Saturday, January 4, 2014

አልጋ ወራሹ ማነው?

Zehabesha AmharicUDJ - Ethiopia

የአንድ ወጣት እድሜ አስቆጥሯል፤ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ህወሃት/ኢህአዴግ መግዛት ከጀመረ። በብሄርና በሃይማኖት እኩልነት ስም ህብረተሰቡን በመከፋፈል ለሃያ ሶስት አመታት ስልጣኑ ላይ ከመቆየቱም በላይ፤ ጥቂቶቹ የቡድኑ አባላትና ደጋፊቆቻቸው በጉቦ በዘረፋና ለም መሬት በመሽጠት ጭምር ሲከብሩ፤ ብዙሃኑ ሕዝብ ግን ኑሮው ከእለት እለት እያሽቆለቆለበት ሲሄድ፤ አገዛዙ ግን በአሥራ ምናምን ከመቶ አድገሃል እያለ ሕዝቡን ሊያታልለው ይሞክራልል።
በአሳ መበላት፤ በዘራፉዎች መደብደብና መዘረፍ ከዚያም አልፎ ተገድሎ የሆድ እቃው መቸብቸብ እንዳለ እያወቀ ባለሁበት ሁኜ ከሚሞት እድሌን ልሞክር በማለት ክፍት በሆነለት መንገድ ከአጋሪቷ የሚሸሸው ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው ። ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ ተርፈው ወደ “ተፈለገበት አገር” የሚደርሱ ወገኖቻችን እዚያም ከደረሱ በኋላ የሚደርስባቸው ስቃይና እንግልት ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ለዚህም በአለም ደቻሳ በሊባኖስ፤ በሸዋዬ ሞላ በሊቢያ፤ እንዲሁም ካሜራና የድምጽ መቅረጫ ያላገኛቸው በሺዎች በሚቆጠሩ፡ ወገኖቻችን የደረሰባቸውና ዛሬም በሳውዲና እንዲሁም በደቡብሱዳ እየደረስባቸው ያለው መከራና ስቃይ በቂ ምስክርነው። በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ እንዲሉ ሊወክላቸው የሚገባው መንግስት ህገወጥ ስደተኖች ናቸው ብሎ ተሳልቆባቸዋል።
ከላይ እንደገለጽኩት የገዢው ቡድን ህብረተሰቡን በመከፋፈልና ያለውን ሃይል በመጠቀም ጭምር እስካሁን ስልጣን ላይ ለመቆየት በቅቶአል፡:
የዛሬው ሁኔታ ባለ መልኩ ለዘላልም ስለማይቆይ ሁሉም ነገር ያልፋልና እነሱ ሲያልፉ (በጡረታም ሆነ በደከመን ወይም በዘረፋው በቃን ሲገለሉ) ልጆቻቸውን ለመተካት ሽርጉዱ ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። መተካካት ይሉታል በነሱ ቋንቋ ።
የመተካካቱ ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያ እርምጃ ተተኪዎችን በአምሳያቸው ማሰልጠን ስለሆነ ለዝህም ለጆቻቸውን በውጭ ሃገር በጥሩ ትምህርት ቤቶች (በአብዛኛው ለዚሁ ጉዳይ) አስተምረዋል እያስተማሩም ነው:: በአንድ ውቅት ይህንኑ የታዘበው ጋዜጠኛ ተመስግን ደሳልኝ እንድህ ብሎ ጽፎ ነበር፡
“በእርግጥ እናንተ ሲደክማችሁ ብላቴና ልጆቻችሁን ለመተካት አስባችሁ ከሆነ የክፍለ ዘመኑ አስቂኝ ቀልድ ነው። ያውም እንዲህ የሚል..ብሶት ከወለዳቸው ወደ ደም የወለዳቸው የሚደረግ መተካካት…በሰም እና አጥንት ቆጠራ ለስልጣን መብቃት ወይም በአባት እግር ልጅን መተካት። ይህ ከሆነ መቼም በነካ እጃችሁ የመሬት ፖሊሲያችሁንም ወደ … ርስተ ጉልት … ሲስተም መቀየር የሚኖርባችሁ የመስለኛል።”
ገዢው ቡድን እንኳንስ ለሚያስቅ ለሚያስለቅስ ያውም የደም እምባ ተግባር ግድ የለለው መሆኑን ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ሲያሳየን የሰነበተ በመሆኑ ከተሳካለት ለሳቃችን ብዙም ደንታ የለውም። የመሬት ስሪቱንም በተመለከተ ዛሬም የመሪት ባለቤት ማን ሆኖ ነው።የገዢው ቡድን ነው ገንዘብ ሲያጥረው በእንቨስትመንት ስም መሬቶችን እየቸበቸበ ያለው።ያውም ነዋሪዎችን ከቄዬያቸው በማፈናቅል።
ሃገርን የሚያህል ነገር ለማስተዳደር አነሰም በዛ በተመሳሳይ ሁኔታ በተግባር መፈተንን የግድ ይላል። ይህንን ስል መልካም አስተዳድርን ማለቴ ሳይሆን በስልጣን ላይ እንዳለው ቡድን ለራስ በሚያመች ሁኔታ መግዛትና ህዝቡን መቆጣጠር መቻል ማለቴ ነው። የህወሃት አባላት ይህንን በረሃ በነበሩበት ወቅት ተለማምድው ነው ቤተ-መንግስቱን የተቆጣጠሩት። ስለዚህም ለተተኪዎቻቸው የሙከራ ሜዳ ማስፈለጉ አልቀረም:: አገር ውስጥ መዋቅሩን እነሱ ስለዘረጉት ተተኪዎቻቸውን (ወራሾቹን) ለማሰልጠን ላያስችግር ይችላል። በዝህ የስለላ መዋቅራቸው (አንድ ለአምስት) ህዝቡን ለግዜውም ቢሆን ጠፍሮ ስለያዙት ስጋታቸው ሌላ ቦታ ነው። ለገዢው ቡድን የራስ ምታት የሆነውና ለወደፊትም ለወራሾቻቸው (ለማውረስ ከበቁ) ጭምር መሆኑ የሚቀጥለው የዳያስፖራው ክፍል ስለሆነ፤ ይህንን ክፍል ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ቀጥሎ፤ ዛሬ ወራሾቻቸው ከሆኑ ዳያስፖራውን መቆጣጠር ከቻሉ የተሳካ ውርስ ሊሆንላቸው ስለሚችል ይህንኑ የተያያዙ ይመስላል። ለዚህም ያለፈው ሰሞን የሳውዲ ተቃውሞ ሰልፍ ሁኔታና የነሱ ቀደም ቀደም ማለት በቂ ምስክር ነው።
ተመስገን ጽሁፉን በመቀጠል

“ከአባት አመራርም ወደ ልጆች አመራር ልታሸጋግሩን መዘጋጀታችሁም ምን አልባት የምትመሩትን ህዝብ አለማወቅ እንዳይመስልባችሁ ብትጠነቀቁ መልካም ነው። ምን አልባት የምትነጥፍው ጥገት ታልባ የተገኘውን ማውረስ እንጂ ሃገርና ህዝብን ለማውረስ መሞከር የመጨረሻ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል ።” ብሎ ነበር
እነርሱ ለምክር የሚሆን ጆሮ ያላቸው አይመስልም። ስልጣናቸውን ተጠቅመው ሀብት አፍርተዋል። የቀራቸው ለስም መጠሪያ የሚያገለግል ዶክቶሬት መሸመት ስለሆነ ይህንኑን ከሰሞኑን የአለም ረከርድ ባሻሻለ ሁኔታ ተያይዘውታል። ስልጣኑን ለልጆቻቸው ካወረሱ በኋላ በጡረተኛ ኑሯቸው ዶክተር እገለ ተባብለው ኑሯቸውን ለመግፋት።
ዳያስፖራው
የተቃዋሚው/የአማራጩ ክፍል ግን ገዚው ቡድን ካጠመደለት የክፍፍል ወጥመድ ብዙም ያመለጠ ሳይመስል 23 አመት አስቆጠረ::
የሃገር ቤቱን የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴን በተመለከተ በዘርም ሆነ በብሄራዊ ደረጃ የተደራጁ ፓርቲዎች እንደ አሸን የፈሉበ ወቅት ከመሆኑ ባሻገር ሀዝቡን በማሳተፍም ሆነ ጫና በመፍጠር ገዢውን ቡድን በህዝባዊ ምርጫ ለመለወጥ አለመቻላቸው እንዳለ ሆኖ ብዙዎቹ በሰላማዊም ሆነ በሌላ አማራጭ ለሥርዓት ለውጥ ትግላቸውን ቀጥለዋል:: ለትግሉ እስካሁን ውጤታማ አለመሆን ምክንያታዊ ሃተታውን ግን ሃገር ቤት ላሉት ገምጋሚዎች ብተው መልካም ነው።
የዳያስፖራው ተሳትፎ ግን ልዩ መልክና ሚና አለው:: በተለያዩ ምክንያቶች ከነበረበት አገር ለቆ ወደ ሌላ አገር ለተወሰነም ሆነ ላልተወሰነ ጊዜ እየኖረ ያለ ሰው/ማኅበረሰብ ቀድሞ ለነበረበት አገር ሰዎች ‹ዳያስፖራ› ይባላል (dispersed; Diaspora /የፈለሰ፤ ፈላሻ ፡፡ ባጭሩ ይህ የዳያስፖራ ትርጉም ሲሆን ይህ የህብረተሰብ ክፍል ለትውልድ አገሩ (Home land) በፖለቲካው በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ኑሮ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
አፋኝ የሆኑ አምባገነናዊ መንግስታት ባሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሃገሮች ሚዲያ በገዢዎች ቁጥጥር ስር ሆኖ ለነሱ ፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት ብቻ በሚያገልግልበት ዳያስፖራው የራሱን ዘዴ በመጠቀም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ አቅም አለው። በተለይም በአሁን የመረጃ ቴክኖሎጂ ክፍለ-ዘመን፤ ማህበራዊ የመረጃ ልውውጦሽ በተስፋፋበት ስራውን ያቃልለታል። ሀገር ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ በገንዘብ በመደጎም አንጻርም የተሻለ አቅም ያለው ማህበረሰብ ነው።በ እንግድነትም ሆነ በቋሚነት በሚኖርበት ሁለተኛ አገሩ ባሉት መግስታት አማካይነት በትውልድ አገሩ አገዛዝ ላይ ጫና በማስፈጠርም ሚና ይጫወታል። ለዝህም ሃገራችንን በተመለከተ ምርጫ 97ትን አስከትሎ ገዚው ቡድን በህዝብ ስም የሚሰበስበውን እርዳታ በተመለከተና የ2006 የኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ተጠያቂነት ድንጋጌ ህገ-ረቂቅ (H.R.5680 (Bill) known as The Ethiopia Freedom, Democracy and Human Rights Advancement Act of 2006) በምሳሌነት የሚጠቀስነው። ለቅንጅትም ስኬታማነት ዳያስፖራው ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በተሟላ የ97 አይነቱ መንፈስ ጥንካሬ ባይሆንም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለትግሉ ወደፊት መራምድ ተጽ እኖ ማሳደሩን እንደቀጠለ ነው። በጥቅሉ ዳያስፖራው ለትውልድ ሃገሩ (Home land ) ለሚደረገው ለውጥ የሚጫወተው ሚና የጎላ ቢሆንም፤ ወሳኝነት የለውም፡፡ ወሳኙ ህዝቡ ነው፤ ችግሩንና ብሶቱን እየኖረ ያለው እሱ ነውና።
በአንጻሩም ሁሉም የዳያስፖራው ማህበረ ሰብ አባል ለትውልድ አገሩ እኩል ይቆረቆራል ወይም ይሳተፋል ማለት አይደልም።ሁሉም ከህወሃት/ኢህአዴግ ከከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ የጸዳ ነው ማለትም አይደለም። እንዲያም ከሀገር ውስጥ ይልቅ መከፋፈል በጉልህ የሚታይበትና የሚተገበርበት በዳያስፖራው ሳይሆን አይቀርም። በዘር በሃይማኖት እንዳለ ሆኖ አልፎ አልፎ በተመሣሣይ እምነትና ዘር መንደርን ጨምሮ ክፍፍል ይንጸባረቃል። የክፍፍል ወረርሺኝ ባህር ተሻግሮ እዚህ ካለንበት ሲያተራምሰን ማየቱ እጅግ ያሳዝናል:: ይህም በበኩሉ ከመተማመን መጠራጠርን፡ ከመከባበር መናናቅን፡ ከጋራነት ግለኝነትን ካንድነት መከፋፈልን አስፍኗል። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ይህንን የሚያራምዱ ጥቂት የማይባሉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በበኩሉ ትግሉን ያከብደዋል ያራዝመዋልም።
በርግጥ በግል አነሳሽነት ብዙ መስራት ቢቻልም ለአስትማማኝና ዘላቂ ውጤት ግን በጋራ መስራት አማራጭ የለውም። ለዚህም ነው የድርጅትና የመሪዎች አስፈላጊነትና ወሳኝነት። ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት አብሮ መስራት በማይቻልበት ወቅት ሰዎች የራሳቸውን ድርጅት ለመመስረት ይወስናሉ::
በርግጥ ይህ ለትግሉ ቀጣይነት አማራጭ ከመፈልግ የመነጨ ቢሆንም የድርጅት ጋጋታ ለብቻው መፍትሄ ልሆን አይችልም። ትግላችን የሚለካው ሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ ባሉት የድርጅቶች ብዛት ቢሆን ኖሮ ለህዝባችን ያሰብነውን መልካም አስተዳደር እውን ባደረግን ነበር።
የድርጅት መብዛት ውድድሩን ያሰፋና የተወሰኑት ጠንክረው አሸናፊ ሆነው የወጣሉ ብለው የሚከራከሩ አልጠፉም። በሃገራችን የተፈጠሩት ድርጅቶች ግልጽ በሆነ የፖለቲካ ስርአት ላይ ሳይሆን ብሄርን መስረት ያደረጉ በመሆኑ ለፉክክር የማያመቹ ናቸው ያ ከሌለ ፉክክር ደግሞ አንዱ አሸናፊ ሆኖ መውጣቱ አይኖርም ማለት ነው። ስለዝህም መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው በሚያመቸው መልኩ የድርጅቶች አብሮ መስራት የግድ ይላል። የሰው ሃይልና ሃብት/ገንዘብ አንድ ላይ በማምጣት ያሉት ድርጅቶች እንዲጎለብቱና ትግሉን በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ይረዳል።
ብዙዎች የዲያስፖራው ማህበርሰብ አባላት፤ አቶ ሃይለማርያም የገዚው ቡድን መሪ ሆኖ ሲተኩ ከቅን አመለካከት የተነሳ፤ መሰረታዊ ባይሆንም ለውጥ ይኖራል፡ በይቅር መባባል ህዝባችንን ወደ ተሻለ አቅጣጫ መምራት ይቻላልና ጊዜ እንስጣቸው ብለው ነበር ። ያ ሳይሆን ቀረ። አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ ምንም እንኳን የተለወጠ ነገር ባይኖርም የማንዴላን ህልፈት በማስታከክ ለእውነትና ለእርቅ (truth and reconciliation) በድጋሜ ጥሪ እየቀረበ ነው።
የበደልንን ይቅር ብሎ አብሮ ለመስራት መፍትሄ መፈለግ ለሁሉም ይበጃል። ተበዳዩ ህዝብ ነውና እሱኑ ይቅርታ ጠይቆ እሱኑ ለማገልገል አብሮ መስራት ብልህነት ነው። የቂም ፖለቲካ የትም አያደርስምና። ችግሩ ግን እርቅ የሁሉንም በጎገ ፍቃደኝነት ይጠይቃል። በምኞት ብቻ የሚሆን አይደለም። ከምኞትም አልፎ አስገዳጅ ሆኔታዎች መፈጠር የግድ ይላል። የደቡብ አፍሪካን ስንመለከትም የአለም አቀፍ መንግስታት ጫና፣ መገለልና አለም አቀፍ ፖለቲካ አሰላለፍ በመለወጡ ጭምር እንጂ ዘረኛው የነጮች መግስት ከምንም ተነስቶ አይደለም ማንዴላንና ፓርቲያቸውን የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስን ነጻ ያደረጋቸው።
ህወሃት/ኢህአዴግ ከጥንስሡ ጀምሮ እያካሄደ ያለው የቂም ፖለቲካ ነው። ብዙ አመታት ወደኋላ ሄዶ እንድህ ነበርን/ነበራችሁ፡ ተደረግን/ተደረጋችሁ እያለ ለስልጣን መቆያ ከመጠቀም ባሻገር እየተጓዘበት ያለው መንገድ የትም እንደማያድርስ አውቆ፤ አንዴም ቆምብሎ አስቦ አብሮ የመድራትን ፍንጭ ያሳየበት ወቅት የለም።
የተቃዋሚው ክፍል ጫና ማሳደር ካልቻለ እርቅ ምኞት ሆኖ የቀራል። በርግጥ ገዢዎቻችን ቢያውቁበት ኖሮ፤ ፕ/ት ኦባማ እንዳሉት በፍቃደኝነት ህዝቡን ነጻ ቢያወጡ፤ እነሱ ጭምር ነበር ነጻ የሚወጡት:: ጊዜያቸው ሲደርስ መውደቃቸው ላይቀር። ያኔ ግን ለይቅርታ ጊዜው የመሸ ይሆናል።
