Wednesday, December 25, 2013

በደም የተገነባ ተቋም ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል


ግንቦት 83/91 ላይ የኢትዮጵያ ሰማይ ክፉኛ በሃዘን ሲመታ ፣ ደመናው ሲጠለሽ ፤ ወንዞች መደፈራረስ ሲጀምሩ ፤
የሰውን ልብ ባር ባር ሲለው …….. የክፉው ቀን ጅማሮ ፣ የውርደት ሃሌታ ፣ የሃገር አልባነት ስሜትና የዜግነት
ውርደት ደጃፍ ላይ መውደቃችን እውነት ነበር ።
Air forceውርስ ከአባት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ካልቻለ ፤ አባት የጀመረውን ልጅ ካልቋጨው ፤ አዲስ መንግስት ሲቀየር
የድሮውን በጐ ነገር ሁሉ ብትንትኑን አውጥቶ ካጠፋ ፤ የትውልድ ቅብብሎሽ ገደል ገባ ማለት አይደል ? እናም
በአገሬ ምድር ላይ የእርግማን ዘመን ያኔ “ በ1991 “ “ ሀ “ ብሎ ጀመረ ።
ሌባው ከሳሽ … ቀማኛው ፈራጅ የሆነበት ፤ አባት ተቀምጦ ልጅ የሁሉ ነገር አዛዥ ሲሆን ፤ አህያ ወደ ሊጥ …
ውሻም ወደ ግጦሽ ከተሰማራ …. እነሆ ዘመነ ብልሹ ላይ መድረሱን ያልተረዳ ካለ … እሱ ባይፈጠር …. እናቱ ሆድ
ውስጥ ውሃ ሆኖ ቢቀር ይሻለው ነበር ።
አገር ሲገነጠል ዝምታ ፤ ንብረት ከመሃል አገር ተግዞ ሲያልቅ ዝምታ ፤ ገዳማት ሲታረሱ ፣ ቤተ ክርስቲያናት
ሲዘረፉና ታቦታት በየገበያው ሲቸበቸቡ ዝምታ ፤ ደን ሆን ተብሎ በሰደድ እሳት እንዲወድም ሲደረግ ዝምታ ፤
ግዙፉ የአገር መከላከያ ኃይል እንደተረት አይናችን ስር ሲበተን ዝምታ …….. የምንወደው ዝነኛው የአየር
ኃይላችንም አብሮ ተደርምሶ እንዳልነበረ ሲሆን ዝምታ ነገሰ ። የሚቆጭ ፤ የሚመክር ፤ የሚቆጣና ሃይ የሚል
ወንድ ጠፋ ። የአድዋና የማይጨው አርበኞቻችን የክብር ሃውልቶች ሲፈርሱም ዝምታ ፣ የጦር ካምፖቻችንም
ታሪካዊ ስያሜ በማን አለብኝነት ለጐጠኞች ስያሜ ሲውልም ዝምታ ነገሰ ።
ዛሬ ደግሞ ከአዲስ አበባ ዋሺንግተን በሚመላለሱና ከዘመነኞቹ ጊዚያዊ የይሁኝት ፈገግታ በተቸራቸው የኛና የኔ
ቢጤዎች አማካኝነት የቬተራን አሶሴሽን እናቋቁማለን ፤ የአየር ኃይሉንም ታሪክ እንፅፋለንና ለዕርዳታ እጃችሁን
ዘርጉ የምትል የኢሜል መልዕክት ደርሳን በትዝብት ተደምመናል ። እስኪ ከበጐ መንፈስ የመነጨ ነው ብለን
እንመን ። ግን ሥጋት አለን !
የአየር ኃይላችንን ታሪክ ለትውልድ ዘግቦ ማስቀመጥ ምንኛ የተቀደሰ ዓላማ ነው ! የአቭዬሽን ቬተራን ማህበርን
ማቋቋምስ እንዴት ትልቅ ራዕይ አለው ? ነገር ግን የአንድ መንደር ልጆችን ዓላማ አድርጐ በጐጠኝነት ማማ ላይ
እየተንጠለጠለ እኛ እና እነሱ ፤ የቀድሞውና አዲሱ ፤ ዲሞክራቲኩና የአንድነት አርበኛ እያለ ሊለያየንና
ሊከፋፍለን ሌት ተቀን የሚተጋው ጐጠኛና ሽፍታ መንግስት የሚገነባውን ከእውነተኛው አየር ኃይል በቅጡ
መለያየት ያስፈልጋል ።
ውሃና ዘይትን ለመቀላቀል በማምሺያ እድሜ መባጀት ጉልበት ማባከን እንዳይሆን ! የነፃነት አርበኛው ጀ/ል ተጫነ
መስፍንና የሽፍቶቹ ጀ/ል አበበ ተ/ሃይማኖት (ጆቤ) በምን ተዓምር ለአንድ ዓላማ ሊሰለፉ ይችላሉ ?
