ጥያቄውን አሁን ማንሳቱን ጠቅሰዋል። ያም ሆኖ ኢህአዴግ በሱዳን ድንበር አሸባሪ የሚላቸው ወገኖች ተደራጅተው እንዳይመጡበት ገዢ መሬት ለማሳጣት ድንበሩን ለድርድር አቅርቦ እንደሚሆንም እንገምታለን ብለዋል። ፓርቲውም ይሄንኑ ጉዳይ እንደ አጀንዳ በመያዝ የፓናል ውይይት በማዘጋጀት ከፓናል ውይይቱ በሚነሳው ኀሳብ ደግሞ ሕዝቡ አቋም እንዲይዝና እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ወደ አካባቢው በማቅናት በጎንደር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል። “በአሁኑ ወቅት መሬቱ በእርግጥም ለሱዳን አልተሰጠም” ያሉት አቶ ስለሺ፤ ሆኖም ግን በድንበር ማካለሉ ላይ ድርድር ተካሂዶ በወረቀት ደረጃ ሁለቱ አገሮች መስማማታቸውን የኢትዮጵያ መንግስትም በኀሳብ ደረጃ ተስማምቶ በመጪው መጋቢት የመሬት ርክክብ እንደሚፈፀም የሱዳን የመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡት እንደሆነም ተናግረዋል። “ጉዳዩን እየደበቀው ያለው ኢህአዴግ ብቻ ነው” የሚሉት አቶ ስለሺ፤ “ነገሩ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ነው” ብለውታል። የድንበር ማካለል ጉዳይ የሉአላዊነት በመሆኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ ሊፈፀም አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል። ኢህአዴግ ለሀገሪቱ ታሪካዊ ሉአላዊነት ደንታቢስ በመሆኑም የድንበር ማካለሉን ለስልጣኑ ብሎ ከመፈፀም ወደኋላ አይልም ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል። ፓርቲያቸው ሕዝቡ ጉዳዩን እንዲያውቀው ከማድረግ ባለፈ ኢህአዴግ በድርድር የተስማማባቸው ስምምነቶች በመጪው ትውልድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራ ነው ጨምረው የገለፁት። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሐሪም እንደሌሎቹ የፓርቲ አመራሮች ጉዳይ የሚያሳስበው መሆኑን በመግለፅ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ተናግረዋል። አጣሪ ቡድኑ በሚያመጣው መረጃ ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ መኢአድ እንደ ፓርቲ ድንበሩ በቅድመ አያቶቻችን አባቶቻችን የተካለለ በመሆኑ እንደገና መከለል የለበትም የሚል አቋም እንዳለው ገልፀዋል። የፓርቲው አቋም የአከላለል ሂደቱ ግልፅ ይሁን አይሁን ከማለት ባለፈ ድንበሩ እንደገና መከለል አይገባውም የሚል እንደሆነ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ድንበር ማካለል ቀደም ሲል በነበሩ ስርዓቶች ሳይነሳ አሁን የተነሳበት ምክንያት የአማራውን ብሔር በመልከአምድር እና በቁጥር ለማሳነስ የሚደረግ ሴራ ነው የሚሉት አቶ አበባው፤ ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲሁም በሕዝብ እኩልነት የሚያምን ሁሉ ሊቃወመው ይገባል ብለዋል። በመንግስት በኩል የድንበር ማካለሉን ሂደት ለሕዝብ ግልፅ ማድረግ በተለይ ጎንደር አካባቢ ሱዳኖች ይገባናል ስለሚሉት መሬት ግልፅ አቋም መያዝ አለበት የሚሉት አቶ አበባው፤ “ሕዝቡ ድምፁ ሊሰማና የታሪክ አዋቂዎችና አባቶች በጉዳዩ ሊጠየቁ ይገባል። ሽፍንፍን ባለ ሁኔታ ድንበር ማካለል ተገቢ አይደለም። ይህ አካሄድ ለሱዳንም ሆነ ለኢህአዴግ አይጠቅምም” ሲሉ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን አድርጎ እና እያደረገ ከሆነም እንደገና ነገሩን እንዲያጤነው” ሲሉ አሳስበዋል። የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው የፓርቲው አዲሱ የስራ አስፈፃሚ እየተወያየባቸው ካሉ ሦስት አስቸኳይ ዋና ርዕሰ ጉዳዮች የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማከለል ጉዳይ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል። ኢህአዴግ በሉአላዊ ግዛት ማስከበር ጉዳይ የላላ አመለካከት ያለው በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊጐዳ የሚችል እርምጃ ሲወስድ በመቆየቱ አሁንም በዚህ ተግባሩ ሊቀጥል እንደሚችል የጠቀሱት አቶ ሀብታሙ ከዚህ በፊትም የሀገሪቱን ታሪካዊ ባለቤትነት በጣሰ መንገድ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መደረጓን አቶ ሀብታሙ አስታውሰዋል። አሁንም የኢትዮ-ሱዳን ድንበር የኢትዮጵያን ጥቅም ባላስጠበቀ መንገድ ሊፈፀም ስለሚችል ከፍተኛ ሰጋት አድሮብናል ብለዋል። “በሱዳን በኩል እየተጠየቀ ያለው መሬት የኢትዮጵያ ነው” የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ ይሄንን ሉአላዊ ግዛት ለሱዳን መስጠት ተገቢ አይደለም ብለዋል። ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ግዛት ላይ እንደገና ከተደራደረበት ከሕዝብ ጋር በመሆን የምንታገለው ነው ብለዋል። እስካሁን በመንግስት በኩል ግልፅ መረጃ እንዲሰጥ ፓርቲያቸው ደጋግሞ እያሳሰበ መሆኑን የጠቀሱት ህዝብ ግንኙነቱ የድርድሩ ውጤት ብቻ ሳይሆን ሂደቱም ለህዝቡ ግልፅ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። “ከዚህ በፊት ከ60ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የረገፉበት የባድመ ጉዳይ መፍትሄ አላገኘም። የአሰብ ወደብን በተመለከተም ኢህአዴግ ቸልተኛ አቋም በመከተሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ጎድቷል” የሚሉት አቶ ሀብታሙ አሁንም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማካለል በተመለከተ ኢህአዴግን እንድንጠራጠረው አድርጎናል ብለዋል። ኢህአዴግ በተፈጥሮአዊ ባህሪውን እና ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚመነጭ አስተሳሰብ መረዳት እንደሚቻለው ግንባሩ በሉአላዊነት ላይ የተዛባ አቋም ያለው በመሆኑ አሁንም የሀገሪቱን ሉአላዊነት በመጠበቅ ላይ ስጋት አለን ሲሉ አቶ ሀብታሙ ገልፀዋል። “ሀገር ማለት ሕዝብ ነው ነው ብለው ለኢትዮ-ኤርትራ ድንበር 60 ሺህ ሰው አስጨርሰዋል” የሚሉት አቶ ሀብታሙ ከሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግና የአባይን ግድብ መደገፉን ተከትሎ መሬት ቆርጦ ለመስጠት ከታሰበ ተገቢም፣ ትክክል አይደለም ብለዋል። ድንበር እየሰጡ ግድብ መገደብ ሰጥቶ መቀበል አይደለም በማለት ተቃውመውታል። ግድብ መገደብ የሀገሪቱ መብት እንደሆነም መታወቅ አለበት ሲሉ አጠቃለዋል። በዚሁ አወዛጋቢ ጉዳይ ላይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ለማነጋገር ጥረት አድርገናል። ነገር ግን ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦፊሴላዊ ጉብኝት ጋር በተያያዘ ስራ ስለበዛባቸው ልናገኛቸው አልቻልንም። በተመሳሳይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች በኩልም መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርገናል። በመስሪያ ቤቱ አሰራር በቃል አቀባዩ በኩል መረጃ ስለሚሰጥ ሊሳካልን አልቻለም። በተጨማሪም የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማልን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ቴሌፎናቸው ስለማይሰራ ልናገኛቸው አልቻልንም። በጠቅላይ ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ደስታ ተስፋውን አነጋግረን አቶ ሽመልስን ወይም አምባሳደር ዲናን ብቻ ማነጋገር እንደምንችል ገልፀውልናል። በቀጣይ ሳምንት የመንግሥትን ምላሽ ይዘን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን።
#MinilikSalsawi‬ ‪#

No comments:

Post a Comment