ከዳያስፖራውም ክፍል ለሆዱ ያደረና ከህዝቡ ይልቅ ህገር ቤት የቀለሰ ጎጆ የሚያሳስበው፤ ቤተሰቡን ሰብስቦ ለቀሪው ዘመዱ ላልሆነው የማይጨነቅ “ገለልተኛ ነኝ” ባይ፤ እኔ ፖለቲካ አልወድም ከሚለው አልፎ ፤የመቶ አመት ታሪክ እየጠቀሰ ተበድለን ነበር ፤ በተቃራኒው “ለዘመናት የነበረህን ቦታ ዛሬ ተቀማህ” እያለ ጢቂቶችን የሚያስጨበጭብ…. .ወዘተ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የገዢውን ቡድን እድሜ የሚያራዝም በተቃዋሚው ጎራ ነኝ ባይ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። የገዚው ቡድን አንደኛውን “ጠባብ” ሌላኛውን ደግሞ “ነውጠኛው ዳያስፖራ” ብሎ የጠራቸዋል። ለትግብርቱ ግን ቀዳሚው እርሱ ነው። ሁለቱም ቃላት ብዙውን ግዜ ያለቦታቸው ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ባይመቹኝም ከላይ የተጠቀሱትን በተመለከተ ግን ሃቁን ያንጸባርቃሉ።
ጥሩም ሆነ መጥፎው፤ ክፉም ሆነ ደግ ያለፉት የኢትዮጵያ ታሪኮች ወደድንም ጠላን የጋራ ታሪኮቻችን ናቸው። ያለፈወን ታሪካችንን መዝግበን የምናቆየውና የምናስታውሰው መጥፎውን ላለመድገምና ጥሩውን ደግሞ ያለንበት ዘመን የሚፈቅድ ከሆነ ለማስቀጠል አሊያም በጥሩነቱ ለማስታወስ እንጂ ለቂም በቀል መጠቀሚያነት ለማዋል አይደለም። እዚህ ላይ በማንኛውም ህብረተብ በአብዛኛው ያለፉት ታሪካዊ ስህተቶች በስህተትነታቸው የሚታወቁት ከብዙ ጊዜ በኋላ እንጂ በወቅቱ ተጫባጭ ሆኔታ እንደ ስህተት ተደርገው አይቆጠሩም። ከነዚህ ስህተቱች ያመለጠና ፍጹም የሆነ የአለም ታሪክም የለም።
ህዝባችን የሚፈልገው የዛሬው ጎስቋላ ኑሮው የሚሻሻልበት፤ ነጻ አየር ተንፍሶ በመኖር የተሻላች ሃገር ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፍበትን ሁኔታ የሚያመቻችለትን እንጂ ብዙ አመታት ወደኋላ ሄዶ በታሪክ ያሳለፈውን ኑሮ እንዲኖር ወይም ከዛሬው መከራና ስቃይ በተጭማሪ ያሳለፈው ችግር እያስታወሱት ለጊዚያዊ የፖሊቲካ አላማቸው መጠቀሚያ የሚያደርጉትን የአዞ እንባ የሚያነቡለትን አይደለም።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ተደራጅቶ እንደታወቁት የአይሁዶች የኩባና የአይርላንድ ዳያስፖራ ድርጅቶች ደረጃ ለመድረስ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፤ ያላቸውን ሃይልና ገንዘብ አንድ ላይ በማምጣት ልዩነትን አቻችሎ፤ ከመጠላልፍ መደጋገፍን፤ ከግትርነት ሰጥቶ መቀበልን በማስቀደም፡ ሁሉንም እኔ አውቃለህና ተከተለኝ እኔ ብቻ ልናገርና አንተ አድምጠኝ፡ ፍጹም ነኝና እኔን ለማረም አትሞክር የመሳሰሉትም ግብዝነትን ትተን፤ በተቃራኒውም የሚሰራ ሰው እንደሚሳሳት በመዘንጋት አሊያም ሆን ተብሎ ትግሉን ለማደናቀፍ የምንሰነዘረውን ቅጥ ያጣ ገንቢ ያልሆነ ትችትን፤ እንደ ጭቃ አንስቶ መለጠፍን አቁመን ለዋና ግባችን (የስርአት ለውጥ) አብረን ከሰራን፤ በየምንኖርበትርበት ሃገር የውጭ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን በማሳደርና ህገር ውስጥ ለሚደረገው ትግል የተሟላ ድጋፍ በመስጠት ገዢው ቡድን ቢያንስ ወደ ክብ ጠረጴዛ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል። ያለ ጫና ከህወሃት/ኢህአዴግ እርቅ መጠበቅ ከየዋህነትም አልፎ ጅልነት ነው።
አላህ ኢትዮጵያን ከነ ህዝቦቿ ይባርካት
ባህር ከማል
ለአስተያየት bahirk@hotmail.com
ዋቢ:
• ይድረስ ለኢህአዴግ አመራር አባላት ልጆቻችሁ ቻይና ምን
እየሰሩ ነው? ተመስገን ደሳለኝ ከፍትህ ገዜጣ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment