Wednesday, January 15, 2014

መንግስት የግል መጽሄቶች የህትመት ቁጥር መጨመር ስጋት ላይ እንደጣለው ታወቀ


ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስታዊዎቹ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና በአሁኑ ወቅት በመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ስር በአንድ መመሪያነት የሚሰራውና በአዋጅ በፈረሰ ስም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እየተባለ የሚጠራው ድርጅቶች በጋራ አጥንተናል ባሉትና ሰባት ያህል መጽሄቶች ሕግና ስርዓትን በመተላለፍ እየሰሩ መሆኑን የሚያውጀው ጥናት መነሻ የመጽሄቶቹ ቁጥር መጨመር ገዢውን ፓርቲ ስጋት ላይ በመጣሉ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደጠቆሙት በጽንፈኝነት ከተፈረጁት ሰባቱ መጽሔቶች ማለትም ሎሚ፣ፋክት፣አዲስጉዳይ፣ዕንቁ፣ቆንጆ፣ሊያ እና ጃኖ መጽሔቶች መካከል አብዛኛዎቹ ሳምንታዊ የህትመታቸው መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣትና የሚጽፉአቸውም ርዕሰ ጉዳዮችም ገዥውን ፓርቲ አጠንክረው የሚተቹ መሆን በተለይ ከመጪው ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ ኢህአዴግን ስጋት ላይ ጥለውታል፡፡
መጽሄቶቹ ለጥናት ሲመረጡ ቀድሞውኑ ውጤቱ ይታወቅ ነበር ያሉት ምንጮቹ ፣ በጥናቱ ተገኘ የተባለው ውጤት ባለስልጣናቱ በየጊዜው ሲሉት የነበረና በአዲስዘመን ጋዜጣ አጀንዳ ኣምድ ላይ በተከታታይ ሲጻፉ የነበሩ ትችቶች ናቸው ብለዋል፡፡ መንግስታዊ ተቋማቱ የጀመሩት ጥናት ገና አለመጠናቀቁንና ከጅምሩ ተቆንጥሮ እንዲለቀቅ የተደረገው በሁዋላ መንግስት ለሚወስደው እርምጃ ከወዲሁ ህጋዊነትን ለማላበስ ታስቦ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ጥናቱ ገና ሳይጠናቀቅና ድምዳሜው ሳይታወቅ ውጤቱ ይፋ መደረጉም መንግስት ሚዲዎቹን ለመወንጀል የቱን ያህል እንደቋመጠ የሚያሳይ ነውም በማለት አክለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በአዲስዘመን ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ የታተመው ዘገባ እንደሚሳየው ሰባቱ መጽሔቶች ከመስከረም እስከ ህዳር 30/2006 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ባወጡዋቸው ዘገባዎች የጽንፈኛ ድርጅቶች ልሳናት መሆናቸውን፣ሕገመንግስቱን እንደሚጥሱ፣ሽብርተኝነትን እንደሚያበረታቱ፣የተሳሳቱ መረጃዎች ሕዝቡ በስርዓቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ እንደሚደርጉ በጥናት ደርሰንበታል መባሉና ኢሳትም ይህንኑ በዕለቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን በታህሳስ ወር 2006 ባወጣው ሪፖርት መሰረት ፋክት መጽሔት በወር 62 ሺ ኮፒ በማሳተም የሚመራ ሲሆን ሎሚ 55ሺ፣ አዲስጉዳይ 51 ሺ ኮፒዎችን በማሳተም ይከተላሉ፡፡ ቆንጆ 7ሺ፣ ዕንቁ 6ሺ 400፣ጃኖ 4ሺ ሲያሳትሙ ሊያ የተባለችው መጽሔት በታህሳስ ወር ምን ያህል ኮፒ እንደታተመች ባለስልጣኑ በመረጃው አላካተተም፡፡
ምንም አይነት ግሳጼ ካልደረሰባቸው ሳምንታዊ ጋዜጦች መካከል ሪፖርተር የእሁድ እትሙ 11 ሺ፣ ፣ አዲስ አድማስ 8 ሺ 700፣ ሰንደቅ 1 ሺ 933፣ ኢትዮ ቻናል፣ 1 ሺ 737 ያሳትማሉ።
Source-http://ethsat.com/

No comments:

Post a Comment