Wednesday, January 1, 2014

አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ በአንድነት አመራር አልተካተቱም

seye-abraha-Meles

ታህሳስ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተካሄደው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ጠቅላላ ጉባኤ
በተካሄደበት ወቅት በአካል ያልተገኙት አቶ ስዬ አብርሃ እና አቶ ተመስገን ዘውዴ ጨምሮ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
ከፓርቲው አመራር ውጪ ሆኑ። በፓርቲው ምስረታ ወቅት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ
በቅርቡ ወደ ፓርቲው የተቀላቀሉት አቶ ስዬ አብርሃ እና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንዲሁም በ1997ቱ ምርጫ በፓርላማ
ተሳትፎአቸው ታዋቂ ተሟጋች የነበሩት አቶ ተመስገን ዘውዴ ከፓርቲው አመራር ውጪ ሆነዋል።
ከወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እስካሁን ግልፅ ባላደረጉት ምክንያት የፓርቲውን ሊቀመንበርነታቸውን በመተው
አሜሪካን ሀገር ለትምህርት ያቀኑ ሲሆን አቶ አንዱአለም አራጌ ደግሞ በሽብርተኝነት ክስ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ
ተብለው የዕድሜ ልክ ፍርደኛ ሆነዋል። አቶ ስዬ አብርሃ ለአንድ ዓመት ትምህርት ለመከታተል ወደ አሜሪካ
አቅንተው በዚያው የቀሩ ሲሆን በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት አቶ ተመስገን ዘውዴ በአሜሪካን አገር ይገኛሉ።
ፓርቲውን ለአለፉት ሁለት ዓመታት በሊቀመንበርተን ሲመሩ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በግል ውሳኔያቸው ፈቃድ
ከማንኛውም የፓርቲው የአመራር እርከን ራሳቸውን አግልለዋል።
በውጪ ሀገር ለትምህርት የሄዱት አቶ ስዬ አብርሃ በአሁኑ የፓርቲው ጉባኤ ላይ የብሔራዊ ም/ቤት አባል ለመሆን
ማመልከቻ አላስገቡም። በተመሳሳይ አቶ ተመስገን ዘውዴ በፓርቲው ሁለተኛ የስልጣን አካል በሆነው ብሔራዊ
ም/ቤት አባል ለመሆን አላመለከቱም።
የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴ አቶ ስዩም መንገሻ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ፓርቲው ነባር አመራሮቹን
ከአመራርነት አለማግለሉንና አብዛኛዎቹም በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት በም/ቤቱ ለመሳተፍ ፍላጎት
አለማሳየታቸውን ነው የገለፁት። አመራሮቹ በፓርቲው የአመራር እርከን መሳተፍ ቢፈልጉ የብሔራዊ ም/ቤት እጩ
ለመሆን ያመለክቱ ነበር ብለዋል።
በአቶ ስዩም ገለፃ ነባሮቹ አመራሮች በፓርቲው ውስጥ በአመራርነት ባይሳተፉም ከአንድነት አይለዩም፣ በአባልነት
ይቀጥላሉ ብለዋል። ፓርቲው አቅሙን በወጣቶች ለማጠናከር በስራ አስፈፃሚ ውስጥ 65 ከመቶ የሚሆኑ
አመራሮች ወጣቶች እንደሚሆኑ ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ጉባኤ ላይ የወጣቶች ቋሚ ኮሚቴ በማቋቋም ፓርቲውን
የሚመሩትን ቋሚ ኮሚቴዎች ወደ 12 ከፍ እንዲል ማድረጉ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በብሔራዊ ም/ቤቱ
የሚሳተፉ 65 ቋሚና ተለዋጭ አባላት መካከልም ዕድሜያቸው ከ35 እና ከዚያ በታች የሆኑ ወጣቶች በጎላ መልኩ
መካተታቸው ታውቋል።
ፓርቲው 204ሺህ ብር በማውጣት ያካሄደው 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሞላ ጎደል ስኬታማ እንደነበር የጠቀሱት
አቶ ስዩም የጉባኤው አባላት ከመላሀገሪቱ የራሳቸውን የመጓጓዣ ወጪ በመሸፈን ፓርቲውን ከከፍተኛ ወጪ
በመታደጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከተመሰረተ አምስት ዓመታት ያስቆጠረው አንድነት ፓርቲ የአባልነት ግዴታቸውን የሚወጡ 23ሺህ አባላትና
በመላ ሀገሪቱ 29 ጽ/ቤቶች ያሉት ፓርቲ መሆኑ ከዶ/ር ነጋሶ የጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment