Sunday, December 22, 2013

የሕወሓት አደገኛ የዘረኝነት መርዝ እና የናዚ ፍልስፍና


ከመጀመርያው ዓለም ጦርነት ማገባደጃ ቦኋላ በጀርመን ማደግ ጀምሮ የነበርው ´´የናሺናል ሶሻሊስት ፓርቲ´´ የናዚ የፖለቲካ ዘይቤን በማስፋፋት ፣ የፋሺስቶች የቀኝ ክንፍ እንቅስቃሴ በዛን ወቅት በዋናነት ይታገል ፣ ይዋጋ ነበረው አንዱ ኮሚኒስቶችን ነበር ፡፡ እነዚህን ክፍሎች ዒላማ ካደረገበት ምክንያት አንዱ ፣ በወቅቱ በዓለማችን ዙርያ እየተጠናከረ የነበረውን ፣ የኮሚኒስቶች እንቅስቃሴ ለመቋቋምና ፣ በስራቸው እየተደራጀ የነበረውን የሰራተኛውን ክፍል (working class ) ከኮሚኒስቶች ነጥሎ በናዚስቶች ስር ለማሰለፍና ነበር ፡፡
የናዚ ፍልስፍና መሰረት ፣ የ አርያን ታላቅ ዘር (Aryan master race ) ከሌሎች የሰው ፍጠረት ዘሮች ሁሉ የላቀና ፣ የተመረጠ ሕዝብ እንደሆነ ያምናሉ ፡፡ እነሱ የሚሰጡትን ገጸ-ባህሪያት የማያሟላ ፣ እንደ ሰው ካለመቁጠራችወም በላይ ``በስህተት ወይም ሳይፈለጉ ተፈጥረው ``የተገኙ ነገሮች ተደርገው ስለሚታዩ ፣ መደምሰስ ወይም መጥፋት አለባቸው ብለው ያምኑ ነበር ፡፡ በዚህም የተነሳ ታሪክ እንደመዘገበው ከነሱ ዝርያ ውጪ ናቸው ብለው ፣ በተለያየ ዘርፍ የመደብዋቸውን ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን በየማጎርያ ካንፑና (concentration camp)፣ በየእስር ቤቱ እየተሰበሰቡ በሚያሰቅቅ ሁኔታ በጋዝ ጢስ ፣ በጥይት እሩምታና በተለያየ መንገድ እንደጨረሱዋቸውና ፣ ከፊሎቹንም ፣ በጣም አሰቃቂና ፣ኢ-ሰባዊ በሆነ መንገድ ፣ ሰውነታቸውን ለህክምና ምርምር ይጠቀሙባቸው ነበር ፡፡ ከዚያም አልፈው ሄደው፣ የሰውን ልጅ ክቡር ፍጡር ከእንሳት በታች አድርገው በመቁጠር ፣ ቆዳቸውን ለማስታዎሻ (souvenir) ለመብራት አንፖል ማጌጫና ፣ ለቤት ማሳመርያ ቁሳቁስ ይጠቀምባቸው እንደነበር ፣ ዛሬ ከነማስረጃው በተለያዩ የማጎርያ ካንፕ ፣ ሙዝየም ውስጥ ተቀምጠው ማየት ይቻላል ፡፡
እነዚህ ከአርያን ዘር ውጪ ያሉትን ፣ መፈጠር አይገባቸውም ነበር ብለው የመደቧቸውን ፣ ይሁዲዎችን ፣ ጂብሲዎችን ፣ የአዕምሮ ህመምተኞችን ፣ አካለ ስንኩላንን፣ ጥቁሮችን ፣ ከነሱ ሃይማኖት ውጪ ያሉትን ፣ እንደ የጆሃቫ እምነት ተከታዮችን ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውንና ፣ የተለየ ጾታዊ አቀራረብ እምነት የነበራቸውን ፣ ከሰባዊ ማንኛውም ፍጡር በታች አድርገው ከማየታቸውም በላይ እንደ የግል መገልገያ ቁሳቁስ አድርገው ፣ አዕምሮዋችን መገመት ከሚችለው በላይ ፣ ኢሰባዊ ድርጊት ይፈጽሙባቸው ነበር ፡፡ የፓርቲ መመሪያቸውም ከላይ የተዘረዘሩትን ከነሱ ውጭ የተፈጠሩትን ፣ የማጥፋት መብት እንዳላቸው ተደርጎ እንዲታመንበት ተቃኝቶ የተዘጋጀ ንድፈ -ሃሳብ ወይም የፖለቲካ ዘይቤ( ideology) ስለነበር ፣ አብዛኛው ሕዝባቸውን በዚህ ፍልስፍና አሳምነው ፣ አሳስተው ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ነበር ፡፡
አርያን የሚለውን ፣ ቃሉን መጠቀም የጀመሩት ሰዎች ፣ ለዚህ የዘረኝነት ተግባር መጠርያ ለማድረግ ሳይሆን ፣ ለአንድ አካባቢ ሕዝብ (ፖርቶ ፣ ኢንዶ አውሮፓውያን ...ወዘተ) መጠርያ ወይም መለያ ለማድረግ ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ናዚዎች ይህንን እውነታ ቀይረው ፣ ትክክለኛ ሕዝብ ማለት በነሱ በነሱ እምነት ፣ ነጭ ፣ ሰማያዊ የዓይን ቀለም ያለውና ፣ ወርቃዊ ቀለም ጸጉር ያለውና ፣ (white, blue eyes and blond hair) የነሱን የፖለቲካ መስመር የሚከተል ...ወዘተ ብለው ያምናሉ፡፡
ይህ አደገኛ በታሪካችን የሚታወቅ በዓለም ሕዝብ ላይ ያደረስው እልቂት ፣ ያስከተለው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት በግልጽ ከመታወቁም በላይ ፣ ዛሬም የነሱ ርዝራዦች ፣ በተለያየ ቅርጽ ፣ እንደ አዲሱ የፋሺስት ንቅናቄ (neonazi´s ) እና ፣ በአውሮፓ በህጋዊ የፖሊቲካ ሽፋን ስር ተደራጅተው በግልጽ ይንቀሳቀሳሉ ፡፡ ቅርጻቸውንና ፣ ዘዴያቸውን በመቀያየርና ፣ ያለውን ዲሞክራሲያዊ ህጋዊ መንገድ እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ እጅግ ወደ ቀኝ ያጋደለ የዘረኛነትን ዓላማ ፣ የሚያራምዱ ፣ ይፋዊና ፣ ህቡዕ የፖለቲካ ድርጅቶች በማቋቋም እስካሁን ድረስ፣ በምዕራቡ ዓለም በይፋ ሲንቀሳቀሱ እናያለን ፡፡ አንዳንዴ በዓለም ዓቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ፣ የሃገራቸው ኤኮኖሚ ሲዳከምና ፣ ችግራቸው ሲጠና ፣ ተራውን ሕዝባቸውን ፣ ለዚህ ችግር ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ፣ የውጪ ዜጎችን ወደ ሃገራቸው ባብዛት መግባትና ፣ የነሱን ሕዝብ ስራና ጥቅም ስለሚካፈሉ እንደሆነ አድርገው ምክንያት እየሰጡ ፣ በተለይ በቀውሱ የተጠቁትን ያሳምኗቸዋል ፡፡
ሕዝብ እነሱን ቢመርጥ ፣ የውጪ ዜጎችን አባረው ፣ ለነሱ የሚጠፋው ንዋይ ለሃገራቸው እንደሚያውሉና ከችግር እንደሚያወጧቸው ቃል ይገቡላቸውል ፡፡ በዚህ የምርጫ አጀንዳ በለስ ቀንቷቸው ስልጣን ሲይዙ ፣ አዳዲስ ጸረ የውጪ ዜጎች ህጎች በማውጣት ከነሱ የተለየ ዘር ፣ ቀለምና ፣ የሃይማኖት እምነት ያላቸውን ፣ የሃገሪቷ ዜጎች ባልሆኑት ላይ ፣ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ፣ ሃገራቸውን ጥለውላቸው እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ያሳድራሉ ፡፡ ይህ በተለይ እንደ
ብዙዎቻችን ሃገራችንን ጥለን በተሰደድነው ዜጎች ላይ የሚያደርሱብን መንፈሳዊ ጫናና መሸማቀቅ ቀላል እንዳልሆነ እናቀዋለን ፡፡
የናዚዎች የፖለቲካ አካሄድ ከነሞሶሎኒ ፋሺስቶቹ ጋር ብዙ የሚጋሩት እምነት ስለነበራቸው፣ በሃገራችንም ለአጭር ጊዜም ቢሆን ፣ በፋሺስት ወራሪ ጠላት በግድ ተጭኖብን ከነበረው የዘረኝነት ህግና ፣ በወቅቱ በነበሩት ወገኖቻችን ላይም ሆነ በሌሎች ሃገሮች ላይ ይደርስ የነበረው መከራ ስንሰማ ፣ ዘረኝነት ምን ያህል አስከፊ ገጽታ እንደነበረው ከወላጆቻችንና በአህጉራችን ላይ በዚህ ጨካኝ የዘረኝነት ስርዓት ውስጥ ካለፉት ሃገሮች ታሪክ ብዙ ተምረናል ፡፡
በሃገራችንም ፣ በአንዳንድ ኋላ ቀር ባህላችንንና ፣ ካለማወቅ ፣ ከብዙዎቻችን የተለየ የአኗኗር እምነት፣ ልዩ ሙያዊ ተሰጥኦ የነበራቸውን ፣ ወገኖቻችንን ፣ ቡዳ ፣ ፋቂ ፣ ቀጥቃጭ፣ መጫኛ ነካሽ ፣ .....ወዘተ እየተባለ አንዱ ከሌላው የተሻለ ወይም ያነሰ ሆኖ የሚታይበት ፣ የዘር ፣ የሙያና ፣ የእምነት አድሎዋዊ አካሄድ ስለነበር ፣ ከነዚህ ወገኖቻችን ጋር ፣ በጋብቻና በማህበራዊ ኑሮ የማንቀላቀልበት ፣ አሳፋሪ ባህል ነበረን ፡፡ ሆኖም ይህንን አስቀያሚ ባህል ፣ ባለፉት ዓመታት በሂደት ፣ በዓለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርት ፣ በሕገ-ደንባችን ...ወዘተ ፣ ለማስወገድ እየተጣረ ነበር ፡፡
ሆኖም ካለፉት 21 ዓመታት ወዲህ ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ቦኋላ ፣ ጎጠኝነት ሕጋዊ ሽፋን ተሰጥቶት አንቀጽ ወጥቶለት ፣ በአዋጅ አጊጦ ፣ ሕዝባችንን ዘረኛ በሆነ ፣ ጎጥንና ቋንቋን መሰረት ባደረገ ``ፌደራላዊ አስተዳደር`´ በሕዝባችን ላይ በሃይል ጭኖ ለየት ባለ መልክ ተኳኩሎ ቀረበልን ፡፡ የህንን የማይቀበሉ ወገኖቻችንን ሲያሳድድ ሲያጠፋና ፣ በግልጽ ኢፍትሃዊ -የዘረኛነት አካሄድ ሲከተል እድሜያችንን አጋምሰናል ፡፡ ይህ ዘረኛ ስርዓት ከተዘረጋ ቦኋላ ፣ ለረዥም ዘመናት አብሮ በኖረ ሕዝባችን ማሃል ፣ በዘመናችን አይተን የማናውቀው ፣ የጎጥና ፣ የሃይማኖት ጥላቻ ውስጥ ለውስጥ በአገዛዙ ፣ እንደ ፖሊሲ እየተነደፉ ልዩነትን በማስፋፋት ፣ እርስ በእርስ ከፋፍለው ፣ አዳክመውን የነሱን ሥርዓት ለማራዘም ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ሆንዋል ፡፡
ይህ በአገዛዙ ፣ ዘዴውንና ፣ ቅርጹን እየቀያየረ ፣ ተራ በተራ በሕዝባችንና ፣ በዕምነታችን መሃል ጣልቃ እየገባ እርስ በእርስ በማናቆር ያደርስ የነበረው ችግር በመጠኑ ተሳክቶለት ቢሆንም ፣ በእቅዳቸው መሰረት እንደፈለጉት ገና አልተሳካም ፡፡ ይህ ተንኮል የገባቸው ክፍሎች እንዲያውም በተቃራኒው ፣ አልፎ አልፎም ቢሆን ፣ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶችና ፣ በፖለቲካውም መስመር ፣ አብረው ተቃውሞዋቸውን ማሰማት ጀምረዋል ፡፡
ይህ ፍልሚያ ቀጣይነት ባለው መንገድና ፣ በተሻለ በተቀናጀ ዘዴ እየተደራጀ ፣ እየተሰባሰበ ፣ ትግሉን አስተባብሮ ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣት እየተካሄደ ያለው አዝማሚያ ግን ገና አስተማማኝ ባይሆንም፣ ጅምሩ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡
ምክንያቱም ፣ አብዛኛው የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ ውስጥ ለውስጥ እያደገና ፣እየተስፋፋ የመጣውን የዘረኝነት አደጋ አሳሳቢ ደርጃ ላይ መድረሱን አልተቀበሉም ፡፡ በዚህም ምክንያት አገዛዙ በቀላሉ ይወገዳል ብለው ስለሚያምኑ ፣ አብዛኛው ጉልበታቸውን የሚያጠፉት ፣ የሌለ የምርጫ ውድድር መድረክ እንደተፈጠረ ፣ እኔ እበልጥ ፣ እኔ እበልጥ አይነት ፉክክር በማድረግ ነው ፡፡ የአንድነቱ ክፍል ነኝ ከሚለው ፣ በተሻለ የጎጥ ፖለቲከኞቹ እየተቀናጁና ፣ እየተደራጁ፣ እየተቻቻሉ ፣ አጀንዳቸውን በማገባደድ ላይ ናቸው ፡፡ ባጠቃላይ ለአንድነት ቆምኩኝ የሚለው ክፍል ፣ ይህንን አደጋ አጢኖ ስላላየው ፣ በወሬ ፣ ስለ ሕብረት ፣ ጥምረት ፣ ውሕደት ፣ አስፈላጊነት ከመቆዘም ውጪ ፣ ተቻችለው የእውነት ተባብረው ለመቆም ገና አልወሰኑም ፡፡
አንዳንድ የምናያቸውም ሙከራዎችም ፣ በራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ዙርያ የሚቀራረቡ ፣ ለስልጣን ክፍፍልና ፣ ሚዛን ለመድፊያ የተማከለ ሆኖ ፣ በአዕምሮዋቸው ለፈጠሩት ``የምርጫ ውድድር`` የተነደፈ እንጂ ፣ በእውነት ይህንን ስርዓት ለማስወገድ ተፈልጎ ፣ለጊዜው ልዩነትን ፣ ለእውነተኛ የምርጫ ጊዜ አቆይቶ ፣ መጀመርያ ሃገራችንን ከአንባገነናዊ ሥርዓት ነጻ ለማውጣት ተብሎ ፣ ተቻችሎ አብሮ ለመቆም የታለመ አይደለም ፡፡ እንዲያውም አሁን ፣ የኅብረት አሰባሳቢዎቹ ብዛት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ቁጥር አልፎ ሊሄድ ስለሆነ ፣ ለነሱም ሌላ ``የኅብረት አሰባሳቢ `` ቡድን ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ መገመት አይከብድም ፡፡
የአገዛዙ ዓላማው ፣ የጎጥ ፖለቲካን በሕዝባችን መሃል ማስፋፋትና ፣ ይህም ቦኋላ ሊያስከትል የሚችለውን የመገነጣጠል አደጋ ያሰጋናል እስካልን ድረስ ፣ በማንኛውም መንገድ ይህንን ከፋፋይ ሥርዓት ተባብሮ ለማስወገድ አለመጣር፣ ወይም እነሱ በሚሄዱበት መንገድ እየተጓዝን የችግሩ ተባባሪ መሆን ፣ መሀከል ምንም ልዩነት የለውም፡፡ የዚህን አደጋ ክብደት መቀበል ካልፈለግን ፣ ምርጫችን የሕዝባችንን ስቃይ ማርዘም ፣ አገዛዙ እንዲቆይ መርዳትና በመጨረሻም ፣ ለሃገራችን መበታተን ምክንያት መሆኑን መቀበል አለብን ፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዋናው ዓላማ ፣ ከላይ በአጭሩ ጠቅሼ ለማሳየት የሞከርኩት ፣ በሃያኛው ክፍለዘመናችን በጀርመን ተከስቶ የነበረው አስቀያሚ የናዚ /የፋሺስቶች የዘር አድልዎ ፖሊሲ ምልክቶቹን ፣ በሃገራችን ፣ በአንዳንድ በተቃዋሚው አካባቢ ባሉም ምሁራንም ጭምር ፣ በአንዳንድ ድህረ-ገጾችና የፓልቶክ የመወያያ ክፍሎች ሲሰሙና ፣ ሲንጸባረቁ ያየሁትን አደገኛ አዝማሚያ፣ ስጋቴን ለወገኖቼ ለማካፈል እንጂ ፣ ባለሙያው ሆኜ አንባቢያንን ለማስተማር አይደለም፡፡
የናዚዝም ፣ ወይም እራሳቸውን የአርያን ማስተር ሬስ (Aryan master race ) ብለው የሚጠሩት ዘርኞች ዋና መለያ አካሄዳቸው ፣ የሌላውን ሰው ሕልውና መካድ ፣ በሕዝብ መሃል ያለውን ታሪካዊ ትስስርን አለመቀበል ፣ ከአንድነቱ ይልቅ በልዩነቱ ላይ ማተኮር ፣ በሕዝቦች መሃል አጥር ማጠር ፣ የግንኙነቱን ድልድይ ማፍረስ ፣ በሰዎች ልጆች መሃከል ሰፊ የማበላለጥና ፣ ሚዛኑ የተንሻፈፈና ቅጥ ያጣ የወገንተኛነት አካሄድ ማስፋፋት ነው ፡፡
ይህ አይነት ግልጽ የዘረኛነት አካሄድ ፣ ትላንት የወያኔው መሪ ፣ `` ከወርቅ ዘር በመወለዴ እኮራለሁ `` ያሉን ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የማበላለጥ ዘረኛ ዓላማ ስንቃወም ሰንብተን ፣ ዛሬ ደግሞ ፣ አውቀው ሆነ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ሳያጤኑት ፣ እንደዚህ አይነት ከፋፋይ ፣ የፋሺስት ዘረኛ ፖለቲካዊ ቋዋንቋ ማሰማት የጀመሩትን ፣ ቁጭ ብሎ ማዳመጥ እየተለመደ መምጣት ጀምሮዋል ፡፡
