Saturday, December 7, 2013

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ህልፈተ ህይወት አስመልክቶ የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ለሶስት ተከታታይ የስራ ቀናት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡


ምክር ቤቱ  ውሳኔውን ያስተላፈው ህዳር 28/2006 ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ነው፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ እንደገለፁት ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድ የተደረገውን ከፍተኛ ትግል የመሩ የነፃነት ታጋይ ከመሆናቸውም ባሻገር መላው አፍሪካ ከጭቆናና ከውጪ ሀይሎች አገዛዝ ነፃ እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ ብለዋል፡፡ 
ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም በህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን በመገንባት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከትውልድ ሀገራቸው ደቡብ አፍሪካ አልፎ በመላው አፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዳስገኘላቸውም ተናግረዋል፡፡  
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ መካከል ያለው የጠበቀ ወዳጅነት ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሶ ኢትዮጵያ ማንዴላ ለታገሉለት የህዝቦች ነፃነትና የዴሞክራሲ ግንባታ ታላቅ አክብሮት እንዳላት ገልጿል፡፡
በስብሰባው ላይ አንድ አንድ የምክር ቤቱ አባላት እንደተናገሩት ታላቁ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ለመላው የአፍሪካ የነፃነት ትግል ላበረከተችው አስተዋጹዎ ልዩ ትርጉም የሰጡ፣ የፓንአፍሪካኒዝም ትግል አቀንቃኝና የነፃነት ተምሳሌት እንደነበሩ አውስተዋል፡፡
ምክር ቤቱም በታላቁ መሪ ህልፈተ ህይወት ምክንያት ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱና በውጪ በሚገኙ መስሪያ ቤቶች የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ለሶስት ተከታታይ የስራ ቀናት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ውሳኔ አስተላልፎል፡፡
ምክር ቤቱ በነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለሀገሪቱ ህዝብ፣ መንግስት እና ለቤተሰቦቻቸው ገልጿል፡፡

ሪፖርተር፦ሰለሞን አብርሃ 

No comments:

Post a Comment