Tuesday, December 31, 2013

የሁሉም ሰው ሥጋት ሕገ-መንግሥቱን ያወጣውም ያጸደቀውም ያንቆለጳጳሰውም ኢህአዴግ ሕገ-መንግሥቱን እንዳይሸሸው ብቻ ነው።

ኢህአዴግ እስካሁን ብዙ ነገር ሸሸ። ቃል ሸሸ። የሰው ስም ሸሸ። የጣት ምልክት ሸሸ። ሸሽቶ ሸሽቶ ከራሱ መሸሽ ግን አልቻለም። የዛሬን አያድርገውና 97 ላይ ኢህአዴግ ቅንጅት የምትለውን ቃል አጥብቆ ፈራት። ጠላት። ሸሻት። እናም በየትኛውም ቃላት ውስጥ ቅንጅት የምትባል አማርኛ ላለመጠቀም ማለ። ጥምረት በሚል ቃል ለወጣት። 

በቀደሙት ‘ቀዳሚ እመቤታችን’ የበላይነት የሚንቀሳቀሰው የሴቶች ጥምረት ሥራውን የምታስተዋውቅለት “ቅንጅት’ የሚል ርዕስ ያላት መጽሔት አሳተመ። የዋሆቹ አዘጋጆች ‘ቃሉ ሌላ ፓርቲው ሌላ’ አሉና መጽሔቱን በየዋህነት በተኑት።የመንግሥት ተሞዳሟጆች ያቺ አደገኛ ቃል በመጽሔት ስም ላይ ሊያውም በራሱ በፓርቲው አባላት መጽሔት ላይ ተንጠላጥላ ስትመጣ ጊዜ ደንብረው ኡኡ… አሉ። ከዚያም ያቺ በስያሜዋ ካልታሰበችበት ቦታ የዋለች መጽሔት ከያለችበት ተለቃቅማ ታጎረች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘ቅንጅት’ የምትል መጽሔት ድራሿ ጠፋ። ስያሜዋን ለውጣ ሸሸች።

በዚሁ ጊዜ ደግሞ የአሸናፊነት (ቪክትሪ) ምልክት ሆኖ የዘለቀው የሌባና የመሃል ጣት ቪ ቅርጽ ድራሹ እንዲጠፋ ተደረገ። ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በምርጫ ምልክትነት ይጠቀምበት ስለነበር ‘ጣቱን የሚቀስር ጣቱን ይቆረጣል’ በሚል ማስፈራሪያ የአሸናፊነት ምልክቱ ከሁለቱ ጣቶች ወደአንዱ ወደአውራ ጣት እንዲዘዋወር ተደረገ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በዚያን ዘመን የሚገቡበት ጠፍቷቸው የሚኮሩበትን የክለባቸውን አርማ የሸሹበት ጊዜ ነበር። ኢህአዴግ ጣት ሸሸ።
ይህ ፓርቲ ሌላም ሌላም ነገር ይሸሻል። የቴዲ አፍሮ ዘፈንንም ሸሽቶታል። ዶክተር ብርሃኑ ‘ጃ ያስተሰርያል’ የሚለውን ዘፈን እወደዋለሁ ስላሉ ይህ ዘፈን በራዲዮ እንዳይዘፈን ተከለከለ። ቴዲ አፍሮም በፖለቲከኛ ዓይን ታየ። ፓርቲው የእኔ በሆነው ነገር የእሱ ድምጽ እንዳይሰማ አለ። ኮንሰርቱ ጭምር የሚዲያ ሽፋን ተነፈገ።

ይህ ፓርቲ ማንዴላ በኢትዮጵያ ወስጥ የነበራቸው ቆይታ ያለፉትን መንግሥታት በጎ ምግባር የሚያጎላ መስሎ ስለታየው ታሪክ ሸሽቷል። ደቡብ አፍሪካ ሄደው ማንዴላ ቀብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን የኢትዮጵያንና የማንዴላን ጥምረት በተመለከተ አንዲት መስመር እንኳን አልተናገሩም። ምክንያቱም ፓርቲያቸው ሲወቅሳቸው ለኖሩት ላለፉት መንግሥታት ስም እንደመስጠትና እውቅናቸውን እንደመጨመር አድርጎ አስቦታልና ታሪክን በተዘዋዋሪ መንገድ ሸሽቶታል። ኢህአዴግ በተለይ ታሪክ ሽሽት ላይ አንደኛ ነው። ‘ኢግኖር’ ሲያደርግ የሚችለው የለም።
ኢህአዴግ እንደፓርቲ የሚቃወሙትን ያገልላል ይባላል እንጂ የሚሸሸው ራሱ ነው። ሌሎች አጠገቡ እንዳይደርሱ ሲያደርግ፣ በሚዲያው ስማቸው እንዳይነሳ ሲያዝዝ ራሱም እየሸሻቸው መሆኑን ያሳብቅበታል።

ብሎ ብሎ የሁሉም ሰው ሥጋት ኢህአዴግ ሕገ-መንግሥቱን እንዳይሸሸው ብቻ ነው። ሕገ-መንግሥቱን ያወጣውም ያጸደቀውም ያንቆለጳጳሰውም ራሱ ነው። አሁን ግን ተቃዋሚውም ዜጎችም ሕገ-መንግሥቱ የሰጠን መብት ተጣሰ እያሉት ነው። ሕገ-መንግሥቱን ትሸራርፋለህ ብለው እየወቀሱት ነው። ሕገ-መንግሥቱን ራስህ አውጥተህ ራስህ ነፍገሃል ብለው እያሙት ነው። ቢወቀስ ቢከሰስ ሁሌም በሕገ-መንግሥቱ አፈጻጸም ጉዳይ ላይ ሆኗልና ቃሉን የፈራው መስሏል። ቀስ በቀስ ሕገ-መንግሥት የሚለው ቃል በሚዲያ እንዳይነገር፣ በኢህአዴግ ስብሰባ እንዳይጠራ፣ ስሙ እንዳይነሳ ሊያደርግ ይችላል። ይህን ሁሉ ነገር ሸሽቶ አሁን በሕገ-መንግሥቱ ጉዳይ ላይ ሲመጡበት ምን እንደሚያደርግ አልለየለትም። ብቻ ሕገ-መንግሥቱንም እንዳይሸሸው ሰጋን።

No comments:

Post a Comment