ዛሬ ከአንዳንድ ተቃውሞን እናስተባብራለን ከሚሉ ፣ ሊያስወግዱ ከሚፈልጉት ስርዓት ባልተለየ መንገድ እየተጓዙ ፣ ቆመንለታል የሚሉት ሕዝብ ያልጠየቃቸውን ፣ እሱ ከሌላው የምበልጥ ነኝ ያላለውን ፣ እሱ ያልፈለገውን በስሙ እንወክለዋለን እያሉ ፣ በሕዝባችን መሃል ፣ ጥላቻንና ፣ መራራቅን የሚጋብዝ ፣ አላስፈላጊ ማበላለጥ ፣ ባልተለመደ መልኩ ሲካሄድ ስንሰማ ፣ ከማሳዘኑም በላይ እያሰጋን ሄድዋል ፡፡
በአንድ የታሪክ ሂደት አስገዳጅነት በተከሰተ ሁኔታም ይሁን ፣ ተፈጥሮ በቸረው ልዩነት ፣ እንደ ጌጣችን ልናየው ፣ የሚገባን ታሪካችንን ፣ አንዱ ከሌላው ፣ የተመረጠ ፣ የተሻለ ፣ ቆንጆ ፣ ጸጉረ ዞማ ፣ አፍንጫ ሰልካካ ፣ ጎበዝ ተዋጊ ፣ ታላቅ ሕዝብ ፣ ወርቅ ሕዝብ .......ወዘተ የመሳሰሉ ፣ በጣም ኋላ ቀር የሆኑ ዘረኛ ፣ ቅጽላዊ ማበላለጦችን በሕዝባችን መሃል ፣ በአለንበት በሃያ አንደኛው ዘመን ማዳመጡ ጆሮ ያሳምማል ፤ አንገት ያስደፋል ፣ ተስፋ ያጨልማል ፡፡ ይህ አይነት አላስፈላጊ ወገንተኝነት ፣ ቆመንለታል ለሚሉት ክፍል ከሌላው ወገኑ እንዲነጠልና ፣ የጥቃት ኢላማ እንዲሆን ከመርዳት ባሻገር የሚጠቅመው ነገር የለም ፡፡
በእርግጥ በማንኛውም ወገናችን ላይ በተናጠል የሚደርሰው ፣ በጎም ይሁን ጉዳት የጋራችን መሆኑን መቀበል አለብን፡፡ የማንኛውም ክፍል ወጋናችን በተናጠልና በተራ በሚደርስበት ፣ መሰቃየት ፣ መታሰር፣ መፈናቀል ፣ መጋዝ ፣ መዋረድ ፣ ለሌላውም ህመም ሆኖ ሲሰማው ኖርዋል ፡፡ ለመፍትሄውም አብሮ ተዋድቋል ፣ ታግሏል ፣ አብሮ በደም የተሳሰረ አንድነት ገንብቷል ፡፡ ያም እየተደናቀፈም ቢሆን ወደፊ ይቀጥላል ፡፡
በተለምዶ ፣ በአባቴ የትውልድ ሃረጌ የዚህኛው ዘር ነኝ ፣ በእናቴ የዚያኛው የእከሌ ወገን ነኝ እንደምንለው ሁሉ ፣ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን ከአማራውም ፣ ከኦሮሞውም ፣ ከሃዲያውም ከሁሉም የሐገራችን ሕዝብ ጋር ትስስር ስላለን ፣ የትኛውም ወገናችን ፣ በተናጠልም ይሁን በጋራ ለሚደርስባቸው ጥቃት፣ የራሳችን ጥቃት መሆኑ ተሰምቶን፣ ከማንኛውም የተገፋ ወገናችን ጎን ቆመን ጥቃቱን በጋራ ልንከላከል ይገባል ፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ሁላችንንም የሚያገናኝ ማእከል ነው ካልን ? እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ዶርዜነት አለብኝ፣ በኢትዮጵያዊነቴ አፋርነት አለብኝ ፣ በኢትዮጵያዊነቴ አማራነት ፣ በኢትዮጵያዊነቴ ኦሮሞነት ....ወዘተ አለብኝ ብለን አምነን ፣ በተግባር በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ አብረን ተደጋግፈን ስንቆም ነው ፣ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነታችንን በተግባር የምናስመሰክረው፡፡
አንዳንዴ ሰዎች እራሳቸው ባልመረጡት መንገድ እንዲሄዱ ፣ ስለሚገፉ ፣ ሰዎች በተናጠል ለሚደርስባቸው ጥቃት እራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ፣ የሌላውን ህልውናና ፣ መብት እስካልተጋፉና ፣ ላጠቃላዩ ሕብረት ችግር እስካልሆኑ ድረስ ፣ በሚያመቻቸው መንገድ የመታገል መብታቸውን መቀበል ብቻ ሳይሆን ማገዝና ፣ ከጎናቸው ሆኖ ብቻቸውን አለመሆናቸውን ማሳየት ወገናዊ ግዴታ ነው ፡፡
