Saturday, December 14, 2013

ኢህአዴግ ከብሔር “ተኮር” ተቃዋሚዎች ጋር ሊሸማገል ነው


eprdf to reconcile
ኢህአዴግ በብሔርና በክልል ደረጃ ከተደራጁ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱት ቅድሚያ በመስጠት ለመደራደር የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ በማመቻቸት ላይ መሆኑን የጎልጉል ምንጮች ገለጹ። ምንጮቹ እንደጠቆሙት ኢህአዴግ ለዚህ ተግባሩ ወዳጅ ጎረቤት አገሮችን፣ አንጋፋ የጎሳ መሪዎችንና ያፈገፈጉ የቀድሞ ተቃዋሚ መሪዎችን እየተጠቀመ ነው።
ህወሃት አሁን በአገሪቱ ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋ የሄደው አለመረጋጋት እንዳሳሰበው የጠቆሙት የኢህአዴግ ሰው ድርጅቱ እርቅ ላይ ከመቼውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ስትራቴጂ መንደፉን አመልክተዋል።
“ከውጥረት ለመውጣት ወይም ውጥረትን ለመቀነስ” በሚል ኢህአዴግ ትኩረት ሰጥቶ የጀመረው አዲሱ የ”ሰላም” መንገድ ህብረ ብሔር ድርጅቶችን ያላከተተበትን ምክንያት አልተብራራም። ይሁን እንጂ ከኢህአዴግ ባህሪ አንጻር አቋሙ ሊቀየር የሚችል መሆኑን አልሸሸጉም።
ለድርድር የተመረጡትን ብሔርና ክልል “ተኮር” ድርጅቶች ይፋ ማድረግ ለጊዜው እንደሚቸግራቸው ምንጮቹ ተናግረዋል። በድፍኑ ግን በተለይ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ክልልና ምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የነጻ አውጪና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶች በማዕቀፉ ውስጥ እንዳሉ አመላክተዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጪ ኢንቨስተሮች ፍሰት መቀነሱ፣ ገብተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ድርጅቶችም ከጸጥታና መሰል ችግሮች አገር ለቀው ወደመውጣቱ ላይ በመሆናቸው፣ አገሪቱ ውስጥ ያለው የስራ አጥነት ችግር እየተወሳሰበ መሄዱና ድህነት በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ መስፋቱ ህወሃቶችን እንዳሳሰባቸው ያስታወቁት የጎልጉል መረጃ ሰጪዎች “የኢህአዴግ አቻ ፓርቲዎችም ለህወሃት ያላቸው የአገልጋይነት መንፈስ እየተመናመነ መሄዱ ዋንኛው የህወሃት ጭንቀት ነው” ብለዋል። በዚህም የተነሳ እርቅ ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ነው።
ህወሃት ባደራጃቸው የብሔርና የጎሳ ድርጅቶች ጥላ ስር ለይስሙላ ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ ከሚባሉ ክልሎችና ዞኖች “እውነተኛ ውክልና አለን” የሚሉ ብሄርን፣ ክልልንና ዞንን መሰረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ለማካሄድ የታሰበው ድርድር ተግባራዊ ከሆነ አተገባበሩ እንዴት ሊሆን እንደሚችልም ምንጮቹ አላብራሩም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ኦህዴድንና ኦነግን ለማስማማት ተካሂዶ በነበረው ንግግር ኦነግን ወደ ኦህዴድ ለማጠቃለልና ለኦነግ ስልጣን ለማጋራት የታቀደው እቅድ መክሸፉን አስታውሰዋል።
