Sunday, December 15, 2013

14 ህፃናት ከመኪና ቃጠሎ ተረፉ


14 ህፃናት ተማሪዎችን አሳፍሮ ከጎተራ ወደ ካቴድራል ትምህርት ቤት ይጓዝ በነበረ ኩምቢ ቮልስ መኪና ላይ ባልታወቀ ምክንያት በተነሳ እሳት ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በህፃናቱ ላይ ምንም አይነት አደጋ አለመድረሱ ታውቋል፡፡ 
ጎተራ ማሳለጫ ላይ ከመኪናው የፊት አካል የተነሳውን እሳት የተመለከተው ሹፌሩ፤ ልጆቹን ፈጥኖ ከመኪናው በማውጣቱ በህይወት ላይ አደጋ አለመድረሱን የጠቆመው ፖሊስ፤ መኪናው በምን ምክንያት ለእሳት ቃጠሎ እንደተዳረገ የቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡
 እሳቱ በምን እንደተነሳ የተጠየቀው ሹፌሩ፤ እሱም ምክንያቱን እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡ ስለ አደጋው ያነጋገርናቸው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ በበኩላቸው፤ መኪናው 8 ሰው ብቻ መጫን ያለበት ቢሆንም 14 ህፃናት አሳፍሮ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
 እሳቱን ለማጥፋት ከ25 ሺህ ሊትር በላይ ፈሳሽ እንደፈጀና መኪናው በቃጠሎው ከጥቅም ውጭ እንደሆነ አቶ ንጋቱ ገልፀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment