Sunday, December 15, 2013

በማንዴላ ሞት መንግሥቱን ከግፍ ለማንፃት? በልጅግ ዓሊ

December 15/2013የማንዴላን ሕልፈተ ሕይወት ተመልክቶ በዓለም ደረጃ የሚያስደንቅ ሁኔታ ስናይ ሰነበትን። ማንዴላ የሠራውን መስራት ሳይሆን እሱ የታሰረበትን ዓላማ በተጻራሪ የሚተገብሩ ሁሉ በቀብሩ ላይ ለመገኘት ከተደበቁበት ብቅ ብቅ ማለታቸው የሚስደምም ነው።

በተለይ አንዳንዶቹ በተለያየ የመገናኛ ዘዴዎች ስለ ማንዴላ ጥሩ ምግባር ቃለ መጠይቅ የሰጡትን ስናጤናቸው ብዙ የሚያስተዛዝብ ሁኔታዎችን እንገነዘባለን። በሺህ መጽሐፍ፣ በሽህ ሬዲዩ ቢታገዙም በደም የወየበ ታሪካቸውን የማይሰርዝላቸው ፋሽሽቶች ይህችን ወቅት ተጠቅመው ለሕዝብ ሃሳቢ ሆነው ለመታየት መራወጣቸው የሚገረም ነው። ይህንን ወቅት ለመጠቀም “እኔም ነበርኩበት“ የሚለው ፋሽሽቱ መንግሥቱ ኃይለማርያምም ሳይቀር ከዚምባዌ ድምጹን አስምቷል።

ታሪክ እንደ ማንዴላ ያለውን ጀግናን ሲያከብር ቡከን ፋሽስትንም ሲኮንን ይኖራል። ይህንን መቀየር የሚችል ማንም አይኖርም። ማንዴላ እንዲህ የተወደደውን ያህል እነ ሒትለር፣ እነ ሙሶሎኒ ፣ እነ እስታሊን ደግሞ ሲኮነኑና ሲወገዙ ኖረዋል። ለወደፊቱም እንዲሁ። ታሪክ በሠሩት ግፍ ብዛት ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ሲያወግዛቸው ይኖራል።

የማንዴላ ሞት ዜና በጎላበት ጀምበር በጀርመንም የናዚ ፋሽሽቶች መሪ ሒትለር ሲነሳ መሰንበቱ አንድ ሌላ አስገራሚ ክስተት ሆኗል። ትግሌ (ማይን ካንፍ ፣Mein Kampf ) ሒትለር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1923 በመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ምክንያት ታስሮ በነበረበት ወቅት የጻፈው መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ እንደ ናዚዎች ማኒፌሰቶ ሆኖ ይታያል። መጽሐፉ በአይሁዳውያን ላይ ጥላቻን የሚያስፋፋና ጀርመኖች ምስራቅ አውሮፓንን መውረር እንዳለባቸው የሚቀሰቅስ ነው። በጀርመን ሕግ በተደነገገው መሠረት ይህን መጽሐፍ መልሶ የማሳተም መብት እገዳ (copy right) በ2015 ዓ.ም ያልቃል። ስለሆነም ማንም የፈለገ አካል የማሳተም መብት ይኖረዋል።

ይህንን ድንጋጌ በሚመለከት ጀርመን ውስጥ የጦፈ ክርክር ሲከናወን ሰንብቷል። እንደተለመደው የናዚ ደጋፊዎች ሒትለር ሃገሩን ይወድ ነበር፣ ለሃገሩ ጥሩ ሰርቷል . . . ወዘተ. የሚል ለሒትለር በታሪክ ጥሩ ቦታ ለመስጠት እንቅልፍ አጥተው ሰንብተዋል። ደጋፊዎቹ መጽሐፉን እንደገና ለማሳተም ሲታገሉ በተቃራኒው የቆሙት ደግሞ በሒትለር የተፈጸመውን ግፍ እያነሱ እንደ ሒትለር ዓይነት በዓለም ውስጥ ዳግም እንዳይነሳ መጽሐፉ መልሶ መታተም እንዳይችል ሲታገሉ ተስተውሏል።

በጀርመን ሃገር ባይረን ተብሎ በሚጠራው ክፍለ ሃገር ግን በ2015 የሚልቀውን የማሳተም መብት በመጠቀም የሒትለር መጽሐፍ እንደገና ለማሳተም የተደረገው ጥረት ከሽፏል። የባየር አስተዳዳሪዎች በሒትለር የተጨፈጨፉትን በማክበር መጽሐፉን እንደገና ማሳተም ኢ-ሰባዓዊነት ነው ሲሉ ወስነዋል።

http://www.bbc.co.uk/news/world-europe-25346140

የክፍለ ሃገሩ መንግሥት ብዙ በሒትለር የተጎዱ ቤተሰቦችን አነጋርግሮ ይህንን መጽሐፍ ማሳተም በቤተሰቦቹ ላይ ሕመምን መቀስቀስ እንደሚሆን አሳምኖ ማሳተምም ሆነ ማባዛትን እንደገና ከልክሏል። ይህ ውሳኔ ፋሽሽቶችን ለሚቃወሙ ጀርመኖች ትልቅ ድል ነው።

