Tuesday, January 14, 2014

በጅምላ ገድሎ በጅምላ መቅበር ወያኔ ተወልዶ ያደገበት ሙያዉ ነዉ::!!!!


Ginbot 7
በወያኔ ዘርኝነት፤ ጎጠኝነትና ወደር የለሽ ጭቆና ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ጀርባዉ የጎበጠዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ሁለት ወራት ዉስጥ በሁለት እጅግ አስቀያሚና ዘግናኝ በሆኑ የታሪክ ምዕራፎች ዉስጥ አልፏል። ለወትሮዉ በወርሃ ህዳርና ታህሳስ፤ ህዳር ሚካኤልንና የገና በዐልን እያከበረ አጆቹን ወደ ፈጣሪዉ የሚዘረጋዉ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ዘንድሮ ከእነዚህ ሁለት የቆዩ ባህሎቹና ወጎቹ ፈቀቅ ብሎ በሁለት ክብሩን ባዋረዱና ማንነቱን ጥያቄ ዉስጥ በከተቱ ከስተቶች ልቡ ቆስሎ ከራሱ ጋር ሲነታረክ ሰንብቷል። የፈጠረዉን አምላክ መለምን እንጂ በፈጣሪዉ አማርሮ የማያዉቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብ . . . የሚያስብልኝ መንግስት እንደለሌለኝ አዉቃለሁ፤ አምላኬ ግን በፍጹም አይረሳኝም። ምነዉ ቅዱስ ሚካኤል አንተና ሰይፍህ እያላችሁ እንዴት እንዲህ ይደረጋል አንዴ . . . እያለ በምድራዊዉም በሰማያዊዉም መንግስታት ላይ የመረረ ጩኸቱን አሰምቷል።

በህዳር 2006 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ አገራቸዉ ዉስጥ የስራ ዕድል ተነፍገዉ ስራ ፍለጋ ወደ ሳዑዲ የተሰደዱ ወገኖቹ በሳዑዲ ፖሊስና ህዝብ ከፍተኛ በደል ሲፈጸምባቸዉ ተመልክቶ በኃዘንና በቁጭት ልቡ በግኗል። በተለይ ወንዶች ልጆቹ ፈለጊ እንደሌለዉ እንስሳ በየአደባባዩ ሲረገጡና ሲደበደቡ፤ ሴቶች ልጆቹ ደግሞ በየማጀቱ ሲደፈሩ ተመልክቶ ለህዝብና ለአገር ለሚያስቡ አስተዋይና ጨዋ መሪዎች ባለመታደሉ በባዕድ አገር ዉስጥ በደረሰበት ዉርደትና መከራ በአለም አቀፍ ደረጃ ጩኸቱን አሰምቷል።በዚሁ በ2006 ዓም በታህሳሰ ወር አጋማሽ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ብርድ ልብስ ተጠቅልሎ የተጣለ የሰዉ ልጅ አጽም ቀርቶ በስመአብ ተብሎ የታረደ በሬ ስጋም ማየት በማይፈልግበት በገና ፆም ወቅት የገዛ ወገኖቹ አጽም በመንገድ ቆፋሪዎች ከመሬት ዉስጥ እየተጎተተ ሲወጣ አይቶ በቆሰለ ልብና በነደደ አንደበት “እባክህ ፈጠሪ ወይ ዉረድ ወይ ፍረድ” እያለ ከወያኔ ጋር ከመኖር የፈጣሪን ፍርዱን አለዚያም ዳግም ምጽአቱን ተመኝቷል።

ባለፉት ሁለት ወራት ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉ ግፍና መከራ ድፍን ህዳርንና ታህሳስን በአለም ዙሪያ በአራቱም ማዕዘን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ያሰባሰበ፤ ያነጋገረ፤ ያበሳጨ፤ ያስቆጨና አንጀት ያሳረረ ጉዳይ ነበር። አዎ የ2006 ህዳርና ታህሳስ አገር ዉስጥም ካገር ዉጭም ለምን መጡ የሚያሰኙ የቀን ጎደሎዎች ነበሩ። የወገኖቹ በባዕድ አገር አላግባብ መታሰር፤መደብደብና መገደል ያበሳጨዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ሀዘኑና ብስጭቱ ሳይላቀቅ ነበር ባለፈዉ ታህሳስ 18ትና 19 ቀን ሌላ አሳዛኝና አስደንጋጭ ዜና የጭንቅና የመከራ ጓዳ የሆነችዉን መዲናችን ከአዲስ አበባን አንደ ሐምሌ ጨለማ የከበባት። ደርግን አሸንፈዉ ስልጣን ሲይዙ ደርግ ገድሎ የቀበረዉን አስከሬን መቃብር እየቆፈሩ ያወጡት የወያኔ መሪዎች እነሱም በተራቸዉ በጅምላ ገድለዉ በብርድ ልብስ እየጠቀለሉ የቀበሯቸዉን ኢትዮጵያዉያን አስከሬን ዬት እንደቀበሩት እንኳን ሰለማያዉቁ እነሱ እራሳቸዉ እየቆፈሩ አዉጥተዉ ወንድሞቹና እህቶቹ እንደወጡ የቀሩበትን የኢትዮጵያን ህዝብ አንጀት እንደገና አቁስለዋል።

