Monday, December 9, 2013

ወያኔ ቁጥርና ቀጠሮ አያውቅም ,, 30ሺ አይሞሉም የተባሉት ስደተኞች ከ150ሺ በላይ ሆነዋልወያኔ እንደሚለው በየአመቱ ከ2ሚ. በላይ የስራ እድል ቢፈጠር፣ ከውጭ ሰራተኛ እናስመጣ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው ማስታወቂያ፣ በበርካታ አካባቢዎች ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞ የውሃ አገልግሎት እንደሚቋረጥ ገልፆ ነበር፡፡ አዲስ መስመር ለማገናኘው ሦስት ቀን ሙሉ ውሃ ማቋረጥ፣ ግራ ያጋባል፡፡ ሁሉም ነገር ከተዘጋጀኮ፣ አዲሱን መስመር  በጥቂት ሰዓታት አገናኝቶ ሥራውን ማጠናቀቅ አያቅትም፡፡ ደግነቱ ቅዳሜ በቀጠሮው ውሃ አልጠፋም፡፡ እሁድ ግን ተቋረጠ። ሰኞና ማክሰኞም እንደዚያው፤ ረቡዕ  ሀሙስም… ትናንት አርብም አልመጣም፡፡ መንግስት ጋ ቀጠሮ አይሰራም፡፡ “የአገሪቱና የአህጉሪቱ መዲና” በምትባል ከተማ…ውሃ ከጠፋ ስድስት ቀን ተቆጠረ።
የድሃ አገር ነገር እንዲህ ነው፡፡ “የባሰ አታምጣ” የሚያስብል ነገር አይጠፋም፡፡ በሰሜን ጐንደር ለስምንት ወር የቧንቧ ውሃ የተቋረጠበት ከተማ ምን ይበል! የከተማዋ አስተዳደር ሲጠየቅ ምን አለ መሰላችሁ? ውሃ የተቋረጠው፣ በፓምፕ ብልሽት ነው አለ፡፡ በቃ፤ በመንግስት ቤት፣ አሳማኝ ምክንያት አግኝቷል፡፡
ሆን ብሎ ቧንቧውን እየዘጋ ውሃ እንዲቋረጥ ካላደረገ በቀር፤ በፓምፕ ብልሽት ውሃ ቢቋረጥ መንግስት ጥፋት የለበትም ማለት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ “በቅርቡ ይስተካከላል” የሚል የማጽናኛ ቃልና የተስፋ ቀጠሮ መስጠቱን አያቆምም፡፡ ምን ዋጋ አለው? በቀጠሮው ከዛሬ ነገ እየተጠበቀ ስምንት ወር አለፈው፡፡
የመንግስት ቀጠሮ እንዲህ ነው፡፡ በ2002 እልል የተባለለትን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ታስታውሳላችሁ፡፡ በአዲስ አበባ በየአመቱ ሰላሰ ሺ ኮንዶምኒዬም ቤቶች ይገነባሉ ተብሎ ነበር። ብዙም ሳይቆይ፤ እንዲያውም ሃምሳ ሺ ቤቶችን በየአመቱ እገነባለሁ አለ፡፡ ለነገሩ እንግዲህ ፉከራ ከጀመረ ከአስራ ሁለት አመት ሆኖታል፡፡ አያችሁ መንግስት ቁጥር እና ቀጠሮ አያቅም የምለው ወድጄ አይደለም፡፡
እንደ አፉ ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በአዲስ አበባ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ (600 ሺ) ቤቶች ተገንብተው ነዋሪዎች ይረከቡ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ መብራትና ውሃ ሳይገባላቸው ኦና የተቀመጡ በሺ የሚቆጠሩ ቤቶችን ጨምሮ ለነዋሪ የተላለፉ ኮንዶምንዬም ቤቶች፣ 90ሺ ገደማ ብቻ ናቸው – የእቅዱ 15 በመቶ ያህል መሆኑ ነው፡፡ አሁን እንደገና ፣ ከሚሊዮን በላይ ቤቶችን እገነባለሁ ብሎ ከነዋሪዎች ቀብድ መሰብሰቡን ደግሞ ካሰቡት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
መንግስት ቀጠሮና ቁጥር እንደማያውቅ ዛሬም ደጋግሞ እያስመሰከረ ይመስለኛል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት፣ ህገወጥ ስደተኞችን አባርራለሁ ብሎ የአደን ዘመቻ ያወጀ ሰሞን ታስታውሳላችሁ። በሳዑዲ፣ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ወደ 20ሺ ገደማ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ነበር የኢትዮጵያ መንግስት የገለፀው። ግን እንደተገመተው አልሆነም፡፡ የሚባረሩት ስደተኞች 40ሺ ሲሆኑ ይችላሉ በማለት ግምቱን ያሻሻለው መንግስት፣ በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ አገር ይመለሳሉ በማለት ነበር ቃል የገባው፡፡ በዚህ አላበቃም፡፡ ትንሽ ቆይቶ የተመላሾቹ ቁጥር 80ሺ ሊደርስ እንደሚችል ግምቱን እንደገና አሻሽሎ ነግሮናል፡፡
አሁንም የመንግስት ግምት አልሰራም፡፡ ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩና ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ስደተኞች ቁጥር 120ሺ  ደርሷል፡፡ አሁንም እየጨመረ ነው፡፡ ለመሆኑ መንግስት “20ሺ… 40ሺ” የሚል ግምት ላይ የደረሰው ከምን ተነስቶ ይሆን?
እንግዲህ አስቡት፡፡ ለሃይማኖታዊ ስርዓት በየአመቱ በአስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሳውዲ ይጓዛሉ፡፡ ብዙዎቹ ግን አይመለሱም፡፡ በህጋዊ ምዝገባ በየአመቱ ከሚጓዙ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች መካከልም፣ ኮንትራታቸውን ከጨረሱ በኋላ የማይመለሱ አሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በየመን በኩል ወደ ሳውዲ ለመግባት በየአመቱ ከ50ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚሰደዱ የዩኤን የምዝገባ ሰነድ ያሳያል፡፡ ካቻምና 75ሺ ኢትዮጵያውያን የመን ገብተዋል፡፡ አምና 85 ሺ ገደማ፣ከዚያም 50ሺ ያህል…
እነዚህን ሁሉ መረጃዎች የሚያውቅ መንግስት፤ “20ሺ ወይም 40ሺ” የሚል ግምት እንዴት ይመጣለታል? በማለት ችግር የለውም፤ መንግስት ቁጥር አያውቅማ! እንደ እንቆቅልሽ እኛ ያላወቅነው አዲስ የአቆጣጠር ስልት ተፈጥሯል ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው፡፡
ካላመናችሁ፣ እዚያው ከዚያው ሌላ “የቁጥር እንቆቅልሽ” ልጨምርላችሁ፡፡
ከሳዑዲ የተባረቡ ስደተኞችን የጐበኙ የፓርላማ አባላት፤ “አይዟችሁ፤ ወደ አገራችሁ ነው የተመለሳችሁት፡፡ ድሮም የባዕድ አገር የባዕድ ነው” በሚል ስሜት ሊያጽናኑ ሞክረዋል፡፡
በእርግጥም ሁሉም አገር እንደ አሜሪካ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል የስራና የብልጽግና እድልን፣ በሌላ በኩል የነፃነትና የህግ አከባበርን አጣምሮ የያዘ አገር እንደልብ አይገኝም፡፡ በተለይ ሳዑዲ በፍፁም እንደ አሜሪካ አይነት አገር አይደለችም፡፡ በጭራሽ፣ ነፃነትንና ህግን በማክበር አትታማም፡፡ እንዲያውም የነፃነት ሽታ ካልደረሰባቸውና በአፈና ከታመቁ ዋና ዋና አገራት አንዷ ሳዑዲ ናት፡፡
ለነገሩ ኢትዮጵያም  በአኩሪ የፖለቲካ ነፃነትና  በአስተማማኝ የህግ የበላይነት የምትታወቅ አገር አይደለችም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ድሃ አገር ናት። ፈጣን እድገት እየተመዘገበ መሆኑ እየካድኩ አይደለም፡፡ ግን አሁንም ከአስሩ የአለም እጅግ ጎስቋላ ድሀ አገራት ተርታ አልወጣችም፡፡ “ድሃ” ማለት ደግሞ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ የስራ እና የብልጽግና እድል የጠበበት አገር ማለት ነው፡፡ የስደት ተመላሾችን የጐበኙ የፓርላማ አባላት ግን፣ ይህንን የአገር እውነት የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ ምናልባት፣ ብዙዎቹ የፓርላማ አባላት፣ መልካም እንደሚመኝ ማንኛውም የዋህ ሰው፣ህልመኛ የመሆን እና በህልም ዓለም ውስጥ ለመኖር የመሞከር ልዩነት ጠፍቶባቸው ወይም ተምታቶባቸው ይሆናል፡፡ ወደፊት የምትፈጠረውን የበለፀገች አገር በምናብ እያዩ፣ የዛሬዋን ድሃ አገር በእውን ማየት ተስኗቸዋል ማለት ነው፡፡
የፓርላማ አባላቱ ግን በዚህ አይስማሙም። እንዲያውም ከንግግራቸው እንደተታዘብኩት፣ ከነሱ በላይ የአገሪቱን ትልቅ አቅም በእውን ማየት የሚችል ሰው ይኖራል ብለው አያስቡም፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ለስደት የሚጐርፉት፣ የአገሪቱን አቅም ማየት ስለተሳናቸው ነው ብለዋል የፓርላማ አፈጉባኤ፡፡ አዲስ አባባል አይደለም፤ ከጠ/ሚኒስትሩ እና ከሌሎች ሚኒስትሮች የምንሰማው የዘወትር አባባልም ተመሳሳይ ነው፡፡ የመንግስት አቋም ነዋ፡፡
በእርግጥ አፈጉባኤው፣ ከስደት ተመላሾችን ለማቋቋም መንግስት ልዩ ድጋፍ እንደማይሰጥ ወይም ልዩ እቅድ እንደማያወጣ መግለፃቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እንደብዙዎቹ ባለስልጣናት “አትጨነቁ፤ የስራ እድል በሽበሽ ነው” የሚለውን የመንግስት ስብከት መድገማቸው የትም አያደርስም። ኢትዮጵያ ውስጥ የስራ እና የብልጽግና እድል ሞልቶ እየተትረፈረፈ እንደሆነ ለማሳመን የመንግስት ባለስልጣናት ነጋ ጠባ አፍ የሚያስከፍቱ ግዙፍ ቁጥሮችን መዘርገፋቸው ምንም ለውጥ አላመጣም፡፡
