Saturday, December 21, 2013

አበራ የማነአብ እና ገነት ግርማ


Ethiopian politicians Genet Girma and Abera Yemaneab
ከግራ ወደ ቀኝ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ እና አቶ አበራ የማነአብ
አንጋፋው የዲሞክራሲና የለውጥ አርበኛ፥ አበራ የማነአብ፥ የሰባ ሁለት ዓመት አዛውንት ናቸው። ከዚህ እድሜያቸው ውስጥ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ባፈላማ ይዟቸው፤ ሃያ አምስቱን ዓመታት ባለም በቃኝና በቃሊቲ ወህኒ ቤቶች ቀርጧቸዋል። ከዚህ ውስጥ ባመክሮ ጥቂት ዓመታት አራግፈው፤ አሥራ ስድስት ዓመት ከስምንት ወራት በሕሊና እስረኝነት አሳልፈዋል። ደሞም ድፍን ሁለት ዓመታትን በጨለማ ቤት በመታገት፤ መራር ግፍና መከራን በመቋቋም፤ ከሞቱት በላይና ከቆሙት በታች በመሆን አቻ እንዳልተገኘላቸው ጉምዙ ትዝታቸው ያረዳናል፡፡
ይህም አልበቃ ያለው አጋች ክፍል አንዲት ጠባብ ክፍል ከሳምባ በሽተኞች ጋር የግድ እንዲጋሩ አድርጎ፤ ለሳምባ በሽተኝነት ዳርጓቸው ኖረዋል። ከዚህ ደዌ ለመፈወስ (ባገር ቤትም ሆነ በቅርቡ እዚህ አውሮፓ ከመጡ በኋላ) አጥብቀው ሕክምናቸውን በመከታተላቸው፤ ዛሬ በሙሉ ጤንነት ላይ ሊገኙ ችለዋል። ለሁለት ዓመታት በካቴና ታስረው እጨለማው ክፍል ውስጥ በሚማቅቁበት ወቅት የጃቸው ቆዳና ሥጋ ተበልቶ አልቆ፤ አጥንታቸው ገጦ ይታይ የነበረበትን የሰቆቃ ዓመታት ሲያስታውሱት እምባቸው ባይኖቻቸው ሙሉ ይሾማል። የኔ ብጤው ሆደባሻ አወያይ ደሞ፤ ሰቆቃቸውን ባይነ ሕሊናው ጭምር እየቃኘ፤ መግቢያ መውጪያው እንደጠፋበት የተከበበ አውሬ ጭንቅ ይለዋል።
“ለመሆኑ እኒህን በምድረ አሜሪካን ከተከበረ ቤተሰባቸው ጋር በሰላምና በተድላ ይኖሩ የነበሩን ትሁት ሰው ምን ተከርቸሌና ተቃሊቲ ወስዶ ዶላቸው?” የሚል መሪ ጥያቄ ያዘለ ሰው ብቅ ቢል አይፈረድበትም። የዚህ መጣጥፍ አቅራቢም ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤልጅግ ብቅ ብሎ በነበረበት ወቅት፤ ይህን ጥያቄ ለሞክሼው ለአቶ አበራ ማስቀደሙ አልቀረም ነበር። አካሄዱ እሳቸውንና እሳቸውን የመሳሰሉ ጎምቱ የፖለቲካው ዓለም ምህዋር አርበኞችን የሕይወት ታሪክ ውርስ ለተሰኘ የዘጋቢ ፊልም ግብዓት ለመቃረም ነበር። (ይህ ለመጪው ትውልድ ቅርስነት የሚቀመጥ የተንቀሳቃሽ ፊልም ዘገባ አገር ቤትና እውጭ የሚኖሩትን ተጠቃሽ ያገር ልጆችን አውደ ሰብእና የሚያካትት ነው።) እናም የዚህ መጣጥፍ አቢይ ጭብጥ የሆነው ጉዳይም የተጨለፈው ከዚያው ከታሪካዊው ጭውውትና ቃለ መጠይቅ ላይ እንደሁ ምስጢር ብጤ ላውጣ። የዚህ ሠናይ ሥራ ዋልታና ማገር የሆኑት ባልደረቦቼ ጋዜጠኛና የፊልም ባለሙያው ክብረት መኮንን፥ ረዳቱ ጋዜጠኛ ሥዩም ደገፋ ይሁንታቸውን አይነፍጉኝም በሚል ተስፋም ምስጢሩን ለተደራስያን ሳካፍል ለይቅርታ እጅ እየነሳሁ ነው።
አዎን… ወደ ተነሳው መሪ ጥያቄ ልመለስና “…ሞክሼ እንዲያው ምን እግር ጥሎዎት ለዚህ ዓይነት ዳፋ ተዳረጉ?…” ለሚለው ጥያቄዬ አቶ አበራ የማነአብ የክፉ ቀን ትዝታን ጀልባ እየቀዘፉ፤  ከአሥራ ሰባት ዓመታት በፊት የሆነውን ሁሉ አጫውተውኛል፡፡ በተፈጥሯቸው እርጋታንና ጸጥታን የተላበሰው ገጽታቸው፤ የዘመኑን አንዳንድ ቀዥቃዣ መነኮሳትና ጳጳሳት ያስንቃል። ታንደበታቸው የሚወጣው እጅግ ቁጥብ አስተያየትና ረጋ ያለው ትረካቸው፤ ሲጠጡት ተዋንጫው እንዳያልቅ የሚጨነቁለትንና የሚሳሱለትን የወይን ጠጅ ያህል ያስጎመጃል። ያውም ከጠይም የመልካቸው ቀለም ጋር እየተናበበ… እየተጨዋወተ… እየተሟዘቀ… 
source http://ecadforum.com

No comments:

Post a Comment