በምንስ ሂሳብ የህ.ው.ሃ.ቱ. አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) የቬተራን አሶሴሽን መስራች ሆኖ በሸራተን አዲስ ይደግሳል ?
እነዚህ ሁለት ፍጥረታት ውሃና ዘይት ናቸው ። በዓላማም በራዕም አንድ አይደሉም ….. አሳዳጅና ተሳዳጅ !
ወንጀለኛና ወንጃይ … አርበኛና ባንዳ .. ውሃና ዘይት ናቸው ። ሊዋሃዱ አይችሉም ።
የእኛው አየር ኃይል በጅምላ ጨፍጫፊና ወንጀለኛ ተብሎ እንደ ጉም በተበተነበት ዘመን ላይ ተቆሞ ….. ለአገር
የደሙ ከያሉበት ታድነው በውርደት በየማጐሪያው ተወርውረው ልባቸው ተሰብሮና ጥሪት አልባ ሆነው በሰው
እጅ ላይ እንዲወድቁ በተበየነበት ዘመን ላይ ፤ ዛሬ ከሲሶው በላይ እውነተኛው አርበኛ አገር አልባ ሆኖና ተዋርዶ
አልጋ ላይ እየዋለ ያለ ደጋፊና አጋዥ ቀና ማለት ባቃተው ሰዓት ላይ የቬተራን አሶሴሽን እያቋቋምን ነው ሲሉንና
ግባታውን በገንዘብ እንድንደግፈው ስንጠየቅ እውን ለእውነተኛው የአየር አርበኛ አገልግሎት እንዲመስለን ይሆን ?
በእርግጥ ጥቂቶች ደም የተገበረበትን አርበኝነታቸውን ሳይሆን የሽንፈት ታሪካቸውን አሜን ብለው በመቀበል
በውርደት በጅምላ የተለጠፈብንን የጨፍጫፊነት ማንነት ፤ በተጨማሪም ለአገር በመሞታችንና ደማቸንን
በማፍሰሳችን ምክንያት እንደ ተራ ነፍሰ ገዳይ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኞች መሆናችንንና/መሆናቸውን
ዘንግተው “ ማምሻም እድሜ ነው “ በሚል የመሰንበት ጉጉት በድለላ እያግባቡን ማየታችን ከላይ በበጐ መንፈስ
ተነሳስተው ነው የሚለውን አቋማችንን እየሸረሸረብን ተቸገርን ።
ለመሆኑ በማን አየር ኃይል ….. በነማንስ ደም ይቀለዳል ?
የእነ ሚሽካ ባቢቼቭ አየር ኃይል …. የእነ ባህሩ ካባ አየር ኃይል …. የእነ ጀነራል አበራ ወ/ማሪያም …. የእነ ጀነራል
አሰፋ አየነ … የእነ ጀነራል አሰፋ ገ/እግዚ …. የነ ጀነራል ታዬ ጥላሁን ….. አየር ኃይል እንዴት ሆኖ ከዚህኛው ዘመን
ጋር ይዋሃዳል ?
እነ ጀ/ል ለገሰ ተፈራ ፣ ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስ ፣ ኰ/ል ታደለ አለሙ ፣ ኰ/ል ትርሲት ፣ ኰ/ል ወርቁ ፣ ሻ/ል
ጥላሁን በዛብህ ፣ መ/አ አባይነህ ኃይሉ ፣ መ/አ ደመላሽ መኰንን የመሳሰሉት በምርኰና በእስር መስዋዕትነት
የከፈሉበት ፤
የነ መርዕድ ዳጨው ደም …. የነ አማኑኤል አምደ ሚካኤል …. የነ ጥላሁን ኃይሉ ፤ የነ ለዊ ደሬሳ …. የነ መንግስት
ዓለሙ … የእነ ሊ/ካዴት ይኩኖ ታደሰ ጨቅላና አድገው ያልጨረሱ ልጆች ደም ፤ የነ ተስፋዬ ብ/ሥላሴ …. የነ
ማ/ቴክ ደገፋ ሆራ …. የነ ኰ/ል ጥላሁን ቦጋለ ….. የነ ሰለሞን መክብብ …. የነ አብረሃም ስንቄ ደም ላይ እንዴት
ዳንኪራ ይጨፈራል ?