ይህ አይነት ወገናዊ ትብብር ፣ ለየብቻ መፍትሄ ፍለጋን ለማበረታት ሳይሆን ፣ የላላውን ለማጥበቅ ፣ የራቀውን ልብ ለማቅረብ ፣ የተጎዳውን መንፈስ ለመጠገን ፣ ይበልጥ የሚያስተሳስረን ፣ በሂደት የገነባነውን በጎ ትሪካችንን የሚንከባከብና ፣ የማይጠቅመንን አስወግደን ለሃገራችን አንድነትና ፣ ለሕዝቦቿ እኩልነት ለሚደረገው ትግል ጽኑ የአንድነት መሰረት እንደሚገነባ በማመን ነው ፡፡
ለሰባዊ መብቶች (human rights)መቅደም ስንታገል ፣ ዘር ፣ ሃይማኖት ፣ ቀለም ፣ ጾታ ፣ ታላቅነት ፣ ጀግነት ፣ የመሳሰሉትን ``እንደ መለኪያ `` አስቀምጠን ሳይሆን ፣ ወይም በቡድንና ፣ በግለሰብ የተደራጁና ያልተደራጁ በሚል ስሌት ከፋፍለን ሳይሆን ፣ በዚህ ምድር ላይ ለተፈጠረ ፣ ለሰው ልጅ የተሰጠው ተፈጥሮዋዊ መብቱ የተጣሰ በመሆኑ ብቻ ነው ፡፡
በሌላው ወገናችን ላይ የሚደርሰው፣ እስር፣ እንግልት ፣ መፈናቀል ፣ የሚሰማን ፣ የእኛ በምንለው ላይ ብቻ ሲደርስ ከሆነ ? የሌላው ወገናችን ስቃይና መከራ ፣ እንደራሳችን የማይሰማን ከሆነ ? ሕዝባችንን ያስተሳሰረውን ሰንሰለት እየበጣጠስን ፣ ለጎጣችን ፣ ለመንደራችን ፣ ብቻ የምንጨነቅ ከሆነ፣ በእውነት እንደ ናዚዎቹ ፣ በዘረኞች በሽታ እንደተለከፍን መቀበል አለብን ፡፡
ትላንት ያልተመችን ፣ ሌሎች ብቻቸውን የሄዱበት ጸረ አንድነት የጥፋት መንገድ ነበር ብለን አሁንም የምናምን ከሆነ ? ፣ ይህንን አካሄድ እኛ ስንደግመው ልክ የሚሆንበት መንገድ ስለሌለ ፣ የምንከተለው የትግል አቅጣጫ ፣ ለጋራ ችግራችን ወደ የጋራ መፍትሄ የሚያደርሰ መንገድ የሚያመቻችልን እቅድ ስንነድፍ ነው ፡፡ በጋራ ታግለን ፣ የምናመጣው ሰላም ፣ ዕድገትና ፣ ፍትህ የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የብዙውን ፣ አለ የምንላቸውን ችግሮቻችንን መፍቻ ቁልፍ ስለሆነ ፣ በየትኛውም አቅጣጫ የምናደርገው ግፊት ፣ ወደ እዚህ አቅጣጫ አቅርቦ የሚያሰባስበን መሆን ይኖርበታል፡፡
የሕዝባችን ጥያቄም ባይሆን ፣ ለረዥም ጊዜ ፊደል በቆጠረው ጎጠኛ (elite) እንወክለዋለን ብለው ወደ ሕዝባችን በሚገፉት አጀንዳ የተጎዳው አንድነታችንን ለመጠገን ፣ በተመሳሳይ መንገድ በእልህ መሄድ ፣ እነሱን መተባበር እንጂ ለሃገር እንደማይጠቅም መታወቅ አለበት ፡፡ በእልህ የሚወሰድ አቅዋም ፣ ለማንኛችንም የሚበጅ አይሆንም ፣ ይበታትነናል፣ በዚህ ደግሞ ማንም አይጠቀምም ፡፡ በሳይንስ እንደተረጋገጠው ፣ ስሜታዊነት ሚዛኑ በዝቶ ካጋደለ ፣ ዕውቀት ወይም ጥበብን የያዘው የአዕምሮ ክፍላችን ስራውን ይቀንሳ፡፡(when emotions is high intelligence is low) የዚህም ውጤት የሚያስከትለውን አደጋ ለማስረዳት አንባቢዎቼን መናቅ ይሆንብኛል ፡፡
ወደድንም ጠላንም የመገንጠልን ዓላማ በሚገፉ ጎጠኛ ኢሊቶችና ፣ በሥርዓቱ ተባባሪነት ይገፋ የነበርው የዘረኞች ዓላማ ፣ ወደ ሕዝባችን እየገባ ፣ ከምንገምተው በላይ እየተራባ ፣ በብሔራዊ አንደንታችን ላይ አደጋ እንዳንዣበበ ያስተዋሉት ጥቂቶች ናቸው ፡፡ የአንድነቱ ደጋፊዎች ነን ከምንል ፣ የጎጥ ፖለቲካ አራማጆች በተሻለ እይተደራጁ ፣ እየተሰባሰቡ እንደሆን መካድ የዋህነት ነው ፡፡
ሕዝብ ደግሞ ፣ መሪ እስከሌለውና ፣ አደራጅቶ ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚመራው እስከሌለው ድረስ፣ ቁጥሩ ስለበዛ ምንም ሊሰራ አይችልም ፡፡ በተግባር የምናየውም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝባችን ብቻውን እንደተውት ነው፡፡ በዚህ ላይ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ በቀጣይነት በሚፈስለት ጥንፈኛ አመለካከት አይሳሳትም ማለት አይቻልም ፡፡ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚ ፣ ሕዝብ የተሳሳተ አቅዋም ሊወስድ እንደሚችል በተደጋጋሚ ታይቷል ፡፡
በእነዚህ ጎጠኛ አስተሳሰብ ባላቸው የሚገፋውን የዘረኝነት ጥፋት ፣ እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ አቅዋም እንደሆነ አድርገን ተስፋ ቆርጠን ፣ በወገኖቻችን ላይ ዕምነት ማጣት የለብንም ፡፡ እንደዛ ማመን የጀመርን ከሆነ ፣ ለጎጠኞች እጅ እየሰጠን እንደሆነና ፣ እኛም የችግሩ ተባባሪ መሆን እንደጀመርን ማመን አለብን ፡፡ በሕዝባችን የሚቀርበው መሰረታዊ ጥያቄና ፣ የተማረው (ኢሊት) በሚፈጥረው ችግር መሃከል ያለውን ልዩነት ማስመር ካልቻልንና ፣ ሁለቱን ካምታታን ፣ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እንዳይወስደን መጠንቀቅ አለብን ፡፡ እየመጣ ያለውን ችግር አቃለንም ሆነ አጋነን ሳናየው ፣ እንደ ሁኔታው ቅደም ተከተል ተደራጅተን ልንታገለው ይገባል፡፡
ያለው አገዛዝ ፣ የጎጠኞችን ፍላጎት በእጥፍ አጩሆ የሚያደነቁረን እንጂ ፣ የአብዛኛውን ፣ አንድነቱን የሚፈልገው ሕዝባችን ድምጽ ስለታፈነ ፣ ባለመስማታችን ልንጠራጠር አይገባም ፡፡ የሕዝባችንን እውነተኛ ፍላጎት በተለያየ አጋጣሚ ቀዳዳ ሲያገኝ አሳይቶናልና ፣ አሁንም ምንም የተለወጠለት ዓዲስ ነገር ስለሌለ ትግሉ ይቀጥላል ፡፡ እስሩ ፣ እመቃው ፣ ችግሩ ፣ ስደቱ ፣ እንደቀጠለ ሆኖ ፣ አሁንም አብዛኛውን ክፍል ያገለለ አንባገነናዊ ሥርዓት በሰፈነበት ሁኔታ፣ ከመታገል ሰንፈን ፣ እንዲሆንልን የምንመኘውን ፣ ከላይ እንዲፈቀድልን በተስፋ ደጅ እየጠናን ተጃጅለል ማጃጃሉ አይጠቅመንም ፡፡
ካለፈው እንኳን የቅርብ ታሪካችን ፣ ይህ ሥርዓት ሁሌ ግፊት በሚደርስበት ወቅት ፣ ``ለመደራደር `` በሚል ስንት አዛውንቶች ፣ ስልጣን እንቁልልጭ እያላቸው ፣ ሰነድ እያስፈረመ ፣ ከሕዝብ አጋጭቶ ሁኔታውን ፣ በግልባጩ ለራሱ እንደተጠቀመበት መርሳት፣ ትልቅ የፖለቲካ የዋህነት ነው ፡፡ መደራደር የሚባል እንኳን ነገር ቢኖር ፣ ትግልን ሳያቀዘቅዙ ፣ ትጥቅን ሳያላሉ ፣ በስልት ግፊት በማሳደር እንጂ ፣ የገነባነውን የትግል ስሜት እራሳችን ከናድንለት ቦኋላ ፣
ተርግጦ መገዛት እንጂ ፣ አገዛዙስ ለምንድነው ለመደራደር የሚፈልገው? ለዛውም እኛው መላ እየመታንላቸውና ፣ እየተረጎምንላቸው እንጂ ፣ ከእነሱ የሰማነው ምንም ተስፋ የለም ፡፡
እንዲያውም አገዛዙ ከሃገራችን አልፎ እጁን አርዝሞ ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በየስርቻው ለአድር ባዮች እየዘራ፣ በጅት መድቦ፣ ያሰማራቸውን የውሸት ተቃዋሚዎች ፣ ``በየስብስቡና፣ በየሕብረቱ `` ውስጥ እየጠቀጠቀ አመራሩን በራሱ ሰርጎ ገቦች ሊያሲዝና ፣ መድረኩን ሊያጣብብ ሲሞክር እየታዘብን ነው ፡፡ ይህ ቀድመው መድረኩን ይዘው ሊሰራ ባማይችል መንገድ ጀምረው ካኮላሹት ቦኋላ ፣ ሰዉ ተስፋ ቆርጦ ሁለተኛ የእውነቱንም እንዳይሞክር ፣ ወይም በእውነቱ እና እነሱ በፈጠሩት መሃከል የተምታታ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ነው ፡፡
