Wednesday, January 15, 2014

ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መመሪያን መተውን አስታወቀ

ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን በቅርቡ ከሚኒስትሮች እና ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይትና ግምገማ ላይ ” ህዝቡን ለመምራት የሚነደፉ ንድፈ ሀሳቦች ( ቲዮሪዎች) በየጊዜው ካልተሻሻሉ የሚዝጉ በመሆናቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲ በልማታዊ ዲሞክራሲ እንዲተካ ተደርጓል ብለዋል። የኢህአዴግ መንግስት ይበልጥ የሚገለጸው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ሳይሆን በልማታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው በማለት አቶ በረከት ገለጽዋል

አቶ በረከት አብዮታዊ ዲሞክራሲ በልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ከመተካቱ በፊት ፣ ግንባሩ ለ3 ተከፍሎ እንደነበር ገልጸዋል። አንደኛው የአመራር ወገን “ችግራችን የውስጥ ነው እና በቅድሚያ የውስጥ ችግራችንን እንፈትሽ የሚል” አቋም ሲይዝ ፣ ሌላው ወገን ደግሞ ዋናው ችግራችን ሻዕቢያ በመሆኑ በቅድሚያ ሻዕቢያን እንውጋ የሚል አቋም ይዞ እንደነበር፣ እና ሻእቢያን ከወጋን በሁዋላ ወደ ውስጥ ችግራችን እንመልከት የሚለው ሶስተኛው አማራጭ አሸንፎ መውጣቱን ገልጸዋል

በ1997 ዓም ዋናው የአመጽ ሀይል የነበረው ስራ ያጣውና ተስፋ የቆረጠው ወጣት ነው በማለት የገለጹት አቶ በረከት ለወጣቱ ስራ ካልተፈጠረለት በመንግስት እና በአገር ላይ እንደሚያምጽ ገልጸዋል። መንግስት የምርጫ 97ትን አመጽ ያስነሱት ተቃዋሚዎች ናቸው ብሎ ሲከስ መቆየቱ ይታወቃል።

ኢህአዴግ ከባላሀብቱ ነጻ የሆነ መንግስት ለመመስረት መነሳቱን የገለጹት አቶ በረከት፣ ስልጣን ላይ የሚያመጣን አርሶአደሩና በከተማ ያለው ጭቁኑ ህዝብ ነው እንጅ ባለሀብቱ አይደለም ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በባለሀብቱ ገንዘብ የሚተዳደር አይደለም ያሉት አቶ በረከት፣ ገንዘብ ከፈለገ ከባላሀብቱ በግብር መልክ መውሰድ እንደሚችል ተናግረዋል። ይህ መንግስት ለህልውናው የራሱ የገቢ ምንጭ እንዳሉት የጠቀሱት አቶ በረከት፣ አየር መንገድን ባንኮችን እና መብራት ሀይልን በምሳሌነት አንስተዋል። የመንግስትን አስተዳደር ያለምንም ችግር ለማስኬድ የባለሀብቱም የውጭ ድጋፍም እንደማያስፈልግ አቶ በረከት አክለዋል።

አቶ በረከት፣ ኢህአዴግ ምርጫውን ያለባለሀብቶች ድጋፍ ማሸነፍ እንደሚችል እየገለጹ ባለበት ጊዜ በድንገት የመንግስት ተቋሞችን በመግለጽ በቂ ገንዘብ አለን ማለታቸው ተሰብሳቢዎችን ማስገረሙን ስብሰባውን የተከታተሉት አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራር ገልጸዋል። አመራሩ እንዳሉት ኢህአዴግ ለምርጫ ማስኬጃ ከመንግስት ገንዘብ እንደሚወሰድ የ አቶ በረከት ንግግር በቂ ማሳያ ነው ።

መንግስት የራሱ ገንዘብ ከሌለው እንደምእራብ የአፍሪካ አገራት ይሆናል ያሉት አቶ በረከት፣ የኮትዲቩዋር ሚኒስትሮች ደሞዛቸውን የሚወስዱት ኮትዲቯር ከሚገኘው የፈረንሳይ ኢምባሲ ነው ይላሉ። በኬንያም ሁኔታው ተመሳሳይ መሆኑን አቶ በረከት አክለዋል

ኢህአዴግ በ2002 በተደረገው ምርጫ ከግል ባለሀብቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ይታወቃል።

በባቡር ግንባታ፣ በመንገድ ቁፋሮና በትራንሰፖርትና እጥረት የተነሳ በአዲስ አበባ መኖር ያስጠላል ያሉት አቶ በረከት ያም ቢሆን ግን ህዝቡ ልማት ነው በሚል እንደሚቀበለው ገልጸዋል ።

No comments:

Post a Comment