Friday, December 27, 2013

የሳዑዲ ጉዳይ፡ “31.700 በላይ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተዋል! “


ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ
(ፎቶ ፋይል)
(ፎቶ ፋይል)
የማለዳ ወግ … የተረሱት ኢትዮጵያውያን የኮንትራት ሰራተኞች በጭንቁ ቀን! 
“31.700 በላይ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተዋል! ”
እለተ ሃሙስ ታህሳስ 17 2006 የወጣው አረብ ኒውስ ” Over 31,000 Ethiopian maids ran away “ሳለፍናቸው አመታት ወደ ሳውዲ መጠው ከነበሩት ኢትዮጵያን መካከል ከ 31 ሽህ በላይ የቤት ሰራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጠፉ !” የሚለውን ዜና የሳውዲ መንግስት ስታስቲክ መረጃ ጠቅሶ አስነበበን ። አረብ ኒውስ ያስተላለፈውን መረጃ ካነብኩ ትዝ ያለኝ በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች እንደ ጨው የተበተኑት በኮንትራት ስራ የመጡ የተረሱት በኮንትራት ሰራተኝነት ከቤተሰብ ጀምሮ በደላላ ፣ በመንግስት ሃላፊዎች ብልሹ አሰራር እዚህ በሰው ሃገር ለከፋ አደጋ የተዳረጉት የኮንትራት ሰራተኞ እህቶች ጉዳይ ነው ። አዎ የእኒህ እህቶች መዳረሻ ባለመታወቁ አበሳቸው ዘልቆ ቢያሳስበኝ የማለዳ ወጌ ቅኝት ለማድረግና የማውቀውን መረጃ ለማስጨበጥ ብዕሬን ለማንሳት ተገደድኩ …
“ከጨለማው ህዳር” እስከ ታህሳስ አጋማሽ …
በህዳር መባቻ ግፍ ተጭኖናል የዘንድሮን ህዳር ጨለማ ማለታችን ቢያንስ እንጅ አይበዛበትም። በጨላማው ህዳር ድህነትና የኑሮ ውድነት በለምለም ሃገራችን ተደላድለን እንዳንቀመጥ ያደረገን ስደት ዛሬ የከፋ ሆኗል። እንዲከፋ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆንም በአቋራጭ ኑሯቸውን ለመቀየር የቋመጡት ህገ ወጥ አንዱ መሆኑና ይህም የጥቂቶች ባላስፈላጊ ስራ መሰማራት ስማችን አክፍቶት ለሃጣን የመጣው ለጻድቃን እንዲሉ በላባቸው ለሚያድሩት መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ሳልጠቅሰው ማለፍ አልወድም ። እናም ዛሬ የመቶ ሽወች ኑሮ ተናግቷል! በጨለማው ህዳር!
በጨለማው ህዳር በዋና ከተማዋ በሪያድ የመንፉሃን ግርግር ተከተለ። የታየው ሁከት የብዙዎቻችን ትኩረት ሳበው! ትኩረቱ ያተኮረውህጋዊ ሰነድ የሌላቸው በተለይም የመንን ድንበር ተሻግረው ፡ ሃጅና ኦምራን ታከው የመጡት ዜጎች ጉዳይ ሆነ ! በግርግሩ የታየውን ጭካኔ በመፍራት የመንፉሃ ነዋሪ ያገሬ ሰው ጎጆውን እያፈራረሰ ሃገሩን ጥሎ ወጣ … ተሸኘ ! የሳውዲ መንግስትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ባልጠበቁት ሁኔታ እዚህ ባደረሰን ሁለት ወር በተጣጋው ጊዜ ወደ 160 ሽህ የሚገመት ወገን ወደ ሃገሩ መግባት ከአስገራሚም አስገራሚ ነው ተባለ ። ከሪያድና ከምዕራቡ የሳውዲ ክፍል አንዳንድ ከተሞች የወጣውን ነዋሪ ብዛት የተመለከተ ባይተዋር ቁጥሩን በአግርሞት ቢመለከተው አያስገርምም ። እኛ በሳውዲ ውስጥ የባጀን የከረምን ግን “ጅዳ መች ተነካና ትገረማላችሁ ፣ ጀዛን ፣ አብሃ ፣ ከሚስ ምሸት ፣ ጣይፍና እና በሌላ ሌላው የከተመው ኢትዮጵያዊ መች ተነካና ትገረማላችሁ ? ” ማለት ያዝን … በቀቢጸ ተስፋ ወደ ሃገር መግባቱን አሻፈረኝ ያለው አድፋጩን ሰነድ የሌለውን የተጨነቀ ወገን ” ከሳውዲ ውጡ ” ከሚለው ጋር ሌላ ተደጋግሞ የተነገረ ግን ስላልተቀበልነው ልብ ያላልነውን መረጃ ቆንስልና ኢንባሲዎች ይዘውት ብቅ አሉ ። በቀጣዩ መጠነ ሰፊ የማጣራት ዘመቻም ከአሰሪው (ከከፊሉ) ጋር የማይሰራ እንደ ህጋዊ ስለማይቆጠር የሳውዲ መንግስት በፈቃደኝነት እጃቸሁን ሰጥታችሁ ወደ ሃገር ግቡ ሲል ደጋግሞ አስታወቀ ። ወደ ሃገር መስደድ እንደተጠናቀቀ አንወጣም ባሉት ላይ ፍተሻ በማድረግ በእስራትና በገንዘብ እንደሚቀጣ ኢንባሲና ቆንስል መስሪያ ቤቶች ሲያስታውቁ ወሽመጡ ያልተቆረጠ አለ ለማለት እቸገራለሁ ። እንዲህ እያልን የቆጥ የባጡን እያነሳን እየጣልን “ወደ ሃገሩ መግባት ሲገባው ሳይገባ የቀረው ቁጥር 80 ሽህ ፣100 ሽህ ፣150 ሽህ ይደርሳል !” ያለን ስነዘባራ መንፉሃ ዳግም በፍተሻ ትናጥ ያዘች! ረቡዕ ታህሳስ 16 2006 …
ለአንድ ማለዳ ወግ ቅኝቴ ይሆን ዘንድ ነፍሴ ፈቅዳለችና እናወጋዋለን!
ከጅዳ የሽሜሲ ጊዜያዊ ማቆያ የሚደርሰኝ ሮሮ !
“የሳውዲ መንግስት ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ሳውዲን ለቀው አንዲዎጡ ያስተላለፈውን እና የኢትዮጵያ ኢንባሲና ቆንስለወ መስሪያ ቤቶች ዜጎች ሀጉን አክብረው ወደ ሃገራቸው እንዲወጡ
ያስተላለፉትን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች በመረዳት ወደ ሃገር ለመግባት ወደ ሽሜሲ መጠለያ በመሄድ እጃችን የሰጠን ዜጎች እየተንገላታን ነው! ” በማለት ሮሮና ቅሬታቸውን ያቀረቡ ወገኖች መጠለያ እንደገቡ በኢትዮጵያ መንግስት የመጓጓዣ ሰነድ የተሰጣቸው ቢሆንም የሳውዲ ፖስፖር ሃላፊዎች የቀረበላቸውን ሰነድ በማጣራት የመውጫ ሰነድ ለመስጠት አንግልት አያደረሱባቸው መሆኑን ገልጸውልኛል። ጉዳያቸውን ለማስፈጸም በአውቶቡስ ላይ እና በመጠለያው ግቢ ውስጥ ተበትነው በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ የገለጹልኝ እኒህ ወገኖች የአቅመ ደላማ ሴቶችና ህጻናትን እንግልት ከግምት ውስጥ በማስገባት የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ከሚመለከታቸው የሳውዲ መንግስት ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ትብብር ያደርጉላቸው ዘንድ ጠይቀዋል።
እኒሁ ሮሯችን ለሚመለከታቸው እንዳሰማ የተማጸኑኝ ወገኖች ወደ ጅዳ ቆንሰል ሃላፊዎች ስልክ ደውለው ስልክ ስለማያነሱ ወደ እኔ መደወላቸውን የገለጹልኝ ሲሆን ወደ ሃገር ግቡ ተብለን ወደ ሃገር እንግባ ባልን እንግልት ሊደርስብን አይገባም ሲሉ ” አሁን በደል እያደረሰብን ያለው ሳውዲ ኢሚግሬሽን መፍትሄ እንዲሰጠን ዲፕሎማቶች የተቻላቸውን ያድርጉልን! ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ። በሌላ በኩል ወደ መጠለያው ገብተው አስፈላጊውን ሰነድ ያሟሉ አንዳንድ ነዋሪዎች መካከል ሻንጣችን ጠፋብን የሚሉና ከአንድ ሻንጣ በላይ እንዳይዙ የተከለከሉ ነዋሪዎችም ተመሳሳይ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ጉዳዪን ለማሳወቅና ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ጅዳ ቆንስል ሃላፊ ወደ አቶ ዘነበ ከበደ እና ወደ ምክትላቸው አቶ ሸሪፍ ስልክ በመደወል ያደረግኩት ሙከራ ዛሬም አልተሳካም!
ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!
ነቢዩ ሲራክ

No comments:

Post a Comment