ወጣቶች ለስደት የሚጐርፉት የአገሪቱን አቅም ማየት ስለተሳናቸው ነው የሚለው መንግስት፤ በየአመቱ ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን  የስራ እድል እየተፈጠረ ነው ይላል፡፡ አፈጉባኤ አባዱላ ብቻ አይደሉም ይህንን የተናገሩት፡፡ የከተማና ኮንስትራክሽን ልማት ሚኒስትር፣ እያሰለሱ በቴሌቪዥን ብቅ ባሉ ቁጥር፤ በከተሞች ብቻ በየአመት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ሳይናገሩ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ በአገራችን ከተሞች ባለፉት ሶስት አመታት 3.5 ሚሊዮን የስራ እድል መፈጠሩን ሚኒስትሩ ገልፀው፣ ዘንድሮና በሚቀጥለው አመት አራት ሚሊዮን ተጨማሪ የስራ እድል ይፈጠራል ብለዋል፡፡ እውነትም መንግስት ቁጥር አያውቅም ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ለምን በሉ፡፡
በ1998 ዓ.ም ዋዜማ በተካሄደ ጥናት፣ በኢትዮጵያ ከተሞች በሙሉ፤ ለስራ የመሰማራት አቅም ያላቸው ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ 4.4 ሚሊዮን ገደማ እንደነበር የስታስቲክስ ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በወቅቱ 3.5 ሚ ያህሉ በስራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ የስራ አጦች ቁጥር 900ሺ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡
በ2002 ዓ.ም ዋዜማ በተደረገ ሌላ ጥናት ደግሞ፣ የመስራት አቅም ያላቸው ከተሜዎች 5.7 ሚ እንደሆኑና 4.5 ሚ ያህሉ ስራ ላይ እንደተሰማሩ ይገልፃል፡፡ ስራ አጦቹ  1.2 ሚ ነበሩ፡፡
ከሶስት አመት በኋላ የስታክቲክስ ባለስልጣን ያካሄደው የቅርብ ጊዜ ጥናት ደግሞ አለ፡፡ ስራ ላይ የመሰማራት አቅም ያላቸው ከተሜ ሰዎች ቁጥር  6.9 ሚ ደርሷል፡፡ የስታክስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርት እንደሚገልፀው ከሆነ፣ 5.7 ሚሊዮን ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ 1.2 ሚ. ያህል ሰዎች ስራ አጥ ናቸው፡፡
እንግዲህ አስቡት፡፡ ከመረጃዎቹ መረዳት እንደሚቻለው፣ በየአመቱ ወደ 400ሺ ገደማ የመስራት አቅም ያላቸው ከተሜዎች ይፈጥራሉ፡፡ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በስምንት ዓመታት 3.5 ሚ የስራ ዕድል ቢፈጠር፤ ዛሬ በየከተማው የመስራት አቅም ያለው ሰው በሙሉ ስራ ይዞ እናገኘው ነበር ማለት ነው፡፡
መንግስት ግን ባለፉት ስምንት አመታት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የስራ እድሎች እንደተፈጠሩ ይገልፃል፡፡ እንዲያውም በሦስት አመት ብቻ፣ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የስራ እድል እንደተፈጠሩ የከተማና ኮንስትራክሽን ልማት ሚኒስቴር እልፍ ጊዜ ነግሮናል፡፡ ጭራሽ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ተጨማሪ 4 ሚሊዮን የስራ እድሎችን እፈጥራለሁ ብሏል፡፡ በአጠቃላይ ከ1998 ወዲህ በአስር አመታት ውስጥ  ከ9.5 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የስራ እድሎች ከተፈጠሩ ኮ… ከዚያ በፊት ከነበረው የስራ እድል ጋር ሲደማመር በ2007 ወደ 13 ሚሊዮን ገደማ ከተሜዎች ስራ ላይ ይሰማራሉ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በ2007 ዓ.ም  የመስራት አቅም ያላቸው ከተሜዎች ቁጥር ቢባዛ ከ8 ሚሊዮን የሚበልጥ አይሆንም፡፡
እንግዲህ ከሌሎች አገሮች ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰራተኞችን አምጥተን ካልቀጠርን በቀር፣ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ በቂ የሰው ቁጥር አናገኝም፡፡ እውነትም መንግስት ቁጥር አያውቅም፡፡

No comments:

Post a Comment