እነ ጀ/ል ፋንታ በላይ …. ጀ/ል አመሃ ደስታ …. ጀ/ል ሰለሞን በጋሻው …. ጀ/ል ተስፉ ደስታ … ጀ/ል ንጉሴ ዘርጋው
… ጀ/ል ገናናው መንግስቱ …… እንዲህ ደማቸው ደመ ከልብ ይሁን ? ለአፍታ ቀና ብለው ቢያዩስ ምንኛ
በባልንጀራቸው ያፍሩ ይሆን !
ዘመናቸውን ሙሉ ለአገራቸው የአየር ክልል መከበር ጨርቄን ማቄን ሳይሉ …… ንብረት ማፍራት …. ሃብት ማካበት
…. ሚስት ማግባትና የአብራካቸውን ፍሬ ለማየት ሳይጓጉ እድሜያቸውን የጨረሱ የአየር ኃይሉ ጌጦችና የአገር
አለኝታዎች እንደ ወሮበላ ማጅራት መቺ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኛ በተሆነባት አገር ላይ እንዴት አይነቱ የአየር
ኃይል የአቪየሽን ቬተራን አሶሴሽን ይገነባል ?
እነ ኰ/ል ታከለ አበበ ፣ ሻ/ቃ አለማየሁ እሳቱ ፣ ሻ/ቃ ከበደ ጫኬ ፣ በላይነህ ተገኝ ፤ ደበበ ሞላ …. ደሳለኝ
ስሜነህ … …. ወዘተ በጉልበት ከአገር ተሰደው በበረሃ ላይ ያለ አልቃሽና ቀባሪ ነፍሳቸውን እንዲሰጡ ላደረገ ሽፍታ
፤ እነ ሻ/ል ፍሰሃ መለስን በእስር ቤት ለገደለ ወንበዴ እንዴት ብለን ክብራችንን ዝቅ አናደርጋለን ?
እነ ኰ/ል ብርሃነ መስቀል ፤ ኰ/ል ሰለሞን ከበደ ፤ ኰ/ል ግርማ አስፋው ፤ ሻ/ል ክፍሌ ውቤ ከእድሜያቸው ከሩብ
በላይ በእስር የገበሩበት ምክንያት ምን ይሆን ? ዘንግተነውስ ይሆን ?
እነ ማ/ቴክ ሽብሩን .. እነ ማ/ቴክ ፀጋዬ ሁሉቃን … እነ ማ/ቴክ ግርማ ሰቦቃንና የመሳሰሉትን በአጠቃላይ
አፕሬንቲሱን ፣ ኤርሜኑን ፣ ቴክኒሻኑን ፣ የአየር ፖሊሱን ፣ በራሪውን ፣ መኰንኑን ፣ ባሌ ላላ ማዕረግተኛውን
እንደ አሮጌ ቁና ሜዳ ላይ በትኖ በስተ እርጅና የሰው እጅ እንዲያዩ የተደረጉበትን እንደ ጨዋታ ቆጥረነው ይሆን ?
እነ ኰ/ል ብርሃኑ ከበደን ፤ ኰ/ል ብርሃኑ ውብነህ ፤ ኰ/ል ጣሰው ወዳጄነህን ….. ኰ/ል ጌታቸው መንገሻን ….
ኰ/ል መንገሻ ሁንዴን …. ኰ/ል የሺጥላ መርሻን ….. ኰ/ል ይልቃልን … አለማየሁ አጐናፍርን …. አለማየሁ ኃይሌን
…. ስንታየሁ አሽኔን … መስፍን መንግስቴን ….. በኃይሌ ደግፌን … ጂልቻ ዱራን …. ኰ/ል ነብዩን …. አሰፋ ተገኝን ፤
አቦነህ ነጋሽን … ዳዊት ወንዲፍራውን ፤ መስፍን ግርማን ……. በአጠቃላይ ስማቸው ያልተዘረዘሩትን የተዋጊውን ፣
የትራንስፖርትና የሄሊኮፕተር ስኳሮኖች በራሪና የቴክኒክ ባለሙያ ሲቪል ሰራተኞችን ሁሉ አገር አልባ አድርጐ …
እንዴትስ አይነት የአቪዬሽ ቬተራን ማህበር ሊመሰረት ይችላል ?
