Thursday, January 16, 2014

መነሻ ገጽ - ኪንና ባህል - የአየር ኃይል ተዋጊ ጀት ሥዕል በ200 ሺሕ ብር ተሸጠ ...



ተጻፈ በ  

የአየር ኃይል ተዋጊ ጀት ሥዕል በ200 ሺሕ ብር ተሸጠ

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ያቋቋሙት ቬትራንስ ማኅበር ታኅሣሥ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም ላይ የ1.5 ሚሊዮን ብር ቃል ተገባ፡፡
የአየር ኃይል ታዋጊ ጀት ሥዕልም በጨረታ 200 ሺሕ ብር ተጠሸ፡፡ በዕለቱ የተገኘው ገቢ በቢሾፍቱ ከተማ ለሚያስገነባው ባለአራት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃና የአየር ኃይል የ70 ዓመት ታሪክ መጽሐፍ ማሳተሚያ የሚውል ነው፡፡ 
መጽሐፉ አየር ኃይል ከተመሠረተበት 1937 ዓ.ም. አንስቶ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ የነበረው አንፀባራቂ ታሪክና ቅርስ ተረካቢው ትውልድ እንዲማርበት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ 
በአርቲስት ለማ ጉያ የተሣለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላንን የሚያሳየውን ሥዕልም ጨረታ ያሸነፉት፣ ኮሎኔል ጳውሎስ አክሊሉ ከእህትና ወንድሞቻቸው ጋር በጋራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
‹‹እኛ ቬትራንስ ነን፣ ሽማግሌዎችም ነን፡፡ የሽማግሌዎች ሥራ ደግሞ መደጋገፍ፣ ማስታረቅ፣ ማስማማት ነው፡፡ የቬትራንስ አሶሴሽኑ ዋነኛ ዓላማም ከአየር ኃይሉ በጡረታ የሚገለሉ አባሎችን በኢኮኖሚ መደገፍ ነው፤›› በማለት የተናሩት የአየር ኃይል ቬትራንስ አሶሴሽን የዕርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሊቀመንበር ኮሎኔል ሥምረት መድኃኔ ናቸው፡፡ 
እንደሳቸው ገለጻ፣ በዕለቱ የሚሰበሰበው ገቢ ማኅበሩ በቢሾፍቱ ከተማ ለጀመረው ሕንፃ ማስፈጸሚያና ለመጽሐፍ ማሳተሚያ ይውላል፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ አስፋው አየልኝ በበኩላቸው የመጽሐፉ ይዘት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን በዕለቱ ለተገኙ እንግዶች አብራርተዋል፡፡ 
ከ13ቱ የመጀመርያ አየር ኃይል ምሩቃን መካከል አንዱ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የማኅበሩ አባል ናቸው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የአየር ኃይሉ አባላት እንደ አሁኑ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ ከሚጠበቅባቸው ሙያዊ ግዴታ በተጨማሪ የጉልበት ሥራ ይሠሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዕለቱ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም የአየር ኃይሉን የ70 ዓመታት ታሪክ በማሳየት የእንግዶቹን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ 
በፕሮግራሙ ላይ ከተገኙ 700 የክብር እንግዶች 1.5 ሚሊዮን ብር ቃል የተገባ ሲሆን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ የማኅበሩን ዓላማ ለማሳካት እንደሚረዳ የአየር ኃይል ቬተራንስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ብርጋዲየር ጀነራል ተጫኔ መስፍን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ መሰል ማኅበራት ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡     
 ethiopianreporter

No comments:

Post a Comment