ይህ ዓይነት ትግል የሚደረገው በጀርመን ብቻ መሆን የለበትም። በእኛም ሃገር ይህ ዐይነቱ አመለካከት ሊዳብር ይገባል። ወያኔ ስልጣን ከወጣ በኋላ የተጀመረውን የጎጠኝነት ፖለቲካ ለመቃወም የተጀመረው ትግል የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ወንጀል ለጊዜው ወደ ጎን አድርጎ ትግሉ በወያኔ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቀጥሏል። ግን ይህ ሃገርን የማስቀደም ክቡር ዓላማ በመንግሥቱ ደጋፊዎች ሲጣስና የመንግሥቱን አረመኔነት ለማድበስብስ የሚደረገው ጥረት ብልጭ ድርግም ማለት ከጀመረ ሰነባብቷል።

የፋሽሽቱ ደጋፊዎች መሪያቸው ከወደቀ በኋላ ስለ መሪያቸው ትልቅነት ማውራት የተለመደ ባህሪያቸው መሆኑንም ታዝበናል። እዚሁ ጀርመን ውስጥ ሒትለር ሃገሩን ይወድ ነበር እንደሚሉት የፋሽሽት ደጋፎዎች ማለት ነው። የሒትለር ደጋፊዎች ለዚህም ድጋፋቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ባንድ ወቅት ከየሃገሩ በሰበሰባቸው እስረኞች ያሰራው አውራ መንገድ (Autobahn) ሁል ጊዜ ይጠቀሳል። “ሒትለር ቢኖር ኖሮ ጀርመን የትና የት በደረስች ነበር“ በማለት ዓመኔታ ለመሸመት ይጥራሉ።

እነዚህ የአስተሳሰብ-ደሃ ጀርመኖች በዴሞክራሲ ካገኙት የዓለም የኤኮኖሚ ትልቅነት ይልቅ የእነርሱ ዘር ትልቅነት ላይ የተመረኮዘው የሒትለር ዓላማ ታላቅነትን የሚያጎናጽፋቸው ይመስላቸዋል። ለዚህም የሒትለርን መሪ መፈክር አንግበው ሲጓዙ ይታያሉ። በአሁኑ ሰዓት ያለውን የዓለም ሥርዓትና ይህም ሥርዓት ለጀርመን ሕዝብ የሰጠውን ጥቅም የሚያውቀው የጀርመን ሕዝብ ሥርዓቱን በማናጋት ይህንን የተንደላቀቀ ኑሮውን ለማበላሸት የሚጥሩትን ወገኖች ዕድሉ እንዲሰጣቸው ብዙሃኑ የጀርመን ህዝብ ፍላጎት የለውም።

ፋሽሽቶችን ከፍ አድርጎ ለማሳየት የሚደረገው ጥረት በጀርመን ብቻ ሳይሆን በኢጣሊያም ይታያል። በቅርብ ጊዜ ግራዚያኒ ሐውልት ተሰርቶለታል። ሞሶሎኒንም እንደ ጀግና የሚቆጥሩ አልታጡም። በተለይ በፋሽሽቱ ሥርዓት ጥቅም ያገኙ የነበሩ ወገኖች የሌላው ሕብረተሰብ ቁስል አይሰማቸውም። ይልቁንም እንጨት ሊሰዱበት ይፈልጋሉ።

በእኛም ሃገር የሚስተዋለው ከዚህ የተለየ አይደለም። “መንግሥቱ ሃገር ወዳድ ነው “፣ “መንግሥቱ ቢኖር እንዲህ አይደረግም“፣ “መንግሥቱ ቆራጥ ነበር“. . . . ሌላም ሌላም ብዙ ከሥርዓቱ ጥቅመኞች የምንሰማው ባዶ ጩኽት አለ። ቆራጥነቱንም በፍርጠጣው፤ ሃገር ወዳድነቱም የተማረ የሰው ኃይል እንዳይኖር በቀይ ሽብርና በሌሎቹ የግድያ ዘዴዎቹ አስመስክሯል። ወንጀሉ የመንገድ ላይ ስጦ ሆኖ የተመለከትነው ነው። ለሃገራቸው አንድነትና ልዋላዊነት አጽማቸውን ሲከሰክሱ የነበሩ ጀግኖች በመንግሥቱ ነፍስ ገዳዮች ከሃዲ እየተባሉ ሲገደሉ፣ ፈሪ ፈርጣጩ ቡከን ጀግና ተብሎ ሲወደስ መስማት ውርደትም ሃፍረትም ይሆናል። እነዚህ ጀግኖችን እየሰደቡ ይጽፉ የነበሩ አሁን ደግሞ በውጭ ሃገር የዚህ ፋሽሽት ቆዳ ለማዋደድ የሚደርጉት ጥረት የሚያሳፍር ነው። ለመሆኑ በዚህ ዓይነት ክህደት ይች ሃገር ከወያኔ ነጻ ትወጣለች ብለው ያስቡ ይሆን?

የመንግሥቱ ደጋፊዎች ሰሞኑን የኔልሰን ማንዴላን ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት በማድረግ የሃገራችንን ፋሽሽት አረመኔው መንግሥቱን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ፋሽሽታዊ የሆነውን ገጽታውን እንደገና ለማደስ ጥረት አድርገዋል። ደጋፊዎቹ ይህንን ቡከን ፋሽሽት ከሃገሩ አልፎ ለዓለም አቀፍ ጭቆና እንደታገለ ሊነግሩን ይፈልጋሉ። እነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች መንግሥቱን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በመንግሥቱ በግፍ የተገደሉትን ወገኖች መልሰው ለመግደል ይጥራሉ። በሕይዎት በተረፉትና የወላድ መኻን በሆኑት ወላጆች ቁስል ላይ ጨው እየነሰነሱ መሆናቸን እንዲገነዘቡ አስታዋሽ የሚሹ ይመስላሉ። እንደ ባየር ክፍለ ሀገር ጀርመኖች የሌሎች ሃዘን ሳይሰማቸው የዚህን አረመኔ ፋሽሽታዊ ገጽታ ለማሳመር ጥረት አድርገዋል። ይህ ደግሞ የሚያሳፍር እንጂ የሚያኮራ ድርጊት አይሆንም። ከማሳፈርም አልፎ በመንግስቱ ኃይለማርያም የተገደሉትን ሰማዕታት መልሶ እንደመግደል መግደል ይቆጠራል። በሃገር ላይ የተሰራ ወንጀልም ነው።

በቃለ መጠይቃቸው ላይ ማንዴላን የጦር ሥልት በማስተማር ትልቅ ጥረት ያደረጉትን እነ ጀኔራል ታደሰ ብሩን ለምን መንግሥቱ ራሱ እንደገደላቸው እንኳን ማንሳት አልፈለጉም። ሳያውቁት ቀርተው አይደለም ነገሩን ሳያነሱት የቀሩት። እንደተለመደው መጠየቅ የሚገባቸውን ሃቆች በመሸፈን የፋሽሽቱን ቆዳ የሌለውን መልክ እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ።

http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-23515879

እነዚህ የሬዲዮ ጣቢያ ሃላፊዎች የመንግሥቱ ጉዳይ መነሳት ለጸረ ወያኔው ትግል ከፋፋይ መሆኑ አይታያቸውም። ከፋፋይ መሆኑም ቢያውቁም ከመንግሥቱ ይበልጥ ሃገር በወያኔ ብትፈርስ ድንታ እንደሌላቸው ነው ድርጊታቸው የሚያሳየን። የብዙሃኑ ጸረ ወያኔ ትግል መንግሥቱን ሥልጣን ላይ ወይም ደጋፊዎቹን ስልጣን ላይ ለመመለስ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ትግላችን ዘረኝነትን አጥፍተን ዴሞክራሲን መገንባት መሆኑ ያልገባቸው ካሉ ትልቅ ስህተት ላይ ወድቀዋል። በኢሠፓ አባልነታቸው እንደገና ወደ ስልጣን ተመልሰን እንወጣለን ብለው አስበው ከሆነ ተስፋ ሊቆርጡ ይገባል። ምንም ይሁን ምን ወደ ኋላ አንመለስም።

መንግሥቱ በሃገር መክዳት ለፍርድ መቅረብ እንጂ እንደ ጀግና በየቦታው ቃለ መጠይቅ እየተደረገለት የእሱ ቆዳ ተገልብጦ እንዲለበስ ጥረት መደረግ የለበትም። ከሃገር ሰርቆና ዘርፎ በፈረጠጠው ገንዘብ የሚገዛው የዕውቅና የሃገር ወዳድነት ጃኖም ሊኖር አይገባም። የወንጀለኛ ቆዳ እንጂ። ንፁህ ነን የሚሉ ካሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ራሳቸውን ከፋሽሽቱ በመነጠል ግልጽ የሆነ አቋማቸውን ሊያሰሙ ይገባል።