መረጃ ሰጪዎቹ አያይዘው እንደተናገሩት በቀዳሚነት በተለይ ከሶስት ክልልና ብሔር “ተኮር” ድርጅቶች ጋር ኢህአዴግ ለማከናወን የሚፈልገው እርቅ በክልሉ ወይም በዞኑ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን መሪዎች እጁን ዘርግቶ እስከመቀበል የሚያደርሰው ነው። ቀጥለው ሲያስረዱም ሙሉ አስተዳደራዊ ስልጣን እስከመስጠት ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።
ህወሃት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ አገሪቱን አሳንሶ አዳክሞና ቆራርጦ የማቀራመት ዓላማ ስላለው ምን አልባትም በደቡብ ክልል አዲስ ክልል ሊወለድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ከምንጮቹ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
Isaias-Afwerki-in-Kenya2
ኢሣያስ ከደቡብ ሱዳን መሪ ሳልቫ ኪር ጋር
በማስታረቁ ስራ ላይ የተሰማሩትን ማንነት መግለጽ ለጊዜው አግባብ አይደለም በማለት ዝምታን የመረጡት የኢህአዴግ ሰዎች እርቅ በመላው አገሪቱ እንደሚያስፈልግ አብዛኛው ካድሬና የበላይ አመራሮች ምኞት መሆኑን ጠቁመዋል። ዋናው ቁልፍ ያለው በህወሃት እጅ በመሆኑ ክልሎችን ቀደም ሲል ያስቀየመ አካሄድ በመሆኑ በአሁኑ እርቅ አካሄድ ላይ የክልል ከፍተኛ ባለስልጣኖችም እንደተሰማሩበት ተመልክቷል። ሰሞኑን ግንቦት 7 የፍትህና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ኢህአዴግ ለሶስት ጊዜ ያህል የእርቅ ጥያቄ እንዳቀረበለት መግለጹና ኢህአዴግም በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በኩል ግንቦት 7ን የመታረቅ እቅድ እንደሌለው በመግለጽ ጉዳዩን ማጣጣሉ ይታወሳል።
ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያና ኤርትራን ለመሸምገል በይፋ ማስታወቋ፣ ኳታርም ቀደም ሲል በተመሳሳይ ለእርቅ ላይ ታች ስትል መቆየቷ የሚታወስ ነው። የሁለቱም አገራት የሽምግልና ሩጫ ምን ውጤት እንዳስመዘገበ የሚታወቅ ኦፊሳላዊ መረጃ ከየትኛውም ወገን አልተደመጠም። ይልቁኑም ህወሃትና ሻዕቢያ አንዱ የሌላውን ባላንጣ በማደራጀት ስራ ላይ መጠመዳቸው ነው በይፋ እየተነገረ ያለው።
Isaias-Afwerki-in-Kenya1
የኬኒያው መሪ ዑሁሩ ኬኒያታና ኢሣያስ
በሌላ በከል ደግሞ ኢጋድንና የኢጋድ አገራት መሪዎችን በይፋ ሲዘልፉ የነበሩት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰሞኑን በሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ተከትሎ አዳዲስ መረጃዎች እየተሰሙ ነው። ከኢጋድ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በይፋ ለማደስ እየሰሩ መሆናቸውም ተነግሯል። ኤርትራ በተባበሩት መንግስታት የተጣለባት እቀባ እንዲነሳላት አጠንክራ እየተከራከረች ባለችበት ወቅት ላይ ሆና ኢጋድን በወጉ ለመወዳጀት ወስናለች መባሉ ወሬውን ሚዛን የሚደፋ እንደሚያደርገው በርካቶች ይስማሙበታል።
ኢህአዴግ በቀጠናው ብሎም በኢጋድ ውስጥ ባለው ተሰሚነት የተነሳ መድረኩ ሻዕቢያንና ወያኔን በማገናኘት ለማሸማገል ለሚደረገው ጉዞ የመጀመሪያው ርምጃ እንደሆነ ከግምት በላይ የሚናገሩም አሉ። ከካርቱሙ ጉብኝት በኋላ በኬኒያ 50ኛ ዓመት የነጻነት በዓል ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጉዳዩ ላይ ከቀጣናው አገራት ጋር እንደሚመክሩበት በመግለጽ ጉብኝታቸውን ከዚሁ ጋር የሚያይዙ አሉ። ይህን አስመልክቶ ግን ከየትኛውም ወገን በገሃድ የተሰጠ መግለጫ ግን የለም።

No comments:

Post a Comment