Sunday, January 12, 2014

አቶ ሽፈራው ጃርሶ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ እስካሁን በህክምና ላይ ይገኛሉ ተባለ


(ዘ-ሐበሻ) በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ከ2 ሳምንት በፊት ባጋጠማቸው ከባድ የመኪና አደጋ የተነሳ እስካሁን በህክምና ላይ እንደሚገኙ የውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለጹ።
ከ2 ሳምንታት በፊት በደቡብ ኦሞ አካባቢ እየተገነባ የሚገኝን የስኳር ፕሮጀክትን ለመጎብኘት ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ወደ ዛው አምርተው እንደነበር የገለጹት ምንጮች በአቶ ሽፈራው ጃርሶ መኪና ላይ በደረሰ አደጋ ባለስልጣኑ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ሽፈራው ላይ አደጋው የደረሰው በወላይታ አካባቢ እንደሆነ ያስታወቁት ምንጮቹ እንደ አደጋው አሰቃቂነት ሕይወታቸው መትረፉ በራሱ ትልቅ እድል ነው። በአካባቢው ሄሊኮፕተር ተልኮ ወዲያውኑ ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል እንደመጡና ህክምናቸውን በዛው እየተከታተሉ እንደሚገኙ ምንጮቹ ጠቅሰው ባለስልጣኑ እስካለፉት 2 ቀናት ድረስ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ካለፉት 2 ቀናት ወዲህ ያለውን የአቶ ሽፈራው ጃርሶን ሁኔታ ዘ-ሐበሻ ለማጣራት ሞክራ አልተሳካላትም።

No comments:

Post a Comment