Sunday, December 22, 2013

በጅጅጋ ከተማ ታቆሽሻላችሁ ተብለው ከታሰሩት መካከል ከ40 በላይ ሰዎች ሞቱ


ታህሳስ ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-9ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በጅጅጋ ለማክበር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ከተማ ያቆሽሻሉ ተብለው ተይዘው ከጅጅጋ 25 ኪሜ ገደማ ከምትገኘዋ ቀብሪበያህ እስር ቤት እንዲገቡ ከተደረጉት መካከል ከ40 በላይ ሰዎች ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በመሞታቸው በታሰሩበት አካባቢ እንዲቀበሩ ተደርጓል። 

ሟቾቹ በደንብ ባለመቀበራቸውና የአንዳንዶችን አስከሬን ጅብ አውጥቶ ስለበላው፣ ሌሎቹ ከእስር ቤቱ ራቅ ብለው በድጋሜ እንዲቀበሩ መደረጉን ኢሳት ከክልሉ ባለስልጣናት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በህይወት የተረፉት ሰዎች ከትናንት ጀምሮ የተለቀቁ ሲሆን፣ የዘመዶቻቸውን መሞት የተረዱ አንዳንድ ቤተሰቦች ሀዘን ተቀምጠዋል።

“ከተማ ታቆሽሻላችሁ እና ለጸጥታ ስጋት ትሆናላችሁ” በሚል ምክንያት ታስረው ከነበሩት ሰዎች መካከል ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በጋሪ መግፋት እና በጉልበት ስራ የሚተዳደሩ ነዋሪዎች፣ አይነ-ስውሮች፣ አካለ ስንኩላን፣ መታወቂያ አሳዩ ሲባሉ የክልሉን መታወቂያ ማሳየት ያልቻሉ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣታቸው ጸጉረ ልውጥ ተብለው የተያዙ የሌላ አካባቢ ነዋሪዎች ይገኙበታል።


በጅጅጋ መታወቂያ ለማውጣት 1 መቶ 15 ብር የሚጠይቅ ሲሆን፣ በችግር ምክንያት መታወቂያ ያላወጡና በድንገት መታወቂያ በተጠየቁበት ጊዜ ማሳየት ያልቻሉ በርካታ ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ ተደርገዋል።
የክልሉን የጸጥታ ዘርፍ ሃለፊ የሆኑትን አቶ አብዱላሂ ኢትዮጵያን ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልላቸውም ልናገኛቸው አልቻልንም።


በአገር ውስጥ ያሉ ወይም በውጭ የሚኖሩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች ወይም የቀይ መስቀል ሰራተኞች ሰዎቹ የተቀበሩበትን ቦታ ቦታው ድረስ ሄደው በማየት መረጃውን ይፋ እንዲያደርጉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ጠይቀዋል። አካባቢው የመከላከያ ሰራዊት አባላት በብዛት የሚንቀሳቀሱበት በመሆኑ ያለክልሉ ፈቃድ ፎቶግራፎችን ማንሳት አይቻልም።
መንግስት የብሄር ብሄረሰቦች በአሉ የለምንም የጸጥታ ችግር ማለፉን ቢገልጽም፣ በጸጥታ እና በገጽታ ግንባታ ስም ዜጎች ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጋቸውን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።


በጅጅጋ የተካሄደውን ዝግጅት በአብዛኛው ከህወሀት ጋር ዝምድና ያላቸው ሰዎች እንዳዘጋጁ ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል። ከውስኪ አቅርቦት እስከ በዛር ዝግጅት፣ ከማስታወቂያ ስራ እስከ እቃ አቅርቦት በአብዛኛው የህወሀትና ከህወሀት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እንዳዘጋጁትና በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አግኝተውበታል።

No comments:

Post a Comment