እዚህ ላይ አንድ እጅግ በጣም ሊያሳስበንና ሊያስጨንቀን የሚገባ ነገር ቢኖር ባለፈዉ ሳምንት ከስድት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የጃንሜዳ ጦር ካምፕ አካባቢ በብርድ ልብስ እንደተጠቀለለ የተገኘዉ የ6 ሰዎች አጽም ሊገኝ የቻለዉ ሆን ተብሎ የጅምላ መቃብር ለማግኘት በተደረገ ቁፋሮ ሳይሆን በአጋጣሚ ነዉ። ይህ የሚያሳየን አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ የአገራችን አካባቢዎች ዉስጥ መረጃ የተሰበሰባበቸዉንና የሚጠረጠሩ ቦታዎችን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአለም አቀፉ ህብረተሰብ ጋር ተባብሮ እየቆፈረ መፈተሽ ቢጀምር ወያኔ ጭካኔዉን ሊያሳየን ከሞከረዉ ከደርግ ስርዐት ጋር ምንም የማይለያይ ጨካኝና አረመኔ ስርዐት ለመሆኑ ማንም ማስተባበል የማይችለዉ ተጨባጭ ማስረጃ ይገኛል ብለን እናምናለን።

የወያኔ ዘረኞች አዲስ አበባን በተቆጣጠሩ ማግስት ስራችን ብለዉ የጀመሩት ደርግ የሰለበዉን የኢትዮጵያን ህዝብ ሞራል ማደስ ወይም በሶሻሊዝም ስም የደቀቀዉን የአገራችንን ኤኮኖሚ መገንባት አልነበረም። የደርግ ሰርዐት አንደ ገለባ ሲበተን አብሮት የተበተነዉ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያሰራዊትም ቢሆን እንደጠላት የሚመለከቱት ኃይል ስለነበር ይህ ለእናት አገሩ ዳር ድንበር መከበር ደሙን ያፈሰሰ ሰራዊት የሚበላና የሚቀመስ አጥቶ ወደ መንገድ ላይ ለማኝነት ሲቀየር ሌላ ቢቀር ጡረታዉን እንኳን ለማስከበር ያደረጉለት ምንም ነገር አልነበረም። ወያኔዎች ስልጣን እንደጨበጡ የደረጉት አቢይ ነገር ቢኖር ከክፍለ ሀገር ክፍለ ሀገረ እየዞሩ ደርግ በቀይ ሽብርና በሌላም ሌላ ግዜ ገድሎ የቀበራቸዉን ሰዎች መቃብር እየቆፈሩ አጽም መሰብሰብ ነበር። በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተከታታይ እንደተመለከትነዉ የወያኔ ጉድጓድ ቆፋሪዎች የሰነበተ መቃብር እየከፈቱና አጽም እየሰበሰቡ ደርግ ምን አይነት ጨካኝ ነብሰ ገዳይ እንደሆነ ለአመታት የምናዉቀዉን እዉነት እንደገና እንድናዉቀዉ አድርገዉናል። በዚህ ከአንድ አመት ከመንፈቅ በላይ በዘለቀዉ የወያኔ መቃብር ቁፋሮ ወያኔ የቀድሞዉን ንጉስ የቀዳማዊ ኃ/ስላሤን ጨምሮ የብዙ ሰዎችን የመቃብር ቦታ እየቆፈረ እሱ ለፖለቲካ ፍጆታዉ የሚፈልጋቸዉንና በተለይ ደግሞ የኔ ናቸዉ የሚላቸዉን ሰዎች አጽም እየለቀመ አንደገና በክብር እንዲቀበሩ ሲያደርግ ሌሎቹን የደርግ ሰለባዎች ደግሞ ምሶ ያወጣዉን አፈር አንደገና መልሶባቸዋል። እንደዚህ አይነት ጉድ የተመለከትነዉ ከሃያ ሁለት አመታት በፊት ወያኔ ኢትየጵያን ሲቆጣጠር ነበር።

ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ዉስጥ መንገድ የሚሰሩ ሰዎች ለራሳቸዉ ጉዳይ መሬት ሲቆፍሩ ከተጠቀለሉበት የደብረ ብርሀን ብርድ ልብስ ዉስጥ እየዘለሉ ወጥተዉ “የፍትህ ያለህ” እያሉ ሲጮኹ የሰማናቸዉ አጽሞች ወያኔ በእኔ ዘመነ መንግስት ሰዉ በሰዉነቱ ይከበራል እንጂ እየተጎተተ አየገደልም ብሎ ከማለ በኋላ በራሱ በወያኔ በግፍ እየተጎተቱ ተገድለዉ የተጣሉ ዜጎች አጽም ነዉ። ይህንን በታሪካችን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ጉድ በስፍራዉ ተገኝተዉ የተመለከቱ የአይን ምስክሮች እንደተናገሩት ቦታዉ ዘመናዊ የመቆፈሪያ ማሽኖች በመቆፈር ላይ እያለ በመጀመሪያ አራት አስከሬኖች በብርድልብስ እንደተጠቀለሉ ተንከባለዉ ወደላይ ሲወጡ የታዩ ሲሆን፤ በሁኔታዉ የተደናገጡት ቆፋሪዎች ስራቸዉን አቋርጠዉ ወደ ቤታቸዉ ከሄዱ በኋላ በነጋታው ረፋዱ ላይ በሌላ አቅጣጫ ሌላ ቁፋሮ ሲያደርጉ አሁንም እንደገና በተመሳሳይ ሁኔታ በብርድ ልብስ የተጠቀለሉ ስድስት አስከሬኖች አግኝተዋል።

አንድ አስከሬኖቹ በተገኙበት አካባቢ በብዛት ተገኝቶ ሁኔታዉን ይመለከት የነበረዉን ህዝብ ለማባረር ወታደሮቹን አስከትሎ የመጣ ከፍተኛ ወታደራዊ የጦር መኮንን “ይህ ግቢ ሶስት ስርዓቶችን ያገለገለ በመሆኑ የማናቸው እንደሆነ ለማወቅ አይቻልም፤ ሆኖም ሰዎች በመሆናቸው ክቡር ናቸውና አፈር አልብሷቸው” በማለት የዘረኞቹን የወያኔ መሪዎች አይን ያወጣ ወንጀል ለመደበቅ ሲሞክር ተደምጧል። ሆኖም ሁኔታዉን በቅርብ ሆኖ የተከታተለዉም ሆነ በርቀት ሆኖ በምስል የተመለከተ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወንጀሉ የሌሎቹ መንግስታት ሳይሆን የወያኔ መሆኑን ለመገንዘብ ግዜ አልወሰደበትም። አስከሬኖቹ በጅምላ የተጠቀለሉበት የደብረ ብርሀን ብርድ ልብስም ቢሆን እንኳን መሬት ዉስጥ ተቀብሮ ምስጥ፤ እርጥበትና ዘመን ተፈራርቀዉበት፤ አልጋ ላይ ህያዉ ሰዉ ለብሶትም ቢሆን ሃያ አመት ቀርቶ አምስት አመትም የሚቆየዉ የዛሬዎቹ የወያኔ መሪዎች ለብሰዉት አንደመጡት ቁምጣ በመርፌ ከተጠቋቆመ ብቻ ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት አርብና ቅዳሜ አስር አስከሬኖችን እንዳቀፈ ከመሬት ዉስጥ ሲወጣ ያየነነዉ ብርድል ልብስ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያዉያንን በሚስጢር እየገደለ እንደ ቆሻሻ ዕቃ ዬትም ቦታ መጣሉን እንዳማያቆም ነዉ።

