Sunday, December 22, 2013

ከ35 ሚ.ብር በላይ በሙስና አከማችቷል የተባለ የጉምሩክ ኃላፊ ተከሰሰ


የአዳማ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የህግ ማስከበር ሃላፊ የነበረው አቶ ተመስገን ጉላን በራሱና በወንድሙ ስም ከገቢው ጋር የማይመጣጠን ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እና ንብረት ይዞ በመገኘቱ ክስ የቀረበበት ሲሆን በፖሊስ ክትትል ስር የነበረው ወንድሙም ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ቀርቦ ክሱ ተነቦለታል፡፡ ቀደም ሲል ተከሳሹ ሁለት ዶዘሮችን በ15ሚ.ብር መግዛቱን ደርሼበታለሁሲል አቃቤህግ መግለጫ መስጠቱ ይታወሣል፡፡ 
የ33 ዓመቱ የህግ ማስከበር ሃላፊ አቶ ተመስጌን ጉላን ዓለሙ፣ በሌላ ስሙ ተመስገን ስዩም አሰፋ፤ ሁለት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን በግብረአበርነት በተያዙት የወልደሚካኤል ሃለፎም አጠቃላይ አስመጪና የፈሣሽ ትራንስፖርት ድርጅት ባለቤት አቶ ወ/ሚካአል ሃለፎም፣ የታደለ ብርሃኑ አስመጪና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ታደለ ብርሃኑ፣ ስራው ያልተገለፀውና እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋለው አቶ ብርሃኑ ዝናቡ ሹመይ እንዲሁም የ24 አመቱ የ1ኛ ተከሣሽ ወንድም አቶ ካህሣይ ጉላን ዓለሙ ደግሞ በአንድ መዝገብ ተከሰዋል፡፡ 
በአቶ ተመስጌን ጉላን ላይ በተናጠል የቀረበው 1ኛው ክስ፤ ተከሣሹ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በተለያየ ሃላፊነት ላይ ተመድቦ ከ1999 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም ለስድስት ዓመታት ሲሠራ፣ አስቀድሞ በነበረበት የመንግስት ስራ ወይም በሌላ መንገድ ሲያገኘው ከነበረው ህጋዊ ገቢ ጋር የማይመጣጠን፣ በወንድሙ በካህሣይ ጉላን ስም በዳሽን ባንክ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ፤ በራሱ ስም ደግሞ በወጋገን ባንክ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በማስቀመጥ እና በማንቀሳቀሱ በአጠቃላይ በራሱና በወንድሙ ስም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ አስቀምጦ በመገኘቱ ተከሷል፡፡ 
ተከሣሹ በጓደኛው ብርሃኑ ዝናቡ ስም ስድስት ቦቴ መኪናዎችን ከነተሳቢያቸው፣ በአቶ ወ/ሚካኤል እና ታደለ ብርሃኑ አማካኝነት ከባንክ 10.5 ሚሊዮን ብር በመበደር ከራሱ 10.5 ሚሊየን ብር በመጨመር በድምሩ በ21 ሚሊዮን ብር ከሰኢድ ያሲን ኃላ.የተ.የግል ማህበር ገዝቶ መኪኖቹን በ2005 ዓ.ም ለተለያዩ ግለሰቦች በመሸጥ፣ በወንድሙ ስም ከቢዩ ኃ/የተ/የግ/ማህ ሁለት ዶዘሮችን በብር 15 ማሊዮን ብር መግዛቱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በወንድሙ ስም በቦሌ ክ/ከተማ 325 ሜ.ካ ቦታ ላይ የተሠራ መኖሪያ ቤት በማፍራቱ እና በ2.8 ሚሊየን ብር በመሸጡም ተከሷል፡፡ 
ቀሪዎቹ ተከሣሾች ደግሞ፣ አቶ ተመስገን ሙስና ፈፅሞ ያገኘው ገንዘብ እና ንብረት መሆኑን እያወቁ መኪኖቹ የሚገዙበትን ሁኔታ ሃሣብ በማፍለቅና በመርዳት፣ የባንክ ብድር እንዲገኝ በማመቻቸት እና በመበደር እንዲሁም በራሱ አስመጪና የትራንስፖርት ድርጅት ስር መኪኖቹ ተጠቃለው እንዲሠሩ በማድረግ አቶ ወ/ሚካኤል ሃለፎም ተጠያቂ ሲሆን አቶ ታደለ ደግሞ በሙስና ወንጀል የተገኘው ገንዘብና ንብረት እንዳይታወቅ ለማድረግ አቶ ብርሃኑ ዝናቡ እና ካህሣይ ጉባል የቀበሌ መታወቂያ እንዲያወጡ በማመቻቸት እና በቀበሌው መታወቂያ መነሻነት የተጠቀሡትን ወንጀሎች እንዲፈፅሙ በማድረጉ  በወንጀሉ በመሣተፉ መከሠሡ ተመልክቷል፡፡ በቁጥጥር ስር ያልዋለው አቶ ብርሃኑ ዝናቡ፤ መኪኖቹ በስሙ እንዲገዙ፣ የባንክ ብድርም በስሙ እንዲበደር በማድረጉ ክስ የቀረበበት ሲሆን ወጣት ካህሣይ ደግሞ ለወንድሙ ውክልና ሠጥቶ በስሙ ገንዘብ እንዲያስቀምጥና እንዲያንቀሣቅስ እንዲሁም መኖሪያ ቤት እንዲገዛ በማድረጉ ተከሷል፡፡ 
ቀደም ብሎ በነበሩት ሁለት ቀጠሮዎች አቶ ተመስገን፣ አቶ ወ/ሚካኤል እና አቶ ታደሰ፤ ክሡ ተነቦላቸው መቃወሚያቸውን አቅርበው፣ አቃቤ ህግም ለመቃወሚያው መልስ የሠጠ ሲሆን ካህሣይ ጉላል ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ ቀርቦ ክሡ ከተነበበለት በኋላ፣ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ከሌሎች ተከሳሾች ጋር አብሮ እያየው ነው፡፡ 
አቃቤ ህግ በተከሣሾቹ ላይ 14 የሠውና 14 የሠነድ ማስረጃዎችን ከክሡ ጋር አያይዞ አቅርቧል፡፡ 
ከትናንት በስቲያ የዋለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 15ኛው ችሎት፤ በመዝገቡ ላይ የተለያዩ ትዕዛዞችን ያስተላለፈ ሲሆን በእለቱ የቀረበው 5ኛ ተከሣሽ፤ የዋስትና መብቱ ተከልክሎ በቀጣይ ቀጠሮ ከጠበቃ ጋር እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ መዝገቡን ለጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ -

No comments:

Post a Comment