Sunday, January 12, 2014

ኢስጋማ በኢትዮጵያዊያን የስፖርት ጋዜጠኞች ላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የደረሰውን መንገላታት አወገዘ

January 11, 2014


by  • 
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መንገላታት ከደረሰባቸው የስፖርት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ኢብራሂም ሻፊ
የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ( ኢስጋማ ) ደቡብ አፍሪካ ጆሀነስበርግ ውስጥ በአባሎቹ ላይ የደረሰባቸውን መንገላታት አወገዘ .

ኢስጋማ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የምትሆንበት የአፍሪካ ሀገሮች ሻምፒዮና ( ቻን ) ለመዘገብ ወደአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ በአለፈው ሀሙስ ( ጥር 1 ቀን 2006 ዓ . ም ) የተጓዙት ኢብራሂም ሻፊ ( አዲስ ጉዳይ መጽሄት ) , ይስሀቅ በላይ ( ሀት - ትሪክ ጋዜጣ ) እና ፍስሀ ይድነቃቸው ( ኢ. ቢ . ኤስ ቴሌቪዥን ) ለጉዞ እና ለስራቸው የሚሆናቸውን አስፈላጊ ማስረጃ ይዘው ጆሀነስበርግ ኦሊቨር ታምቦ አየር ማረፊያ ጣቢያ ከደረሱ በኋላ በኢሚግሬሽን ሰራተኞች ከአየር ማረፊያው እንዳይወጡ ታግደዋል .

እንደ ማህበሩ ገለጻ ሶስቱ ጋዜጠኞች የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ( ካፍ ) እንደ ቪዛ እንደሚያገለግል የሚገልጸውን ይፋዊ " የሚዲያ አክረድቴሽን " እና ሌሎች የጉዞ ሰነዶችን አሟልተው ጆሀነስበርግ ቢደርሱም የአየር ማረፊያው ሰራተኞች ጋዜጠኞቹ የያዙትን ማስረጃ በመጠራጠር እና ህገወጥ ነው በሚል በጊዜያዊ እስርቤት ውስጥ በማጎር ሌሊቱን እንዲያሳልፉ አድርገዋቸዋል .

ጋዜጠኞቹ በማግስቱ አርብ ( ጥር 2 ቀን 2006 ዓ . ም ) ወደ ሀገራቸው በግድ እንዲመለሱ የተደረጉ ሲሆን ጓዛቸውን እንኳን ይዘው እንዲመለሱ አለመደረጉን ጋዜጠኞቹን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ቅሬታን ባዘለው መግለጫው ላይ አስቀምጧል .

ከሶስቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪ የፎቶ - ጋዜጠኛው ደመቀ ፈይሳ እስከ ቅዳሜ ጥር 3 ቀን 2006 ዓ . ም ጠዋት ድረስ በጆሀንስበርግ ኦሊቨር ታምቦ አየር ማረፊያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኝ እንደነበር ማህበሩ በመግለጫው አስታውቋል .

በአባሎቹ ላይ በደቡብ አፍሪካው ኦሊቨር ታምቦ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ የደረሰውን እንግልት እና ስቃይ ያወገዘው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አባሎቹ ያለምንም መንገላታት ሰብአዊ መብታቸው እና ሞያቸው ተከብሮ ስራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ እንዲፈቀድላቸው ከመጠየቁ በተጨማሪ , ወደሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ጋዜጠኞች ንብረት በቶሎ እንዲመለስም ጠይቋል .

ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ ሀገሮች እግርኳስ ሻምፒዮና ( ቻን ) ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፊታችን ሰኞ ከሊቢያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በሻምፒዮናው የሚኖረውን ጉዞ ይከፍታል

No comments:

Post a Comment