የአገራችን የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀይማኖት የሚሰጠዉ ቦታ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። በእስልምናዉ፤ በክርስትናዉም ሆነ በአይሁድ ሀይማኖቶች አስተምህሮ በሀይማኖት ዉስጥ ሁለቱ ዋና ዋና አካሎች እግዚአብሄርና ሰዉ ናቸዉ፤ ይህ የሚያሳየን ሰዉ ክቡር ፍጡር መሆኑን ነዉ። ወደዚህ አለም ሲመጣም ሆነ ይህችን አለም ሲለይ በከብር መጥቶ በክብር የሚሸኝ የሰዉ ልጅ ብቻ ነዉ። የኢትዮጵያ ክርስትና እምነት መሰረት ከሆነችዉ ከትግራይ ክልል የመጡት የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን ክርስትናዉን ብቻ ሳይሆን የራሳቸዉንም ሰዉ መሆን የረሱ ይመስላል። ሰዉን የመሰለ ክቡር ፍጡር በጅምላ ተገድሎ፤ በጅምላ ከተቀበረበት ቦታ በኮንስትራክሺን ሠራተኞች ከመሬት ዉስጥ እየተጎተተ መዉጣቱን የሰሙ የወያኔ መሪዎች ጉዳዩን አስመልክቶ አንድም ትንፍሽ ያሉት ቃል የለም። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ በእነሱ ቁጥጥር ስር ያሉት የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥንም እነማን እንደሆኑ፤ መቼ እንደሞቱና ማን እንደገደላቸዉ የማይታወቅ ሰዎች አስከሬን በብርድልብስ ተጠቅልሎ ሲገኝ ያንን ለስድብና ህዝብን ለመኮነን ቀኑን ሙሉ የሚከፍቱትን አፋቹዉን መክፈት አልፈለጉም። የሚገርመዉ እንደ አለባሌ ነገር ከተጣሉበት ቦታ ተጎትተዉ የወጡት አስከሬኖች ሁኔታና የተጠቀለሉበት ብርድልብስ ሙሉ በሙሉ ወንጀሉን ወያኔ ላይ ስለሚያመለክት ነዉ እንጂ የእነሱ እጅ የሌለበት ወንጀል ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሳምንት ሙሉ ሌላ ዜና አይሰማም ነበር።

አገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገሮች የሚኖረዉ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ባለፈዉ ሳምንት እንደ ዋዛ ከመሬት ዉስጥ እየተጎተቱ የወጡ ወገኖቹን አስከሬን ጉዳይ በቀላሉ መመልከት የለበትም። ወያኔ ስልጣን እጁ ከገባ ጀምሮ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን እያፈነ በየማጎሪያ ቤቱ አጉሯቸዋል። ከሰሞኑ ጃንሜዳ አካባቢ ያየነዉ ዘግናኝ ክስተት ስለእነዚህ ወያኔ በየድብቅ አስር ቤቶች አስሮ አድራሻቸዉ ስለጠፋ ዜጎቻችን ብዙ የሚለዉ ነገር ያለ ይመስለናል። እኛ ነን አድራሻቸዉ የጠፋ ሰዎች እያልን የምንጨነቀዉ እንጂ እነዚህ ወያኔ አስሯቸዉ አድራሻቸዉ የጠፋ ሰዎች ዬት እንዳሉ ጃንሜዳ አፉን ከፍቶ ነግሮናል። አዲስ አበባና በየከተማዉ የሚኖረዉ ህዝብ ስለወያኔ የጅምላ ግድያ የሚያዉቀዉ ብዙ ሚስጢር ይኖራል፤ በጅምላ ተገድለዉ በጅምላ የሚቀበሩ ሰዎችንም ጉዳይ በተመለከተ ማንም ሰዉ ሳያየዉና ሳያዉቀዉ የሚፈጸም ነገር አይመስለንምና ከአሁን በኋላ ጥረታቻን ሁሉ የወያኔ የጅምላ ግድያዎች በብሄራዊና በአለም አቀፍ አካላት እንዲመረመሩና ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ መሆን አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ያላቸዉ ዜጎች መረጃዎቻቸዉን ማሰባሰብ፤ማደራጀትና ለሚመለከተቸዉ አካላት መስጠት ይኖርባቸዋል። ዬት እንደደረሱ ሳናዉቅ ባለፈዉ ሳምንት ሳይተሳብ በደብረህርሃን ብርድ ልብስ እንደተጠቀለሉ ከመሬት ዉስጥ የወጡ ዜጎቻችን ፍትህ ሳያገኙ ማንም ኢትዮጵያዊ እንቅልፍ ሊወስደዉ አይገባም።

No comments:

Post a Comment