Saturday, January 4, 2014

የጃዋር ተቃርኖዎች፡ ባለመንጫው መቼ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል?


የዛሬን አያድርገውና ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ ጃዋር መሃመድ በበርካቶች በተለይም በዲያስፖራው ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ጃዋር በተለያዩ ጊዜያት ሶማሊያና የኢትዮጵያ ሁኔታ ከሚሰጠው ትንተና ባሻገር ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የኢህአዴግን አስተዳደር ሲቃወም ተስተውሏል፡፡ ለአብነት ያህል በአንድ ወቅት ከቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስተር አቶ በረከት ስሞኦን ጋር አልጀዚራ ቴሊቪዥን ላይ ቀርቦ ለኢትዮጵያውያንን ጠበቃ ሆኖ መከራከሩ አይዘነጋም፡፡ ይህ የጃዋር ጥረት ከኦሮሞ ብሄርተኝነትንና የፖለቲካ ተንታኝነት አልፎ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሚል ክብር አጎናጸፈው፡፡ ጃዋር ራሱም ከጠባብ ብሄርተኝነት ይልቅ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ አብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ መክሯል፡፡ ለአብነት ያህል የብአዴን ጀኔራሎች ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ተለቅመው በታሰሩበት ወቅት ለአማርኛ ተናገሪ ኢትዮጵያውያን ተከራክሯል፡፡ እነዚህ ህዝቦች ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቆምም ኢትዮጵያውያን በአንድነት መስራት እንዳለባቸው መክሯል፡፡ በወቅቱ ‹‹Ethiopia: General Tadesse and General Asaminew›› በሚል መጣጥፉ ኢትዮጵያውያን በየ ብሄራቸው ከመታጠር ይልቅ አንድ መሆን እንዳለባቸው ለማሳሰብ ታዋቂውን ጸረ ናዚ አባባል ተቅሶ እንዲህ መክሯል፡፡ ‹‹መጀመሪያ በኮሚኒስቶቹ ላይ መጡ፡፡ አልተናገርኩም፡፡ ምክንያቱም ኮሚኒስት አልነበርኩም፡፡ በመቀጠልም በማህበራቱ ላይ መጡ፡፡ አልተናገርኩም፡፡ ምክንያቱም ማህበራቱ ውስጥ አልነበርኩም፡፡ ከዚያም በቤተ እስራኤላዊያን ላይ መጡ፡፡ አልተናገርኩም፡፡ ምክንያቱም ቤተ እስራኤላዊ አልነበርኩም፡፡ ከዚያም በእኔ ላይ መጡ፡፡ (አሁን) ለእኔ የሚናገርልኝ ማንም አልቀረም፡፡›› ብሎ ኢትዮጵያውያንን አስጠንቅቆ ነበር፡፡
jawar
‹‹በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻን እየዘራ ለምዕተ አመት ስልጣኑን እያራዘመ የቆየውን አምባገነንነት መበጠስ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ የተረጋጋ አገርና ዴሞክራሲ ለመመስረት ያስችል ዘንድ አንዱን ቡድን ከሌላው ቡድን እያጋጨ የመኖርን አዙሪት መበጠስ ይኖርብናል፡፡ ዜጎቻችን በሰላምና በተድላ ይኖሩ ዘንድ በአገራችን የህግ የበላይነት መስፈን ይኖርበታል፡፡›› ሲልም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከብሄር ድንበር ወጥቶ ለኢትዮጵያውያን መቆሙን እምነት ተጥሎበት ነበር፡፡ በወቅቱ በአማራነታቸው ታሰሩ ያላቸውንም ‹‹የፖለቲካ እስረኞቻችንን በዚህ በዓል ሰሞን እናስታውሳቸው፡፡ ገቢያችን የሚፈቀድልን ደግሞ ለሚወዱት (ለቤተሰቦቻቸው) እጃችንን መዘርጋት ይገባናል›› ሲል በኢትዮጵያውነት መንፈስ ጽፏል፡፡ በእርግጥ እነዚህን ተግባራት በሚያከናውንባቸው ጊዜያት ጃዋር በብሄር ጉዳይ ሰፊ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ግን ጃዋር ባልታወቀ ምክንያት አቋሙን ቀያይሮ የማይታረቁ ተቃርኖዎች ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡
እንደገና ጠባብ ብሄርተኝነት (ተቃርኖ.1)
የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ በብዛት፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ትልቁን ቦታ የሚይዝና የሚያበረክት ህዝብ ነው፡፡ ይህን ጃዋርም በተደጋጋሚ ሲሟገትበት ተስተውላል፡፡ ኦነግ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውን ህዝብ ‹‹መገንጠል›› በሚል የአናሳ ጥያቄ ውስጥ አፍኖ ማግኘት የነበረበትን ስልጣንና ክብር አሳጥቶታል፡፡ ጃዋርም ኦነግ ለኦሮሚያ ህዝብ የሚገባውን እንዳልሰራና ህዝብም ተገቢውን ስልጣን አለማግኘቱን ባገኛቸው መድረኮች ይገልጻል፡፡ ከዚህም ባሻገር ጃዋር በሌሎች ብሄሮች ላይ ተፈጸመ የሚለውን ችግር ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ አገራችን፣ ወንድሞቻችን›› በሚል በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ሲታገል ቆይቷል፡፡ አንድ ሆነን ብሄርን የሚያጋጨውን ስርዓት እናስወግድ፤ በራሳችን ብቻ ታጥረን ሌሎቹ ላይ የሚደርሰውን ችግር ዝም ብለን በማየታችን ችግሩ የሚደርሰው ‹‹እኛው›› ላይ ነው ብሎም ታዋቂውን ጸረ ናዚ አባባል ጠቅሶ መክሯል፡፡ በዚህ ሰናይ አቋሙም በተለያዩ ወቅቶች እንደ አንድነት ያሉ ህብረ ብሄር የአገር ውስጥ ፓርቲዎችና የዲያስፖራው አካላትም እየተጋበዘ ኢትዮጵያውያን በጋራ ችግራቸውን መቅረፍ እንዳለባቸው ትንታኔውንና አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ይህም ይበልጡን በኢትጵያውያን ዘንድ እንዲታወቅና ትልቅ ክብር እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡
ሆኖም ህዝብን ተጠቃሚ ባለማድረጉ የሚተቸው ኦነግ በተሸነፈበት በአሁኑ ወቅት ብሄር ዘለል ትግል ጀምሮ የነበረው ጃዋርም እንደገና ወደ ኦነጋዊ ጠባብ ብሄርተኝነት ተመልሷል፡፡ በተለይ በቅርቡ ‹‹እኔ በቅድሚያ ኦሮሞነቴን ነው የማስቀደመው›› ብሎ አገራችን፣ ወንድሞቻችን እያለ ሲያነሳው ከነበረው ይልቅ ከኦሮሞ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጻል፡፡ ምንም እንኳ ይህ የአቋም ለውጥ በጃዋር ያልተጀመረ ቢሆንም ‹‹አንዱን ብሄር ከሌላኛው ብሄር›› በማጋጨት ላይ ተመስርቷ ብሎ ይቀወመው ወደነበረው ያረጀ ያፈጀ ፖለቲካ መመለሱ ትልቅ ቦታ ይሰጡት በነበሩት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡
mencha
ከኦሮሞነት ወደ ሙስሊም ኦሮሞነት (ተቃርኖ.2)
ጃዋር በኢትዮጵያውነት ማዕቀፍ ከሌሎች ጋር ጀምሮት የነበረውን ትግል ትቶ ‹‹ቅድሚያ›› ለኦሮሞ ማለቱ ያልተጠበቀ ቢሆንም መብቱ ነው ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በዚህ መንሸራተቱ አለመቆሙ ግን ተቃርኖውን ይበልጡን አጠናክሮታል፡ በተለይ አልጀዚራው ‹‹ስትሪም›› በኋላ ጃዋር ከኦሮሞም ወረድ ብሎ ለኦሮሞ ሙስሊም ቅድሚያ እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡ በአንድ መድረክ ባስተላለፈው መልዕክት እሱ የተወለደበት አካባቢ ‹‹99 በመቶው›› ሙስሊም በመሆኑ ቀና ብሎ ለመሄድ የሚሞክር ክርስቲያን ኦሮሞ አንገቱን በሜንጫ እንደሚቆረጥ በኩራት ተናግሯል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ማዕቀፍ አምባገነንነትን መዋጋት አለብን ብሎ ጸረ ናዚውን አባባል ጠቅሶ ሲያስተምር የነበረው ጃዋር ወደ ኦሮም ማዕቀፍ መውረዱ ሳይበቃ አሁን ደግሞ ከኦሮሞነትም ወደ እምነት አጥብቦታል፡፡ ‹‹የተወለድኩበት አካባቢ አንገትክት ቀና ያደረክ ክርስቲያን ኦሮሞ አንገትክን በሜንጫ ትቆረጣለህ›› የሚል ‹‹ጃሃዲስት›› መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በዚህም ጃዋር ‹‹የኦሮሞ መብት›› ይከበር ሲል የሙስሊም ኦሮሞዎች መሆኑ እንደሆነ አሳብቆበታል፡፡ ምክንያቱም ሙስሊም ኦሮሞዎች ክርሲቲያን ኦሮሞዎች አንገታቸውን ቀና አድርገው ሲሄዱ ሙስሊሞች በሜንጫ እንዲጨፈጭፏቸው እየሰበከ ለክርስቲያን ለኦሮሞ መብት መቆም ስለማይችል ነው፡፡
……ወደ ኢትዮጵያዊ ሙስሊምነት (የማይታረወቅ ተቃርኖ.3)
ስለ ሌሎች ብሄሮች ችግር፣ ስለ ሁሉም ኢትዮጵያዊነት ሰብአዊ መብት አብረን እንስራ በሚል ወደ ኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ እየገሰገሰ የነበረው ጃዋር ወደ ኦሮሞነት ከዚያም ለክርስቲያን ኦሮሞዎች ርህራሄ የሌለው ሙስሊም ኦሮሞነት ተንደርድሯል፡፡ በዚሁ አቋሙ ሳይወጣ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ለመሆንም ይጥራል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች በሙስሊሙ አንገታቸው እንዲቀላ የሚያበረታታው ጃዋር የጎንደርና የአክሱም ሙስሊሞች ከኦሮሞ ሙስሊሞች ጋር አብረው እንዲሰሩ ሊመክር ሞክሯል፡፡ ከኢትዮጵያውነት ወደ ኦሮሞና ከዚያም ሲጠብ ወደ ኦሮሞ ሙስሊምነት የወረደው ጃዋር የብሄርን ድንበር ጥሶ የእምነት አንድነት ለመፍጠር ሲፍጨረጨር የማይታረቅ ሌላ ተቃርኖ ውስጥ መግባቱን የተረዳ አይመስልም፡፡
የዚህ ተቃርኖ በሁለት መንገድ የሚታይ ነው፡፡ አንደኛው ወደ ጠባብ የኦሮሞ ሙስሊምነት የተንደረደረው ጃዋር በብሄር ለማይመስሉት የትግራይና አማራ ሙስሊሞች መጨነቁ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ እምነትና ብሄር አብረው የማይሄዱና የሚጋጩ ማንነቶች መሆናቸው ነው፡፡ የብሄር ደንበር የማይወስነው የእምነት ማንነት መገንባት ከተፈለገ ‹‹እኔ ቅድሚያ ኦሮሞ ነኝ፣ አማራ፣ ጉራጌ…›› ማለት አያስፈልገውም፡፡ ቅድሚያ ሙስሊም አሊያም ክርስቲያን መሆን ነው የሚችለው፡፡ ይህ ከሆነ ጃዋር በቅርቡ ‹‹እኔ ቅድሚያ ኦሮሞ ነኝ›› ያለው ማንነቱ ያበቃለታል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ብሄርና እምነት በአገር ማዕቀፍ ሲታዩ የማይጣጣሙ ማንነቶች በመሆናቸው ነው፡፡ ጃዋር መጀመሪያ ሙስሊም ልሁን ካለ አርሲ ውስጥ ከሚገኘው ክርስቲያን ኦሮሞ ይልቅ አክሱምና ጎንደር ከሚገኙት ሙስሊሞች ጋር ዝምድና ይኖረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ማንነቱ ኢትዮጵያዊ ነው የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም! ሙስሊም ኦሮሞ ነኝ ብሎ ከክርስቲያን ኦሮሞው ይልቅ ሌላውን ሙስሊም ሊያስቀድም አይችልም፡፡ ‹‹ቅድሚያ ኦሮሞ ነኝ!›› ካለ ደግሞ ቀድሞ የሚመጣው የጎንደርና የአክሱሙ ሙስሊም ሳይሆን ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ክርስቲያንና ዋቄ ፈታ ኦሮሞ ነው፡፡ ጃዋር ግን በሁለቱ መካከል ሲምታታ ቆይቷል፡፡
ጃዋር ከዚህም ባሻገር ኦሮሞ ማለት ሙስሊም ማለት ነው በሚል ሌላ የተምታታ ትርጓሜ ውስጥም ገብቷል፡፡ ኦነግና አንዳንዴ የዚሁን ተሸናፊ ፓርቲ አቋም የሚይዘው ጃዋር ኦሮሚያ ምድር ላይ አልደረሱም የሚሏቸው እነ አጼ ዮሃንስና አጼ ቴዎድሮስ በሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ አደረሱ ብሎ የሚያምነውን ጥቃት ኦሮሞን ለመጉዳት መሆኑን ሲገልጽ መታረቅ ወደማይችለው የተቃርኖ አዙሪት ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በአንድ ወቅት ሌላኛው ሲጎዳ ዝም ማለት የለብንም በሚል ጸረ ናዚውን አባባል ተቅሶ ሲመክር የነበረው ጃዋር አሁን ወደ ብሄር ከዚያም ወደ እምነት ናዚያዊነት እየወረደ ነው፡፡
ከኦነግነት ወደ ‹‹ጎበናነት›› (ተቃርኖ 4)
ያኔ እንዲህ ሳይምታታበት ጃዋር ኦህዴድን ኦሮሞን የሚያስገዙ አዲሶቹ ‹‹ጎበናዎች›› ብሎ ይተች እንደነበር ይታወቃል፡፡ ያኔ ‹‹ከጎበናዎቹ›› ይልቅ ከእነ አንድነት ጋር በመስራት የበኩሉን አስተዋጽኦም አድርጓል፡፡ እያቆየ ግን ጃዋር ከኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እየሸሸ አሁን አብሯቸው እየሰራ ከሚገኘው ኢህአዴጎች ጎን መሸጎጥ ጀምሯል፡፡ ጃዋር ‹‹እኔ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ›› ከሚለው አንስቶ ከህወሓት ጋር እንዲተባበር ያስገደዱት የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዱና የመጀመሪያው እሱ ‹‹ቀኝ ጽንፍ›› ብሎ የሚጠራቸው ፓርቲዎች ከሌሎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ነው፡፡ ጃዋርና አቶ ቡልቻ ይበልጡን መጥበብ የጀመሩት አንድነት አብሮት መሄድ ካልቻለው መድረክ ይልቅ ከሌሎች ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ጋር ትብብር ለመፍጠር ፍላጎት እንዳለው በተነገረበት ማግስት ነው፡፡ ሰማያዊና አንድነት በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች መንገዶች ጠንከር ያለ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ሲያደርጉ ደግሞ እነ ጃዋር ‹‹የጠላቴ ጠላት›› ብልሹ ፖለቲካ ውስጥ ገቡ፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲያ በአዲሱ መጽሃፋቸው እንደሚገልጹት 97 ላይ ቅንጅት ጠንካራ እንቅስቀሴ ሲያደርግ ህወሓትም ሆነ ኦህዴድ ‹‹የጸረ ነፍጠኛ›› ግንባር ለቋቋም ጥሪ አድርገውላቸው ነበር፡፡ ዶክተሩ ‹‹አልፈልግም!›› ብለው ባይመልሷቸው እሳቸውም በነ ጃዋር ‹‹አዲስ ጎበና›› ሆነውት አርፈው ነበር፡፡ ይህ ለደ/ር መረራ የቀረበ ጥሪ አንድነትና ሰማያዊ ሲጠናከሩ፣ አሊያም ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ኦህዴድ እራሱን ሊያጠናክር፣ ወይንም የዲያስፖራውን ጫና ለመቀነስ ጃዋርና የእነ ለንጮው ኦነግም ‹የጸረ ነፍጠኛው›› ጥሪ ደርሷቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የእነ ለንጮ ለታው ኦነግ በ2007 ዓ/ም ምርጫ ለመድረስ እየተሰናዳ እንደሆነ እየተወራ ነው፡፡ ኦነግ ለ‹‹ጸረ ነፍጠኛ›› ትግሉ ያመቸው ዘንድ አገር ውስጥ የራሱን ጠባብ ሚዲያዎች ማቋቋም ጀምሯል፡፡ ለአብነት ያህል ከወራት በፊት ‹‹ሰፉ›› የተባለች በኦሮምኛና አማርኛ የምትታተም መጽሄት ገበያ ላይ አውሏል፡፡ ለዚህም የተደራዳሪዎቹ የኦህዴድም ሆነ ህወሓት ይሁንታ እንደሚያስፈልግ አጠያያቂ አይደለም፡፡ የመጽሄቷ ዋና አላማም ስለ አሁኑ ዘመን ጭቆናም ሆነ በደል ሳይሆን ‹‹አማራ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያደረሰውን በደል ማጋለጥ ነው››፡፡ ይህ እንግዲህ የድርድሩም ሆነ የኦነግ ስልት አንዱ አካል መሆኑ ነው፡፡ ህወሓትና ኦነግ የሚስማሙበት አላማ!
በእርግጥ ወደ አገር ውስጥ የሚመለሱት የኦነግ አመራሮች ብቻ አይደሉም፡፡ ጃዋር ሊመለስ እንደሚችልም አንዳንድ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከሌሎቹ ተቀናቃኞቹ ይልቅ ለጃዋር ርህራሄ ማሰየቱን ማሳየቱ አንድ ፍንጭ ነው፡፡ እነ አቡበክር፣ እስክንድር፣ ርዕዮት…. በእጃቸው ምንም ሳይገኝ፣ በፍጹም ሰላማዊነታቸው ‹‹አሸባሪ›› ተብለው ሲፈረድባቸውና ፊልም ሲሰራባቸው የሜንጫ ጀብድን ሲያስተምር የታየው ጃዋር ምንም አልተባለም፡፡ ከእሱ ይልቅ ኮፈሌ ውስጥ ለበቅ የያዙ ወጣቶችን ከቦኮሃራም፣ ከታሊባንና አልቃይዳ ጋር እያመሳሰሉ ‹‹አሸባሪዎች›› ብለው ፊልም ሰርተውባቸዋል፡፡
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደግሞ ኤሊያስ ክፍሌ ስለ ኤሌክትሪክ ገመድ ማቋረጥ ያወራው ‹‹የአሸባሪዎች ማንነት ማሳያ!›› ተደርጎ ሊቀርብ ነው፡፡ በምን መመዘኛ የኤሌክትሪክ መስመር መቁረጥ የሰው አንገት በሜንጫ ከመቁረጥ በልጦ ‹‹ሽብር›› ሊሆን ይችላል? የጃዋርን ‹‹ጀብድ›› እነ ዶ/ር መረራ፣ ዶ/ር ብርሃኑ፣ የኢሳት ጋዜጠኞች፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ….አውርተውት ቢሆን ኖሮ ስንት ፊልም ይሰራበት ነበር? ኢህአዴግ ይህንን የጃዋር ጀብድ አሁን ባይጠቀምበትም መቼም አይጠቀምበትም ማለት አይደለም፡፡ ሌሎች እሱ ከእኛ በላይ የሚያውቃቸውንም ሚስጥሮች እንደተደራደረባቸው ሁሉ ወደ አብሯቸው እየሰራ እንዳያፈነግጥም በልጓምነት ይጠቀሙበታል፡፡ እግረ መንገዱን በርካታ ‹‹ፋኦሎችን›› ያሰሩታል፡፡
በእርግጥ ጃዋር በፖለቲካው ከስሮ ወደ አገር ቤት የገባ የመጀመሪያው ሰው አይደለም፡፡ በርካቶቹ ከእሱ በላይ ‹‹ጀግና›› ተብለው ከህወሓት/ኢህአዴግ ብብት ተሸጉጠዋል፡፡ እነ ሰለሞን ተካልኝ ኤርትራ በርሃ ድረስ ሄደው ‹‹በለው!›› እንዳላሉ ተመልሰው ‹‹ይቀጥል!›› ብለዋል፡፡ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች ፖለቲከኞች፣ የእምነት ‹‹አባቶች›› ብቻ በርካቶች እየከሰሩ ተመልሰዋል፡፡ ሲወናበድ የኖረው ጃዋር ተደራድሮ ቢመለስ የሚገርም አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ለጃዋር አገሩ ናትና መመለሱን የሚጠላ የለም፡፡ ችግሩ በዚህ ስርዓት ምርጫ እንደሌለ ሲናገር እንዳልቆየ ለምርጫ ሊመለስ መሆኑ መነገሩ ነው፡፡ ለኦሮሞ ህዝብ ባለመቆማቸው ኦህዴዶችን ‹‹ጎበናዎች›› እንዳላለ ከህወሓት፣ ብአዴንና ደኢህዴን ስር የሴቶች፣ የትራንስፖርት……ሚኒስቴር ስር ለመስራት ከፈቀደ ነው፡፡
Ze-Habesha 

No comments:

Post a Comment