እነዚህ ሰረገው የሚያስገብዋቸው የሰለጠኑ አደናባሪዎች ፣ መንገድ ለይ እንደተንጠለጠለ የሕዝብ ቴሌፎን ፣ ገንዘብ እያቃሙዋቸው ፣ በቀሚስና ፣ በንዋይ እያባበሉዋቸው የሚያስለፈልፋቸው ፣ አስመሳይ ተቃዋሚዎች አንዱ እግራቸውን ጠላት ሰፈር ፣ ሌላውን ተቃዋሚው ሰፈር ተክለው ፣ እንደ ቱቦ አስተላልፉ የተባሉትን ውዥንብር (disinformation) በመረጃ ስም እየበተኑ ፣ አሁንም የተቃዋሚው ክፍል ተጠናክሮ እንዳይደራጅ የሚችሉትን ሁሉ እንደቀድሞው ለማደናገር ሲሞክሩ የምናየው ነው ፡፡ ተቃዋሚውም ፣ ማን ምን እንደነበር የራሱ (trackrecord) ስለሌለው ፣ ትላንት ከውስጣችን ወጥተው ፣ አስር ጊዜ እየካዱን ሲመለሱ ፣ የሚቀበላቸው በእቅፍ አበባ ነው ፡፡
ከአዲሱም ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በትክክል በሚገባን ቋዋንቋ የሰማነው ነገር ቢኖር፣ ሊመልሱ የተዘጋጁት የሕዝባችንን ጥያቄ ሳይሆን ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የጀመሩትን ``ራዕይ`` በተጠናከረ መንገድ እውን ማድረግን ነው ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወጥቶ ``የሃዘናቸው ተካፋይ መሆኑን`` ለዓለም ሕዝብና ፣ ለእኛ ሊያሳዩን ሲነሱ ፣ ከፍተኛ ድጋፍ አለን ፣ በጀመርነው መንገድ እንቀጥላለን ማለት መሆኑን የማይገባን ከሆነ ፣ አስተርጓሚ ሊያስፈልገን ነው ፡፡ ወይንም አንዳንዶች በሌላ ዘረኛ ስሌት ሊነግሩን እንደሚፈልጉት `` ችግራችን ሥርዓቱ ሳይሆን ፣ የመሪው ማንነትና ፣ የመጣበት ክፍልን ነበር የምንቃወም`` ብለው በግልጽ ይነግሩን እንደሆን እንጂ፣ ተስፋ ማየት ገና ምንም አልጀመርንምና ለገላጋይነት አንጣደፍ ፡፡
ባጠቃላይ ይህን ሁሉ ዘርፈ ብዙ የጋራ ችግራችንን፣ ለማስወገድና አደጋውን ለመከላከል የምንችለው፣ ባልሆነ ተስፋ እራሳችንን በማታለል ፣ ወይም በእልህ እነሱ በሄዱበት የጎጥ መንገድ በግልባጩ ተጉዘን ሳይሆን ፣ ሰከን ብለን ፣ ትግላችንን ሳናቀዘቅዝ ፣ ትጥቃችንን ሳናላላ ፣ ለዋናው ብሔራዊ ደህንነታችን ስንል መለስተኛ ልዩነቶቻችንን በይደር አቆይተን ``cease-fire`` ይህች ሓገር እንደ ሃገር እንድትቀጥል የምንፈልግ የአንድነት ሃይሎች ፣ ጋባዥ ሳይጠራን ፣ አስተናጋጅ ሳያስፈልገን፣ ግርግር ፣ ድግስ ፣ አሜሪካ ኦባማ እያልን ``መቀላወጥ`` ሳናበዛ ፣ እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ፣ ተፈላልገን ፣ ተጠቃቅሰን ፣ ተሰባስበን ፣ ተደራጅተን፣ ብሔራዊ አጀንዳችንን ቀርጸን በጋራ አምርረን መታገል ስንጀምር ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ሁሌ በራሱ መንገድ ይጠብቃታል ፡፡ብስራት ኢብሳእኛም በቀና የአንድነት መንፈስ እንተባበረው ፡፡http://minilik-salsawi.blogspot.com/2012/09/blog-post_7748.html?spref=fb

No comments:

Post a Comment