በተለይ በሕዝብ ገንዘብ የተቋቋመ እንደ ኢሳት ዓይነት የዜና ማሰራጫ በመንግሥቱ ግፍ የተሰራባቸው ሁሉ እርዳታቸውን የለገሱት መሆኑን አስተዳዳሪዎቹ ልብ ሊሉት ይገባል። እርዳታቸውን ለጠላታቸው ማስተዋወቂያ ሲያደርጉት ሊያጡት የሚችሉትን ድጋፍ መመዘን ብልዕነት ነው። ለምን ቢባል ጥያቄው የሞራል ጥያቄ ነውና!! አሊያ ግን የኢሳትን ዓላማ ጥርጣሬ ውስጥ ይከተዋል።

http://ethsat.com/ESAT-Radio-player/arc ... c_2013.mp3

ለኢሳት ገንዘብ በማሰባሰብ ጥረት ያደረጉ “የሰበዓዊ መብት ታጋይ ነን” የሚሉ ደግሞ ይህ ድርጊታቸው ለሁሉም የሰው ዘር ሰብዓዊ መብት መከበር እንዳልቆሙ ያጋልጣቸዋል። ያገኙት ተሰሚነትም ፀሐይ እንደነካው በረዶ ሊቀልጥ ይችላል።

ይህንን አረመኔ ለፍርድ ይቅረብ ብለው ሲናገሩ ያልተሰሙ፣ በመንግሥቱ ስለተጨፈጨፉት ሲናገሩ ያልተደመጡ፣ ለፍትህ ያልቆሙ፤ ዛሬ ለዚህ አረመኔ መድረክ መስጠታቸው የሃገሪቱ ዜጎች ሁሉ በእኩል አይን እንደማያዩ ድርጊታቸው አጉልቶ ያሳየናል። ሌላው ቢቀር ማንዴላን በሚመለከት ባለውለታዎች ሲነሱ ጀኔራል ታደሰ ብሩም ሆነ ማንዴላን በብዙ የደገፉ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ባለስልጣናት የአሟሟት ሁኔታም መጠቀስ ነበረበት። ታሪክ ግማሽ የለውምና ሙሉው የኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦ በዘገባው መካተት ነበረበት።

http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-23515879

ወያኔን አስወግደን ሃገራችንን ዴሞክራሲያዊት እናደርጋታለን ብለን የምናስብ ሁሉ ከደርግና ከመንግስቱ ኃይለማርያም ፋሽሽታዊ ወንጀል ራሳችንን ነጥለን መንግሥቱም ይሁን ወያኔን የህዝብ ጠላትነታቸውን አውቀን ካልሄድን ሃገራችንን ከወያኔ ጭቆና ነጻ የምናወጣበትን ቀን እናራዝመዋለን። ትግሉ ጥርት ብሎ ለዴሞክራሲ ካልሆነ በስተቀር ከሃገር በተሰረቀ ገንዘብ መልሰን ስልጣን እንወጣለን በሚል እቅድ መጓዝ በሃገሪቱ ውስጥ ሊነሳ የሚችለውን ችግር አለማጤን ይሆናል። ማንም ከድጡ ወደ ማጡ መሄድ የሚፈልግ አይኖርም።

መንግሥቱን ለቃለ መጠይቅ የጠሩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ይህንን በማድረጋቸው ምን ያህል ከወያኔ ጋር የሚደረገውን ትግል እንደከፋፈሉ ካልተረዱ የሚያሳዝን ነው። በዚሁ አጋጣሚም የሕዝብ ድጋፍ እንደሚያጡ ሊረዱት ይገባል። ነጻ ፕረስ ሃላፊነት የጎደለው ፋሽሽቶችን ማመጻደቂያ ሊሆን አይገባምና ከዚህ መጥፎ ምግባር መቆጠብ አስተዋይነት ይመስለኛል።

ሂትለር፤ ጀኔራል ፍራንኮ፤ ሞሶሎኒ፤ መለስ ዜናዊ፤ መንግስቱ ኃይለማርያም፤ (በቁም የሞተ) ሁሉም ፋሽሽቶች ሞተዋል። ስማቸው ግን ከታሪክ ጠባሳ ገጾች አይፋቅም። ባንጻሩ ጋንዲ፤ ማንዴላ፤ ማርቲን ሉተር ኪንግና ሌሎቹም ጀግኖች ሞተዋል። ግን ሰማዕታት ናቸው። ታሪካቸውም በጀግንነት የወርቅ ቀለም ተጽፎ ትውልድ ሲወራረሰው ይኖራል። የሁለቱም ወገኖች ስም ከመቅበር በላይ ውሏል። ሆኖም የፋሽሽቶቹ የነ ሂትለር በፀረ-ህዝብነት፤ የነማንዴላ ግን በህዝባዊነት!!

በፋሽሽቶች ለተጨፈጨፉ ሁሉ የሚያስብ በሰላም ይክረም !

ታህሳስ 2006

Beljig.ali@gmail.com

No comments:

Post a Comment