ጀነራል ተጫኔ መስፍን ደም ገብረው በአቀኑት አየር ኃይል ውስጥ አበበ ተ/ኃይማኖት አንዳችም የአየር ኃይል
ትምህርትና ዕውቀት ሳይኖረው የቬተራኖቹ አየር ኃይል አዛዥ ሆኖ በራሪ ተማሪዎችን ሲሸልም በአፍሪካ ውስጥ
በበረራ ሰዓታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው የተዋጊ አውሮፕላን በራሪና ኢትዮጵያን በተለያየ ጊዜ የተቃጣባትን ወረራና
ጥቃት በጀግንነት የመከቱ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጅ ጀነራል ተጫነ መስፍን በዚህ አይነት በአሳላፊነት
መታየታቸው ምን ያክል አገር አልባ እንደሆንን አያሳይ ይሆን ? እውን ታዲያ ይሄ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነው ?
እንደዚህ አይነት አገር የማታከብረው ቬተራንስ የት አገር ነው ያለው ?
ጀነራል ተጫኔም በዚህ አይነቱ ሁኔታ እራሳቸውን ለማሳነስ ባይፈቅዱ እንዴት ጥሩ ነበር ? እነ ጀነራል መስፍን …
ጀነራል ተሻለ … ኰ/ል ጥላሁን ነብሮን የመሳሰሉት ባለ ወርቅዬ ታሪክ ባለቤቶች እንደ አገር አልባና ሁለተኛ ዜጋ
ተገልለውና ተጥለው ያለ ፎቶ ግራፍ ይኖሩ የለ ?
በእርግጥ በዚህ ዘመን ጀ/ል ተጫነ ከአቻዎቻቸው በተለየ ሁኔታ ከነ ሙሉ ክብራቸውና ጥቅማቸው በአገራቸው
በቬተራን ማዕረግ እየኖሩ ያሉ ብቸኛ ሰው ናቸው ። ቀደም ሲልም እንደ ጀ/ል ተጫኔ ሁሉ ጀ/ል ሰለሞን በየነ
በዚሁ በተንቆጠቆጠው ማማ ላይ ተሰቅለው እንዳሉ እናውቃለን ፤ ይህ እንግዲህ የልደታ አየር ምድብ አዛዥ
ተደርጐ ተሹሞ የነበረውን ሻለቃ ተስፋዬ ተገኝን ሳንዘነጋ ፣ የሚሊታሪ አታቼውንና ጀ/ሉን ኃይለ ሥላሴ ገብሩንም
ማ/ቴክ ረዳዕይና ማ/ቴክ ክንድያን እንዲሁም ካላዩ አፅበሃንም በማሰብ ነው …….. ። በእርግጥ አድሎው አይን
ያወጣ ቢሆንም ከወደ ኰረም ፣ አዲግራትና አድዋ የመወለድ ጣጣ ነው እያልን ቆይተናእነሆ ምክር እንለግሳለን …….
የአየር ኃይላችንን ታሪክ መፃፉን እናበረታታለን ። ይሁን እንጂ …….
ዛሬ የሚፃፍ ካለ … አየር ኃይሉ እንዴት እንደተመሰረተ ብቻ ሳይሆን እንዴትም እንደፈረሰ ፤ ለአገር የደሙና የሞቱ
እንዴት እንደወንጀለኛ በየማጐሪያው እንደተጋዙ … ህብረ ብሄሩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዴት ወደ አንድ ዘር
የሽፍቶች ስብስብነት እንደተቀየረ የሚተርክ ካልሆነ …. ጀ/ል ተጫነ መስፍን ፣ ኰ/ል አስፋው አየልኝንና
የመሳሰሉትን የትውልድም የታሪክም ተወቃሽ ፤ የአገርም ክህደት እንዳይሆን ይታሰብበት ።
የአቭዬሽን ቬተራን አሶሴሽንም ከመመስረቱ በፊት አርበኛውን ከጐጠኛው መለየት ፤ እውነተኞቹን የአየር
አርበኞችና ቬተራኖች ከብቀላ ፍርደኝነታቸው ነፃ ማድረግና ዝነኛውን አየር ኃይል በጅምላ ከተለጠፈበት
የጨፍጫፊነት ስያሜ እንድናላቅቅ የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል ።
ጨረስን ።
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ ።
ትብብር ለመልሶ ማቋቋም
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል
Source-ethioforum.com

No comments:

Post a Comment